ዮሐንስ ኃይሉ (ኩባ) የት ይገኛል?

ለየት ባለው ፀጉሩ እና ለተጫወተባቸው ክለቦች ለረጅም ዓመታት በማገልገል የሚታወቀው ዝምተኛው ኩባ የት ይገኛል ?

የእግር ኳስ ጅማሮው በኒያላ ነው። ከክለቡ ሦስተኛ ቡድን ካደገ በኃላም አሳዳጊ ቡድኑን ለስድስት ዓመታት አገልግሏል። በ1997 ደግሞ ለመተኃራ ስኳር አንድ የውድድር ዓመት ካሳለፈ በኃላ ጥሩ ቆይታ ወዳደረገበት መከላከያ ተሸጋገረ። ዘጠኝ ዓመታት በቡድኑ ተጫውቶ አምስት ዓመታት ጦሩን በአምበልነት መርቶ ሁለት የጥሎ ማለፍ ዋንጫዎች አንስቷል። በ1998 በአስራት ኃይሌ መሪነት የጥሎ ማለፍ ዋንጫ ባነሳው ድንቅ ስብስብ ውስጥም አባል ነበር።

የመከላከያን ተከላካይ ክፍል ለበርካታ ዓመታት ከመራ በኃላ በ2007 ወደ ከፍተኛ ሊጉ ወልዲያ በማምራት ቡድኑን በአምበልነት እየመራ ወደ ፕሪምየር ሊግ ገብቷል። በውድድር ዓመቱ መጨረሻ ላይም ክለቡ ወደ ፕሪምየር ሊግ ማደጉ ያረጋጠበት ወሳኝ ጨዋታ ላይ ሙገር ሲሚንቶ ላይ ግብ አስቆጥሯል። በ2010 ከወልዲያ ጋር ከተለያየ በኃላ ከክለብ እግር ኳስ የራቀው ይህ ተከላካይ ከእግርኳስ የራቀበትን ምክንያት እና ተያያዥ ጉዳዮች አስመልክቶ ከሶከር ኢትዮጵያ ቆይታ አድርጓል።

ከእግርኳሱ የራቀበት ምክንያት

የአቅም ችግር የለብኝም፤ ብዙ አሰልጣኞች ይመሰክራሉ። መንገዱን አለማወቅ ነው እንጂ ሌላ ምክንያት የለውም። በሃገሪቱ ካሉ ትላልቅ አሰልጣኞች ጋር ሰርቻለው። አሥራት ኃይሌ፣ ሰውነት ቢሻው፣ አብርሃም ተክለሃይማኖት፣ አብርሃም መብራቱ ፣ ገብረመድኅን ኃይሌ እና የመሳሰሉ አሰልጣኞች ስር ስለሰራሁ ብዙ ልምድ አለኝ። በዚህ አጋጣሚ ሁሉም አሰልጣኞች ብዙ ጥሩ ነገር ሰጥተውኛል፤ እዚህ ለመድረሴም የነሱ ድርሻ አለበት። እና ከእግር ኳሱ የራቅኩበት ምክንያት መንገዱን አለማግኘት ነው እንጂ አሁንም ከልምምድ አልራቅኩም። የመጫወት ፍላጎቱም ብቃቱም አለኝ።

አሁን ስላለበት ሁኔታ

አሁን ልምምዴን እየሰራሁ በግል ስራ ላይ ነኝ። ወደ ክለብ እግር ኳስ ለመመለስ ፍላጎቱ አለኝ። ለዛም ነው ልምምዴን የምሰራው። ግን ያለው ሁኔታ ትንሽ አስቸጋሪ ነው። እኔ ከሰው ጋር ብዙም አልግባባም። ወደ እግር ኳስ መመለስ ግን እፈልጋለሁ። ጫማዬን አልሰቀልኩም አሁንም አቅሙ አለኝ። አሁን የግል ስራ በመስራት ላይ ነኝ። አስኮ አከባቢ ሥጋ ቤት እና ግሮሰሪ አለኝ።

ስለ ክለብ ቆይታዎቹ

ኒያላ ያደግኩበት ክለብ ነው። በክለቡም ለስድስት ዓመታት ቆይቻለው። ከዛ በኃላ በመተሐራ ስኳር አንድ ዓመት ተጫውቼ ወደ መከላከያ ነው ያመራሁት። መከላከያ በጣም ጥሩ ክለብ ነው። በክለቡ ቆይታዬ በጣም አሪፍ ጊዜ አሳልፌያለው። በመከላከያ ብዙ ነገር ተምርያለው። ልክ እንደ ብቁ ወታደር ሥነ-ስርዓት በደምብ ያወቅኩበት ክለብ ነው። መለማመጥ ምናምን አልወድም። ልምምዴን በአግባቡ እሰራለሁ። ራሴን በደምብ አዘጋጃለው። ከዛ ውጭ ወደ ቤት ነው።

ወልዲያ ደግሞ ሌላው ጥሩ ጊዜ ያሳለፍኩበት ክለብ ነው። ክለቡ ወደ ፕሪምየር ሊግ ሲገባ አምበል ነበርኩ ። ጥሩ ስብስብ ነበር። ነብሱን ይማረው እና ንጉሤ ደስታም ጥሩ አሰልጣኝ ነበር። በመጨረሻ ግን ውለታችን ተረስቶ ክለቡ ለቀቅን። ደጋፊውም ጥሩ ነገር የሚመጣ መስሎት ነበር። ግን በሚያሳዝን መልኩ ወረደ።

ስለ ነበረው ልዩ የመሪነት አቅም

መሸነፍ አልወድም። በመሪነት ባህርዬ ከኔ ጋር የተጫወቱ ተጫዋቾች ይሰሙኛል፤ ያከብሩኛል። ያለኝን ሁሉ ነገር ሳልሰስት እሰጣለሁ። የመሪነት ክህሎት ደግሞ ከድሮ ይዤው የመጣሁት ነገር ነው። አብዱልፈታህ ይባላል፤ ኒያላ ነው የተገናኛነው። በሁሉም ነገር የገራኝ እሱ ነው። እሱም መሸነፍ አይወድም ጠንካራ ሠራተኛ ነው። እኔም መሸነፍ አልወድም ጠንካራ ሰራተኛ ነኝ ። ተጨማሪ ልምምዶችም እሰራለው። ረጅም ዓመት የመጫወቴ ምስጢሩም እሱ ነው። ከልምምድ በኃላም ራሴን እጠብቃለው። ረጅም እረፍትም እወስዳለው። ከእጅ ስብራት ውጭ ጉዳት ደርሶብኝ አያውቅም። ከዓመት ዓመት ሙሉ ጨዋታዎችን ነበር ያደረግኩት።

ስለ ብሔራዊ ቡድን

2002 ላይ በኤፊ ኦኖራ ተጠርቼ ነበር። ልምምድ ጀምረን አሰልጣኙም ወዶኝ ነበር። ግን በአንዳንድ ጉዳዮች ትጥቅ ከወሰድኩ በኃላ ቀናት ሲቀሩት ተቀነስኩ። በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ሃገሬን ባላገለግልም በእግርኳስ ሕይወቴ ግን ደስተኛ ነኝ።

በልዩ ስለሚታወቅበት ፀጉሩ

አሁን ፀጉሬ ቆርጩዋለው። ከእግር ኳስ ውጭ ባለው ሕይወት ላይ እንደዚህ ፀጉር ስታሳድግ ብዙም ሰው ደስ አይለውም። በዛ ምክንያት ተቆርጬዋለሁ። ዐቢይ ሃይማኖትም ልክ ኳስ እንዳቆመ ነበር የተቆረጠው። ዘፋኝ ተዋናይ ምናምን ካልሆንክ ፀጉር ማሳደግ ከባድ ነው።

የቤተሰብ ሁኔታ

አግብቼ ሁለት ልጆች አፍርቻለው። ሁለቱም ሴቶች ናቸው። ማራኪ እና ኤልዳና ይባላሉ።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!