የሴቶች ገፅ | ቆይታ ከአዳማ ከተማዋ ነፃነት ጸጋዬ ጋር

በዛሬው የሴቶች ገፅ እንግዳችን ወጣቷ እና በአጭር ጊዜ ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆነችው የአዳማ ከተማዋ ተከላካይ ነፃነት ፀጋዬን በአዝናኝ ጥያቄዎች መሰናዶ አቅርበናታል፡፡

ሲዳማ አለታ ጩኮ በምትባል ገጠራማ አካባቢ ነው መነሻዋ። ዛሬ ላይ በእግር ኳሱ እናንሳት እንጂ በትምህርቷም ጠንካራ እንደሆነች ይነገርላታል፡፡ቤተሰቦቿ በትምህርቷ ብቻ ገፍታ ማየትን ቢያልሙም እሷ ግን እየተደበቀች ከወንዶች ጋር በመጫወት ከትምህርቷ ጎን ለጎን በመከወን ጊዜዋን ታሳልፍ እንደነበር መለስ ብላ ታወሳለች። የትውልድ አካባቢዋን ወክሎ በመጫወት የተነሳው የተጫዋችነት ዘመኗ ለሲዳማ ዞን እንዲሁም ለደቡብ ክልል የፕሮጀክት አልያም ሀገር አቀፍ የእግር ኳስ ሻምፒዮናዎች ላይ ተሰልፋም በመጫወት አሳልፋለች፡፡ ከእግር ኳሱ በዘለለ የመረብ ኳስን በልጅነቷ አጣምራ በመጫወት ጉዞዋ ቢቀጥልም ወደ እግር ኳሱ ያዘነበለው አቅሞ ይኸው ለዛሬው ውጤታማነቷ አግዟታል፡፡2009 የሲዳማ ቡና የወቅቱ አሰልጣኝ የነበረው ፍሬው ኃይለገብርኤል የውስጥ ውድድርን ስታደርግ ይመለከታትና ወደ ሲዳማ ቡና እንድትገባ ያደርጋታል፡፡ እሷም ያለ ማመንታት ሲዳማ ቡናን ተቀላቅላ እስከ 2010 ክረምት ድረስ በመስመር ተጫዋችነት፣ ተከላካይነት እና ቡድኑን በአምበልነትም ጭምር እስከ መምራት ደርሳም አገልግላለች፡፡

በክለቡ አጭር ጊዜን ብቻ ብትቆይም በነኚህ ጥቂት ጊዜያት ባሳየችው ብቃት መነሻነት በ2011 አዳማ ከተማን በመቀላቀል በግሏ ምርጥ ጊዜን በማሳለፍ ከቡድኗ ጋር የፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ማንሳት ችላለች። በኢትዮጵያ የኦሊምፒክ እና የዋናው ብሔራዊ ቡድን ውስጥም በቅርቡ ተጠርታ የመጫወት ዕድሉን አግኝታለች፡፡

የአዳማ ከተማ ቆይታዋ ዘንድሮ የሚያበቃው እና ከትልልቅ ክለቦች ጋር ከሰሞኑ ስሟ እየተነሳች የምትገኘው የግራ መስመር ተከላካይዋ ነፃነት ፀጋዬ የዛሬው የሴቶች ገፅ እንግዳችን ነች፡፡

እግር ኳስ ተጫዋች ለመሆን አርዓያ ያደረግሺው ማንን ነው ?

ለእኔ አርዓያዬ ወይሸንት ፀጋዬ (ኦሎምቤ) ነች፡፡ ሲዳማ ቡና እያለሁ ነበር በደንብ ያወኳት። እሷን ካወኳት ጊዜ ጀምሮ ብዙ ነገሮችን ትመክረኛለች። እኔ ልጅ ስለሆንኩ ስለ ኳስም ሆነ ስለ ክለብ እውቀቱ አልነበረኝም። የማውቀው ብዙም ነገር አልነበረም። እሷ ግን ካየችኝ ጀምሮ ልክ እንደ እህት በጣም ነበር የምትመክረኝ። እኔ ከፕሮጀክት ገና ወደ ሲዳማ ስገባ ጨዋታ ነበረን። ከንግድ ባንክ አዲስ አበባ ላይ ነበር። ሁላችንም የወረዳ ልጆች ነበርን፤ ማንም ሲኒየር ተጫዋች ቡድናችን ውስጥ የለንም ነበር፡፡ ያን ጨዋታ አቻ ነበር የወጣነው። ኦሎምቤ እሱን ጨዋታ እያየች ነበር። የዛን ቀን አሰልጣኝ ፍሬው ከእርሷ ጋር አስተዋወቀኝ። ያኔ አይታኝ ስለ ነበር በደንብ መከረችኝ። ማስተካከል እና ማሻሻል ያለብኝንም ነገረችኝ። እኔም እሷ ከነገረችኝ ጊዜ ጀምሮ ብዙ ነገሮች እያስተካክልኩ መጥቻለሁ። ለእኔ አይቼው ያደኩት አርዓያ ባይኖረኝም ኦሎምቤን ካወኳት ጊዜ ጀምሮ ምሳሌዬ እሷ ናት፡፡

በኮሮና ምክንያት ውድድሮች ከተቋረጡ ወራቶች አስቆጥረዋል። ነፃነት እንዴት ነበር ጊዜዋን ስታሳልፍ የነበረው ?

አብዛኛዎቹን ጊዜያት ማሳልፈው ፊልም አያለሁ። በጣም ደግሞ እናቴን አግዛታለሁ፤ ቤት ውስጥ ስራዎችን በመስራት ማለቴ ነው፡፡ በሳምንት ሦስቴ ደግሞ ልምምዶችን እሰራለሁ። አሁንም እንደዛ እያደረኩኝ ነው እያሳለፍኩ የምገኘው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መፅሃፍ አነባለሁ። አዳማም ሆኜ ትምህርቴን እየተማርኩ ስለነበረ በሚገባ እንዳነብም ጊዜ ሰጥቶኛል፡፡ በስፋት ግን ጠዋት ተነስቼ ሩጫ እሮጣለሁ። ሁለት ቀናትን መርጬ ደግሞ ቤት ውስጥ እሰራለሁ። ብዙም አብረውኝ ስፖርት የሚሰሩ በአካባቢዬ ስለሌሉ ብቻዬን ነው የምሰራሁ። ሩጫንም ሆነ በቤት ውስጥ በግሌ እሰራለሁ። በሳምንት ሶስቴ በደንብ በመስራት ጊዜዬን አሳልፋለሁ፡፡

በሁለት ክለቦች የመጫወት ዕድሉ ገጥሞሻል። ለአንቺ ጥሩ የውድድር ዓመት ያሳለፍሺበት መቼ ነው ?

ሲዳማ እያለሁ አስጨናቂ ጊዜ ነበር። በዚያን ጊዜ ክለቡ ውስጥ የነበረው ነገር ጥሩ አልነበረም፡፡ምንም የተስማማኝ ወቅት አልነበረም። ግን አዳማ ከመጣሁ በኃላ በጣም ጥሩ ጊዜን ነበር ያሳለፍኩት። ምክንያቱም ብዙ ልምድ ያላቸው በቡድኑ ውስጥ አሉ። እነ ሎዛ፣ ሴናፍ፣ ሰናይት፣ መስከረም፣ ኦሎምቤ፣ አልፊያ እጅግ ብዙ ብዙ ትምህርት ወስጃለሁ። ሲዳማ እያለሁ ብዙም አልችልም ነበር፤ በቃ ቢያንስ አንድ ወይንም ሁለት ኳሊቲ ብቻ ነው ያለኝ። መሮጥ እና ኳስ መምታትን ብቻ ነበር የምችለው። ምክንያቱም በሰዓቱ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ስላልነበሩ መጠለዝ እና ማግባት በቃ። አዳማ ከመጣሁ በኃላ ብዙ ነገርን ነው ያወቅኩት። በተለይ በመጣሁበት ዓመት 2011 ጥሩ ነበር። ለእኔ በአዳማ ያሳለፍኳቸው ዓመታት ደስ ብለውኝ ነው ክፉም ነገር ገጥሞኝ አያውቅም ምክንያቱም። እኔ የማደንቃት ኦሎምቤ አጠገቤ ነው ያለችሁ፡፡ ትነግረኛለች ስህተቶቼን እየነገረችኝ አብራኝ ነበረች።

እግርኳስ ተጫዋች ባትሆኚ ኖሮ በምን የሥራ መስክ ላይ እናገኝሽ ነበር ?

2008 የአስራ ሁለተኛ ክፍል ተፈታኝ ነበርኩ። 2009 አጋጣሚ ሆኖ ውጤት አልመጣልኝም ነበር፡፡ ከቤተሰቦቼ ኳስ እንድጫወት ማንም የሚፈልግ አልነበረም። እኔም በግድ እየተደበቅኩ ነበር የምጫወተው። እየተማርኩ ጨዋታ ሲኖር ውድድር ሲኖር ጥዬ ነበር የምሄደው። አለታ ወንዶ አምስት አመት ኖሪያለሁ፤ እዛ ነበር የምማረው። በቃ ኳስ አለ ከተባልኩ ማንም ሳያውቀኝ ሄዳለሁ። ስመጣ ደግሞ ትምህርቴን እቀጥላለሁ። እኔ እየተማርኩ በኃይሏ የሲዳማ አሰልጣኝ እያለች ወንዶ መጥታ እናግራኝ ነበር፡፡ እኔ አስተምርሻለሁ ነይ እኔ ጋር ተጫወቺ ብላኝ። እኔ ደግሞ አይ መጀመሪያ ትምህርቴን እጨርሳለሁ ትምህርቴን ከጨረስኩ በኃላ ነው በእግር ኳሱ የምቀጥለው አልኳት። ለዚህም ቶሎ ወደ ኳሱ አልገባሁም። ዛሬ እግር ኳስ ተጫዋች ባልሆን ትምህርቴን ቀጥዬ ጨርሼ የሆነ ስራ ላይ እሰማራ ነበር፡፡ 2009 ውጤት ሲጠፋ ግን ተጫዋች ሆንኩ።

በፕሪምየር ሊግ ደረጃ በመጫወት አራት ዓመታት አልፈውሻል። ስትጫወቺ አይተሻት አብራኝ ብትጫወት ደስ ይለኛል የምትያት ተጫዋች ትኖር ይሆን ?

አዎ አለች፡፡ ከብርቱካን ገብረክርስቶስ ጋር ብጫወት ደስ ይለኛል። አጋጣሚ ሆኖ ብሔራዊ ቡድን አብረን ነበር፡፡ ግን አንድ ላይ ሆኜ አብሪያት ብጫወት ደስ ይለኛል፡፡

በጨዋታ ውስጥ በተቃራኒው ሆነሽ ስትገጥሚያት የከበደሽ፣ የፈተነችሽ፣ አላፈናፍን ያለችሽ ተጫዋች ማን ትሆን ?

እስከ አሁን የፈተነኝ የለም፡፡ አጋጥሞኝም አያውቅም። በራሴ ስለምተማመን እጫወታለሁ አቅሜንም ስለማውቀው። ምክንያቱም እኔ እንደምረዳው እኔም ሰው ነኝ። እሷም ሰው ነች ብዬ ነው የማስበው። እኔም ሁለት እግር አለኝ እሷም አላት ስለዚህ እስከዛሬ አጋጥሞኝ የሚያውቅ የለም፡፡

ለአንቺ ምርጧ ተጫዋች ማናት ?

በዚህ አጋጣሚ የማደንቃት ሎዛን ነው፡፡ ስትጫወት በጣም ፍላጎት እና ወኔ አላት። አብራኝ አዳማ ስትጫወት በደንብ አይቻታለሁ። ምንም ሳትፈራ ትጫወታለች። ደስ የምትለኝ እሷ ናት፡፡

በእግር ኳስ ዘመንሽ የምታደንቂው አሰልጣኝ ማን ይሆን ?

ለእኔ ማደንቀው ሳይሆን ማመሰግነው ቢባል ደስ የሚለኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ብቻ ነው፡፡ በጣም ነው የማመሰግነው። ዛሬ እዚህ ለመድረሴ አስተዋጽኦ ስላደረገልኝ፡፡

ደስተኛ የሆንሺበት ወቅት መቼ ነው ?

መጀመሪያ አዳማ እንደገባሁ ሁለት ጨዋታ አውት ኦፍ ነበርኩ። እንደዛ ስሆን በጣም በጣም አልቅሻለሁ። ከምልህም በላይ አልቅሼ ነበር። ግን ብዙዎቹ አጨዋወቴን ስለሚያውቁ በደንብ እየመከሩኝ ከዛ በኃላ በሌላ ጨዋታ አርባ ደቂቃ ምናምን ነበር ዕድል ተሰቶኝ ገብቼ ተጫወትኩኝ። እና ሁለት ኳሶችን አሲስት አደረኩ። ከዲላ እየተጫወትን ነበር። የዛን ቀን ሁለት ኳስ አቀበልኩ። በኃላ ቤስት መሆን ቻልኩ። ያኔ አርባ አምስቱን ደቂቃ በመጫወቴ በጣም ነው ደስ ያለኝ። እንዴት እንደ ተጫወትኩኝም አላውቅም። ያን ጊዜ ተናድጄ ስለገባሁኝ ያኔም ነበረ እጅጉን ደስ ያለኝ፡፡

ያዘንሽበት ወይም የተከፋሽበትስ ?

እየሳቀች… የተከፋውትም ቅድም እንደነገርኩህ ሁለት ጨዋታ አውት ኦፍ በመሆኔ ነው፡፡ ለምን አልጠበኩም ነበር። አሰልጣኙ በሰዓቱ ያሰበው ሲኒየሮች ስላሉ ነው ብሎ ሊሆን ይችላል። እኔ ደግሞ ያኔ አላሰብኩም። ከጨዋታ እወጣለሁ ብዬ አልጠበኩም። በጣም የከፋኝም ያለቀስኩትም በሁለቱ ጨዋታዎች ነበር፡፡

እግር ኳስ ተጫዋቾች ብዙ ገጠመኞች አሏቸው እንደው አንቺስ ምን አይነት ገጠመኝ አለሽ ?

አንድ ጊዜ ፕሮጀክት እያለሁ አንድ ጨዋታ ላይ ዳኛ ቢጫ ካርድ ይሰጠኛል፡፡ እኔ ደግሞ ቢጫ ካርድም ሆነ ምንም አይቼ አላውቅም። ዳኛው ቢጫ አውጥቶ ሲሰጠኝ ከሜዳ ቀጥ ብዬ ወጣው (እየሳቀች)… ምንም አላውቅም ስለሰጠኝ ብቻ ውጪ ያለኝ መሰለኝ። አልተናደድኩም ግን የሰጠኝ ለምንድነው ብዬ አላሰብኩም። እንደሰጠኝ ዝም ብዬ ነው የወጣሁት። መጨረሻ ላይ ሁሉም ሳቁና እረ ግቢ ችግር የለውም ብሎ አሰልጣኙ ሲነግረኝ ተመልሼ ገብቼ ተጫወትኩ።

ተጫዋች ሆኖ ጓደኛ አይጠፋም ይባላል፡፡ የሚስጥሬ ተጋሪ አልያም የቅርብ ጓደኛዬ እሷ ናት የምትያት እግር ኳስ ተጫዋች አለች ?

የቅርብ ጓደኛ የለኝም። አንድ ልጅ ነበረች ሲዳማ አብራኝ ትጫወት የነበረች። አሁን አቁማ ትምህርቷን እየተማረች ነው ያለችው። እሷ ነበረች በሰዓቱ። አሁን ግን የቅርብ የምለው ጓደኛ የለኝም፡፡

እስቲ ስለ ባህሪሽ እናውራ ምን አይነት ባህሪ አለሽ ? የተለየስ የምትይው ነገር አለሽ ?

የተለየ ባህሪ የለኝም እኔ፡፡ ማንም ሲጫወት ኳስ አያለሁ። ልምምድ ስሰራ ሲሪየስ ሆኜ ነው የምሰራው፤ አልቀልድም፤ አልስቅም። በጨዋታ ላይም ቀልድ አላውቅም። ምክንያቱም ስራዬ ነው ብዬ ስለማስብ። ከአካባቢዬ ርቄ ወጥቼ ትምህርቴንም ትቼ የምጫወተው እንጀራዬም ነው ብዬ ስለማስብ ስለሆነ አንድም ቀን ስራ ላይ ሆኜ ቀልጄ አላውቅም። ከእግር ኳሱም ውጪ ዝምተኛ ነኝ፤ በጣም ዝምተኛ። ማውራት ካለብኝ ትንሽ አወራለሁ። ከዛ ውጪ ግን ዝምተኛ ነኝ፤ ቤትም ሆኜ ውጪ ሆኜ፡፡

በመጨረሻም ከእግር ኳሱ ውጪ ያሉ እረፍቶችሽን በምን ታሳልፊያቸዋለሽ?

አዳማ እያለሁ ካምፕ ነበር፡፡ ካምፕ ስለምውል ምንም አልፈልግም፤ ንቅንቅም የለም፡፡አዳማ ደግሞ ነፃነት አለኝ አንዴ ልወጣ እችላለሁ። ከዛ ውጪ ግን አልወጣም። አንዳንድ መፃህፍትን አነባለሁ። ፊልሞችን አያለሁ። ሰፊውን ጊዜ ደግሞ እተኛለሁ። እረፍት አደርጋለሁ፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!

error: