በ2011 ለሀድያ ሆሳዕና ሲጫወቱ የነበሩ ተጫዋቾች በክለቡ ላይ ቅሬታ አሰሙ

ከሀድያ ሆሳዕና ጋር በ2011 በከፍተኛ ሊጉ ሲጫወቱ የነበሩ ተጫዋቾች “ቃል የተገባልን የመሬት ሽልማት አልተሰጠንም፤ እንግልታችንን ህዝቡ ይወቅልን” ሲሉ ቅሬታ አሰምተዋል፡፡

ሀድያ ሆሳዕና በ2011 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሐ በበላይነት አጠናቆ ነበር ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማደግ የቻለው። ክለቡ ወደ ሊጉ ሲያድግ በክለቡ ውስጥ ለነበሩ የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ክለቡ የመሬት ስጦታ እና ከሰላሳ እስከ ሀያ ሺህ የሚደርስ የገንዘብ ሽልማትን እንደሚያበረክት ቃል ገብቶ በመስከረም ወር 2012 ለተጫዋቾቹ የገንዘቡን ሽልማት ቃል በገባው መሠረት ቢያበረክትም የመሬቱ ሽልማትን በሒደት አስፈፅማለሁ በሚል ሀሳብ ለተጫዋቾቹ እንደገለፀላቸው ይናገራሉ፡፡ ከአንድ ወር በፊት የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ መላኩ ማዶሮ ለድረገፃችን በጥቂት ጊዜ ውስጥ መሬቱ እንደሚሰጣቸው የነገሩን ቢሆንም አሁንም ችግሩ አለመፈታቱን አስራ ዘጠኝ የሚደርሱ ተጫዋቾች ለሶከር ኢትዮጵያ ተከታዩን የቅሬታ ሀሳብ ልከውልናል።

“ለሽልማት ብለው መሬት ለመስጠት ቃል ከገቡ አንድ ዓመት አልፎናል። እስከ አሁን ግን እጃችን አልገባም። እንዲሰጠን እየተመላለስን ጠይቀናል። ለሀገር ውስጥ ተጫዋቾች መሬቱ ይሰጣችዋል ተብለን ለውጪ ተጫዋቾች ግን ስለማይቻል በመሬቱን ምትክ ወደ ገንዘብ ተለውጦ የላቸው አምስት ለሚሆኑት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ከሰባ አስከ ዘጠና ሺህ ብር የሚደርስ ገንዘብም ወስደዋል። እኛ ግን በማኅበር ተደራጁ ተብለን ብር ቆጥበን ወይም ከብራችን አልሆን ወይም ከመሬቱ አልሆንም። ቀጣይ ሳምንት እናስረክባለን ቀጣይ ሳምንት እንሰጣችዋለን በሚል በተደጋጋሚ ተመላለስን። ሁላችንም ከያለንበት ክፍለ-ሀገር ተሰብስበን ወደ ሆሳዕና እየሄድን ብንጠይቀም መልስ አላገኘንም። ከንቲባውንም ጠይቀናል፤ የማዘጋጃ ኃላፊዎችንም ጠይቀን የሚሰጡን ምላሽ በአጭር ቀን ውስጥ መሬቱን እንደሚያስረክቡ ነው። አጉል ተስፋ ሆኖ ስለቀረ እና እንግልታችንም ስለበዛ የመጨረሻ አማራጭ አድርገን ወደ ሚዲያ መጥተናል። ህዝቡ እንዳልወሰድን ይታወቅልን።”

በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ እንዲሰጡን የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ መላኩ ማዶሮ ጋር ደጋግመን ብንደውልም ስልክ ማንሳት ባለመቻላቸው የክለቡን ምላሽ ማካተት ሳንችል ቀርተናል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!