“ጥሪ በተደረገ ቁጥር ውስጤ ከሚጎዳ ራሴን ከብሔራዊ ቡድን አግልያለሁ” ግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ

የሲዳማ ቡናው ግብ ጠባቂ መሳይ አያኖ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መጠራት እየተገባኝ አልተጠራሁም፤ ይህ በመሆኑ ራሴን ማግለሌ ይታወቅልኝ ሲል ለሶከር ኢትዮጵያ በላከው ሀሳብ ተናግሯል፡፡

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ በቅርብ ጊዜያት ከታዩ ምርጥ ግብ ጠባቂዎች መካከል የቀድሞው የደቡብ ፖሊስ፣ አርባምንጭ ከተማ እና ከ2010 ጀምሮ ደግሞ ለሲዳማ ቡና እየተጫወተ የሚገኘው መሳይ አያኖ ተጠቃሽ ነው፡፡ ግብ ጠባቂው በተለይ በ2011 ሲዳማ ቡና በፕሪምየር ሊጉ ከመቐለ 70 እንደርታ ቀጥሎ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቅቅ በ26 የፕሪምየር ሊጉ ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ ክለቡን ከማገልገል ባለፈ የፕሪምየር ሊጉ ሦስት እጩ ግብ ጠባቂዎች የዓመቱ ኮከቦች ዝርዝር ውስጥ መካተት እንደቻለም የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው፡፡ በተሰረዘው የ2012 የፕሪምየር ሊግም ጥቂት ጨዋታዎችን ብቻ በጉዳት መጫወት ባይችልም ካገገመ በኃላ በውድድር አመቱ ሊጉ እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ ተጫውቷል።

ተጫዋቹ ዓምና ለኢትዮጵያ ለብሔራዊ ቡድን ጥሪ ቢደርሰውም በስተመጨረሻ ከፓስፖርት በጊዜ ካለመድረስ ጋር በተያያዘ ሳይሳካለት እንደቀረ እና ይህም በወቅቱ ቅሬታ እንደፈጠረበት እና ” ድርጊቱ ሆን ተብሎ ተደርጎብኛል” በማለት ለሶከር ኢትዮጵያ መግለፁ ይታወሳል፡፡ በቅርቡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው የተሾሙት ውበቱ አባተ በዛሬው ዕለት ለአርባ ተጫዋቾች የብሔራዊ ቡድን ጥሪን ሲያደርጉ ከተጠሩት አምስት ግብ ጠባቂዎች መካከል መሳይ አያኖ አለመካተቱን ተከትሎ “ራሴን ከብሔራዊ ቡድኑ ማግለሌ እንዲታወቅልኝ” በማለት ተከታዩን ሀሳብ ሰጥቶናል፡፡

“ጥሩ ዓመታትን እያሳለፍኩ እና በጥሩ ብቃት እየተጫወትኩ ለብሔራዊ ቡድን ግን አልጠራም። ይሄ ደግሞ እኔ ላይ ፌር ያልሆነ ሥራ እየተሰራ እንደሆነ እንዳስብ አድርጎኛል። ሀገሬን አገለግላለሁ ብዬ ብዙ ጠበቅኩ፤ የአሁኑንም ስጠብቅ ነበር። ከዚህ በኋላ ግን ውስጤ እንዲጎዳ አልፈልግም። በጣም ነው የተሰማኝ። ከዚህስ በላይ አቅሜን እንዴት ማሳየት አለብኝ? እናንተ ብዙ ጨዋታዎችን አይታችኋል። ቢያንስ አሰልጣኝ ውበቱ አቅሜን ያውቀዋል። ከሁሉም የተሻለ ቢኖረኝ እንጂ ያነሰ ብቃት የለኝም። ሀገሬን ለማገልገል ከዚህ በላይ መሥራት አይጠበቅብኝም። ስለዚህ ሁልጊዜ ጥሪ በተደረገ ቁጥር ውስጤ ከሚጎዳ ራሴን ከብሔራዊ ቡድን አግልያለሁ። ለመጫወት ፍላጎት ቢኖረኝም ከአሁን በኋላ ብጠራም የመሄድ ሞራሉም የለኝም።”

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!

error: