ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | መከላከያ አዲስ አሰልጣኝ ሲመድብ አንድ ተጫዋች አስፈርሟል

መከላከያ አሰልጣኝ በለጠ ገብረኪዳንን በዋና አሰልጣኝነት ቦታ ሲመድብ የግራ መስመር ተከላካይ አስፈርሟል፡፡

የ2012 ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን በኮሮና እስከ ተቋረጠበት ጊዜ ድረስ በአሰልጣኝ ሰለሞን ታደለ እየተመሩ ተሳትፎን ያደረጉት መከላከያዎች አሁን ደግሞ በለጠ ገብረኪዳንን ዋና አሰልጣኝ አድርገዋል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የመከላከያን የወንዶች ቡድንን በፕሪምየር ሊጉ ከረዳት እስከ ዋና አሰልጣኝነት አሰልጥነው ያለፉ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ረዳት በመሆን ሰርተዋል። አሁን ደግሞ የመከላከያ የሴቶች ቡድንን ዘንድሮ ለማሰልጠን ኃላፊነቱን ተረክበዋል፡፡

ከአሰልጣኝ ሹመት በኃላ አሰልጣኙ የመጀመሪያ ፈራሚ የአዳማ ከተማዋን ተከላካይ ነፃነት ፀጋዬን አድርገዋል፡፡ ከ2009 ጀምሮ ለሲዳማ ቡና በመጫወት የክለብ ህይወቷን ጅማሮ ያደረገችው የግራ መስመር ተከላካይዋ በ2011 ወደ አዳማ ካመራች በኃላ በገባችበት ዓመት የሊጉን ዋንጫ ያነሳች ሲሆን ዘንድሮ በክለቡ ቆይታን በማድረግ ወደ ሀዋሳ ለመቀላቀል ስምምነት ቀደም ብላ ብታደርግም መከላከያን ምርጫዋ አድርጋ ለሁለት ዓመት መፈረሟን ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግራለች፡፡

ክለቡ ራሱን ለማጠናከር በቀጣዮቹ ቀናት በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾችንም ሆነ ውላቸው የተጠናቀቁትን ውል ለማራዘም በድርድር ላይ ይገኛል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!