የውበቱ አባተ ምክትሎች ታውቀዋል

በትናንትናው ዕለት የዋሊያዎቹ ዋና አሠልጣኝ ተደርገው የተሾሙት ውበቱ አባተ አብረዋቸው የሚሰሩት ምክትሎችን አስታውቀዋል።

የቀድሞ የአዳማ ከተማ፣ ደደቢት፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ንግድ ባንክ፣ ሀዋሳ ከተማ፣ ፋሲል ከነማ እና የሰበታ ከተማ ዋና አሠልጣኝ ሆነው ያገለገሉት ውበቱ አባተ ትናንት በይፋ የብሔራዊ ቡድኑ ዋና ዋና አሠልጣኝ ተደርገው ተሹመዋል። አሠልጣኙም ለሁለት ዓመታት ብሔራዊ ቡድኑን እንደሚያሰለጥኑ እና በቆይታቸው ብሔራዊ ቡድኑን ለአፍሪካ ዋንጫ እንዲሁም ለዓለም ዋንጫ የመጨረሻ ፕሌይ ኦፍ የማድረስ ግዴታ ተጥሎባቸዋል። በትናንትናው መግለጫ ላይ የራሳቸውን ምክትሎች እንዲመርጡ እድል የተሰጣቸው አሠልጣኙም በዛሬው ዕለት ምክትሎቻቸውን ለይተው ማሳወቃቸውን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘው መረጃ ይጠቁማል።

በዚህም መሠረት በመብራት ኃይል እና ኢትዮጵያ ቡና በነበረው የተጫዋችነት ዘመን ትልቅ ስም የነበረው አንዋር ያሲን የመጀመሪያው የውበቱ ረዳት ሆኗል። በተጫዋችነት ዘመኑ ያገለገለውን መብራት ኃይል በአሠልጣኝነት ሲያገለግል ከነበረው አንዋር በተጨማሪ አሥራት አባተ ሌላኛው የውበቱ ረዳት አሠልጣኝ መሆኑ ታውቋል። በሴቶች እና ወንዶች እግርኳስ ላይ ትልቅ ስራ የሰራው አሥራት የአዲስ አበባ ከተማ ዋና አሠልጣኝ ከሆነ በኋላ የቢሾፍቱ እና ቡታጅራ ከተማ አሠልጣኝ ሆኖ አገልግሎ ነበር።

ከሁለቱ ረዳቶች በተጨማሪ የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ምርጥ ግብ ጠባቂ የነበረው ደሳለኝ ገብረጊዮርጊስ የዋሊያዎቹ የግብ ጠባቂዎች አሠልጣኝ በመሆን በውበቱ አባተ ተመርጧል። ደሳለኝ ከዚህ ቀደም በቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ ሆኖ መስራቱ ይታወሳል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!