የደጋፊዎች ገፅ| ቆይታ ከሲዳማ ቡና ደጋፊዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት አዲሱ ቃሚሶ ጋር

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የደጋፊዎቹን ቁጥር በመጨመር እና ለሊጉ ውበት በመፍጠር እየታዩ የመጡት የሲዳማ ቡና ደጋፊዎችን በመወከል በ’ደጋፊዎች ገፅ’ አምዳችን ከማኅበሩ ፕሬዝዳንት አዲሱ ቃሚሶ ጋር ቆይታ አድርገነው።

ሲዳማ ቡና በ2002 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ከተቀላቀለበት ጊዜ አንስቶ በየዓመቱ አዳዲስ ፊቶችን በማሳየት እና ጠንካራ ቡድን በመሥራት ጥሩ ተፎካካሪ ሆኖ እየዘለቀ መገኘቱ ይታወቃል። በተለይ ደግሞ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ወደተሻለ ምዕራፍ ተሻግሮ በዋንጫው ፉክክሩ ውስጥ በመግባት ለየትኛውም ቡድን ፈተኛ መሆን ችሏል። በቡድኑ ጥንካሬ ውስጥ ከዚህ ቀደም በሜዳው ላይ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ከሚያገኘው ደጋፊ ውጭ በተለያዩ ሜዳዎች እየተጓዘ የሚደግፍ ደጋፊ እምብዛም አልነበረውም። ሆኖም ያለፉትን ሦስት ዓመታት በአዲስ መልክ የደጋፊ ማኅበር ካዋቀረ እና የሚጫወትበተን ሜዳ ወደ ሀዋሳ ከለወጠ ወዲህ በሜዳውም ሆነ ከሜዳው ውጭ ቁጥሩ ቀላል የማይባል ደጋፊዎችን እያገኘ ይገኛል። ማኅበሩን ለመጀመርያ ጊዜ በፕሬዝዳንትነት እየመራ ከሚገኘው አዲሱ ቃሚሶ በክለቡ የድጋፍ እንቅስቃሴ እና የወደፊት እቅድ ዙርያ ያደረግነውን ቆይታ በተከታይነት ይዘን ቀርበናል። መልካም ንባብ!

ከቅርብ ዓመታት ጀምሮ ከሜዳ ውጭ በርከት ያሉ የሲዳማ ቡና ደጋፊዎችን አንመለከትም ነበር። አሁን ጥሩ የሚባል ከሜዳ ውጭ የደጋፊ ድባብ እየተመለከትን ነው። አዲሱ የደጋፊ ማኅበር ምን ቢሰራ ነው ከሜዳ ውጭ የደጋፊው ቁጥር የጨመረው ?

እውነት ነው። ከዚህ ቀደም በተበታተነ እና በተናጥል የሚደረገውን የድጋፍ መንገድ ለመቀየር የተለያዩ ሥራዎችን ሰርተናል። በመጀመርያም ደጋፊው ሰብሰብ ብሎ በብዛት ከሜዳ ውጭ ጨዋታዎችን መከታተል ይፈልግ ነበር። ሆኖም የተደራጀ እና የደጋፊውን ስሜት የሚረዳ ማኅበር ባለመኖሩ በተናጥል ነበር ቡድኑን ይደግፍ የነበረው። በአዲስ መልኩ የደጋፊ ማኅበር ከተቋቋመ በኃላ ግን ደጋፊውን ሰብስበን በማናገር የአደጋገፍ ሥርዓት እና ስፖርታዊ ጨዋነት ግንዛቤ ማሽጨበጫ በማዘጋጀት ተነጋግረናል። ክለባችን እንደሚታወቀው እስከ ታች ቀበሌ እና ወረዳ ድረስ ህዝባዊ መሠረት ያለው እንዲሁም የክለቡ መጠርያ ስያሜ በሆነው የቡና የንግዱ ሴክተር በጣም ተወዳጅ እና ሲዳማ ቡና የኔ ነው የሚል ስሜት አለ። ሆኖም ይህን አቀናጅቶ አንድ አድርጎ በባለቤትነ ኃላፊነት ወስዶ ወደ ክልል የሚሄዱ ደጋፊዎችን ይዞ የሚመራ መሪ ጠፍቶ ደጋፊው ተበታትኖ ይጓዝ የነበረ ቢሆን የደጋፊ ማኅበር ከተቋቋመ ወዲህ ክለቡ ከሜዳ ውጭ የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች እስከ ጎንደር ድረስ በሌሎችም ሜዳዎች በቁጥር በዝተን አንድ ሆነን በመጓዝ የምታዩትን ከሜዳ ውጭ ድባብ መፍጠር ችለናል። በፊት በተናጥል ለመደገፍ በሚሄዱት ላይ የተለያዩ መጎሳቆል እና አላስፈላጊ ነገር ሲደርስባቸው የነበሩ ተስፋ ቆርጠው የነበሩ ሁሉ አሁን መብታቸውን የሚያስከብር ደጋፊ ማኅበር በመኖሩ ከሜዳ ውጭ ሲዳማ ቡናን የሚመለከት ደጋፊያችን እየጨመረ ሊመጣ ችሏል።

የደጋፊ ማኅበሩ መቼ ተቋቋመ?

በቅርብ ነው፤ ሦስት ዓመት ቢሆነው ነው። ከዛ በፊት የደጋፊ ማኅበር አልነበረውም። እኔም የማኅበሩ የመጀመርያ ፕሬዝዳንት በመሆን እያገለገልኩኝ እገኛለሁ። ማኅበሩ ከተመሰረተ በኃላ በሺዎች የሚቆጠሩ የአባልነት መታወቂያ በማውጣት መዋጮ በመክፈል ክለቡን እያገዙ ይገኛሉ። ሊመዘግብ የሚመጣው ሁሉ የአባልነት መታወቂያ ሲወስድ የክለቡን ማልያ አብረን እንሰጣለን። ይህ መሆኑ አንድ ከለር ያለው ውብ ደጋፊ እንድንፈጥር ረድቶናል።

በክለቡ የቦርድ አመራር ውስጥ ያላችሁ ድርሻ እንዴት ነው ?

ከቦርዱ ጋር በቅርበት ይገናኛል። በክለቡ በሚደረጉ ማንኛውም እንቅስቃሴዎች ውስጥ በቅርበት ይሰራል። የሚፈጠሩ ችግሮችም ካሉ አብሮ ያስተካክላል። መልካም የሚባል ግኑኝነት ነው ያለን።

ሲዳማ ቡና ደጋፊዎች በሜዳም ከሜዳም ውጭ አዲስ የአደጋገፍ ስልት ይዘው በመጡበት ወቅት ነው የኮሮና ወረርሺኝ መጥቶ የተቋረጠው። አሁን ደግሞ ጨዋታዎች በዝግ መሆናቸው በደጋፊው ላይ ምን ተፅዕኖ ያሳድራል?

እኛን ራሱ በጣም ያሳሰበን ይህ ነው። ዘንድሮ ደጋፊው የክለቡን ጨዋታ የማይከታተል መሆኑ በጣም አሳስቦናል። ውድድሩ ታኅሣሥ ሦስት ይጀመራል ሲባል ኧረ እስከዛ ኮሮና ይጠፋል በማለት ደጋፊያችን የሚወደውን ክለብ ለመመለከት ከፍተኛ ፍላጎት እያሳየ ነው። በስልክም ደውለው የሚጠይቁን አሉ። እኛ ግን ያው ከሁሉም በላይ ጤንነት ይቀድማል። እግርኳሱ የሚኖረው ሀገር ሰላም ህዝቡ ጤና ሲሆን ነው። ደጋፊያችንም ይሄን ይረዳል ብለን እናምናለን። የሲዳማ ቡና ደጋፊ የቡድኑ ወሳኝ አስራ ሁለተኛ ተጫዋች ነው። በዚህ ምክንያት ጨዋታዎች ሁሉ በክፍት ቢሆን ደስታቸው ነው። ሆኖም ግን በሀገር የመጣ በመሆኑ ደጋፊዎቻችን ውሳኔውን የሚቀበሉት ይሆናል። አሁን ደግሞ በመገናኛ ብዙኃን እንደሰማነው ከሆነ ጨዋታዎቹ በዲኤስ ቲቪ በቀጥታ ስርጭት እንደሚተላለፉ መነገሩ በጣም መልካም ዜና ነው። ደጋፊውም በዚህ በጣም ደስተኛ መሆኑን እየነገረን ነው።

በኮሮና ዘመን ደጋፊዎቻችሁ በምን ዐይነት በጎ ሥራ አሳልፈዋል ?

ብዙ በጎ ሥራዎችን ሰርተዋል በተለያዩ ከተሞች ውሀ፣ የእጅ ንፅህና ሳሙና በማዘጋጀት እጅ የማስታጠብ ስራ ሠርተዋል። እንዲሁም የግንዛቤ ማስጨበጫ የቅስቀሳ ሥራዎችን በመስራት መልካም ተግባር ከውነዋል። በተጨማሪም የማዕድ የማጋራት ሥራ በራሳቸው ወጪ በማውጣት አስተባብረው ከፍተኛ የሆነ ተግባራት ሲከውኑ ቆይተዋል። ችግኞችን የመትከልም ሥራ ስንሰራም ነበር።

ከሌሎች የደጋፊ ማኅበራት ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል ?

ከሁሉም ክለብ ደጋፊ ማኅበሮች ጋር መልካም ግኑኝነት አለን። በተለይ ከሜዳ ውጭ ጨዋታ ለማድረግ ወደ ምንሄድበት ክልል ከመሄዳችን አስቀድሞ እየተደዋወልን አስፈላጊውን ሁኔታዎች እንዲያመቻቹልን እናደርጋለን። እነርሱም ወደ ሀዋሳ ሲመጡ ግኑኝነት ፈጥረን ከጥቁር ውሃ ጀምሮ በመሄድ አቀባበል እንደርግላቸዋለን። ደጋፊዎቻችን እንደምታቁት በስፖርታዊ ጨዋነት ላይ በጣም ሥርዓት ያለው ደጋፊ ነው። ሀዋሳ ላይ ምንም የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል አጋጥሞ አያውቅም። ይህም ከሌሎች ክለቦች ደጋፊዎች ጋር ያለን ግኑኝነት ጥሩ እንዲሆን አድርጎታል።

በተለይ ከወላይታ ድቻ ደጋፊዎች ጋር ዓምና ሶዶ ላይ በነበረው ጨዋታ ጥሩ ነገሮችን ተመልክተናል። በቀጣይስ ይህ ነገር እንዲቀጥል ምን ለማድረግ አስባችዋል ?

በጣም ደስ የሚል ከዚህ ቀደም የነበሩ ስጋቶችን ያስቀረንበት ነበር። የዓምናው የአንደኛው ዙር ጨዋታ ከከተማው ወጣ ብለው ነው ጥሩ አቀባበል ያደረጉልን። ከባለፉት ዓመትት አኳያ የተሻሉ ነገሮች መመልከት ችለናል። እኛም ሲመጡ ጥሩ አቀባበል ነው ያደረግነው። ይህ በቀጣይም እግርኳሳዊ ሰላም እና ፍቅር በሁለቱም ክለቦች መካከል ይቀጥላል ማለት ነው።

አንዳንድ ጊዜ ደጋፊ ክለቡን ከመደገፍ ይወጣ እና በአሰልጣኝ፣ በተጫዋቾች እና በክለብ አመራሮች ላይ ጣልቃ ገብነት ይታያል ይህ በእናንተ በኩል አለ ?

በዚህ ረገድ እንዲያውም የእኛ ደጋፊ ሊመሰገን ይገባል። ለምሳሌ በቡድኑ ላይ ሙሉ ኃላፊነት ያለው አሰልጣኙ ነው። በተጫዋች አሰላለፍ፣ የተጫዋች ቅያሪ፣ ከተጫዋች አያያዝ ጋር ኃላፊነቱ የእርሱ ነው። ደጋፊው ይህን በሚገባ ያውቃል ጣልቃም ገብቶ አያውቅም። አንዳንዴ ውጤት ሲጠፋ ታውቃለህ አንድ ተጫዋች በተደጋጋሚ ኳስ ሲያበላሽ ይውጣ ይቀየር ሲል ልትሰማ ትችላለህ። ይህ ስሜት ነው። ግን ጣልቃ ገብነት የለም። እንኳስን ደጋፊው የክለቡ አመራር እና ቦርዱ በምንም አይነት ጣልቃ አይገቡም። የቡድኑ ሙሉ ኃላፊነት የአሰልጣኙ ነው። ዘርዓይ ሙሉ ደግሞ በጣም የምንተማመንበት ትልቅ አሰልጣኝ ነው። ተጫዋች ሲቀይርም ሆነ ሲያስቀምጥ በራሱ ምክንያት እንደሆነ እናውቃለን። ደጋፊ ማኅበሩ ለተጫዋቾቻችን ሳይቀር የዓመቱ መጨረሻ ላይ ግብዣ አድርገን ላደረጉት መልካም ነገር አመስግነን እንዲሁም የዓመቱ ኮከብ ተጫዋች በመምረጥ ማበረታቻ ሽልማት እናዘጋጃለን። ይህ ደግሞ እኛን ለየት የሚያደርገን ነገር ነው።

ወደ አንተ የግል ጥያቄ ልምጣ ሲዳማ ቡናን በመደገፍ ሒደት የተለየ ገጠመኝ አለህ ?

ከልጅነቴ ጀምሮ እግርኳስን በመጫወት ነው ያሳለፍኩት። በፕሪምየር ሊግ ደረጃ ገብቼ ባልጫወትም መቐለ ዩኒቨርሲቲ በነበረኩበትም ወቅት እጫወት ነበር። እንዲሁም የዞን፣ የክልል ሻምፒዮናዎች ላይ እጫወት ስለነበረ የስፖርት ፍቅር በውስጤ ነበር። ሲዳማ የአካባቢዬ ቡድን በመሆኑ ፕሪምየር ሊግ ሳይገባ በፊት የማየት ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበረኝ መከታተል ጀምሬያለው። በተለይ ግን ሲዳማ ውስጤ የገባው እና አሁንም ከውስጤ የማይወጣው 2002 ወደ አዲስ አበባ ተጉዘን ደደቢትን አሸንፈን ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ነው።

የሲዳማ ቡና ደጋፊ ሆነህ ያዘንክበት አጋጣሚ?

በ2011 አዲስ አበባ ላይ ከሜዳ ውጭ የመጨረሻ ጨዋታችንን ለማድረግ ላለመውረድ ከሚጫወተው መከላከያ ጋር አድርገን 4-1 የተሸነፍንበት ጨዋታ በጣም ያዘንኩበት ነው። ያን ጨዋታ ብናሸንፍ ወይም አቻ ብንወጣ ኖሮ የሊጉ ዋንጫን እናነሳ ነበር። መከላከያን እናሸንፈዋለን ብለን በጣም እርግጠኞች ነበርን። ይህን ጨዋታ ካሸነፍን ደግሞ የመጨረሻው ጨዋታችን በሜዳችን ስለነበረ እንደምናሸንፍ እርግጠኛ ሆነን ነበር። በርካታ ደጋፊ ጨዋታውን ለመከታተል አዲስ አበባ ስታዲየም ገብቶ ነበር። ሆኖም ባልጠበቅነው ሁኔታ በሰፊ ጎል ተሸነፍን፤ በጣም አዘንኩ። የሚፀፅተኝ ደግሞ ሲዳማ በኃላ ላዬ በአንድ ነጥብ ማጣት ምክንያት ዋንጫ ማጣቱ ነው።

ሲዳማ ይርጋለም ይጫወት በነበረበት ወቅት ከህፃን እስከ አዋቂ ሲዳማን ለመመልከት የነበረው ጉጉት ታዳጊዎች ኳስ ተጫዋቾች እንዲሆኑ የሚያነቃቃ ነበር። ሲዳማ ጨዋታ የሚያደርግበትን ሜዳ ወደ ሀዋሳ አምጥቶ መቀየሩ ያንን ድባብ አላጣውም ትላለህ ?

በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው። ይርጋለም በቆየበት ጊዜ ያልከው ፍቅር ነበር። ሲዳማን ለመመለክት የነበረው ድባብ እንዳልከው ደስ የሚል ነበር። አብዛኛው ደጋፊ ከይርጋለም ብቻ ሳይሆን ከአለታ ወንዶ፣ ከሀዋሳ ከተለያዩ አካባቢዎች ነው ተጉዞ በመምጣት ይደግፍ የነበረው። ጨዋታው ወደ ሀዋሳ የመጣበት ምክንያት ወደ ይርጋለም ይጓዝ የነበረውን ደጋፊ ለማስቀረት እና በሀዋሳ ያለውን በርካታ ደጋፊ ለመጠቀም ነው። አይተህ ከሆነ ሲዳማ ሀዋሳ ላይ ሲጫወት ከይርጋለም በእጥፍ እጅግ በርካታ ደጋፊ እየተከታተለ ነው። ሌላው የሀዋሳ ሜዳ አመቺ መሆኑ እና ሜዳው ለደጋፊው በቅርብ ርቀት መሆኑ የበለጠ ተመራጭ አድርጎታል። ለፀጥታም ቁጥጥር የተሻለ ስለሆነ በዚህ ምክንያት ነው ወደ ሀዋሳ የዞረው። መጀመርያም ቢሆን ይርጋለም የሆነው ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ህዝቡ ታዳጊዎች እንዲነቃቁ ለማድረግ በማሰብ ነው። ይህ ሀሳብ ወደ ሀዋሳም ሲመጣ እጥፍ ነው የሆነው።

የኔ ዋና የጥያቄዬ ትኩረት ሜዳው መቀየሩ ሳይሆን በአካባቢው ያሉ ጨዋታን በመከታተል ያገኙትን የነበረው መነሳሳት አያጡም ወይ? ይህን እንዳያጡስ አልፎ አልፎ ጨዋታ የሚከታተሉበትን መንገድ እንዲፈጠር እንደ ደጋፊ ማኅበር ምን ታስባላችሁ ለማለት ነው ?

ይሄ ትክክለኛ ጥያቄ ነው። አንድ የታቀደ ነገር አለ። ስምንት ከተሞች ላይ እንደ ሀለታ ወንዶ፣ ቤንሳ፣ ይርጋለም ሌሎችም ላይ ፕሮጀክቶች ለመክፈት እንቅስቃሴ ላይ ነን። ይህ አንደኛው ለጥያቄህ መልስ ነው። ሌላው ተስፋ ቡድኑ ይርጋለም ላይ እንዲጫወት ተደርጓል። እንዲሁም የሲዳማ ክልል ዓመታዊ የከተሞች ውድድሮች ይርጋለም ላይ እንዲደረጉ ተደርጓል። ይህ ለእግርኳስ ፍቅር ያላቸው ታዳጊዎች ጨዋታዎችን እንዲከታተሉ የተመቻቹ እድሎች ናቸው።

በቀጣይ የሚለወጥ ነገር ከሌለ ጨዋታዎች በዝግ እንደሚሆኑ ተግልጿል። ክለቡ ከደጋፊ የሚያገኘውን ገቢ እንዳያጣ ምን ታስባላችሁ?

ትክክለኛ ጥያቄ ነው። በርግጥ ብዙ ገቢ ነው የምናጣው። ባይገርምህ ዘንድሮ የአርቴፊሻል ሜዳው ተመልካች የመያዝ አቅሙ አነስተኛ በመሆኑ በትልቁ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ጨዋታ ለማድረግ አቅደን ነበር። ሆኖም ጨዋታዎች በዝግ በመሆናቸው ገቢ ሊያጣ ይችላል። እኛ እያሰብ ያለነው ከመዋጮ፣ ከስፖንሰር፣ ከባለ ሀብቶችን በማነሳሳት ክለባችንን ለማገዝ ነው።

በመጨረሻ መልዕክት ካለህ?

የሲዳማ ቡና ደጋፊን በጣም ነው የምንወዳቸው የምናከብራቸው። እንግዲህ ዘንድሮ ጨዋታዎች በዝግ ቢሆኑም ባሉበት ሆነው የደጋፊነት ስሜቱ ሳይጠፋ በሚተላለፉ የመገናኛ ብዙኃኖች በመከታተል ድጋፋቸውን እንዲሰጡ ጥሪዬን አቀርባለሁ። ኮሮና ጠፍቶ ሁላችንም ውበታችንን ፍቅራችን ጠብቀን በአንድ ላይ ገብተን ክለባችንን እስክንደግፍ ድረስ በናፍቆት ነው የምንጠብቃችሁ። ራሳቹሁን ከኮሮና ቫይረሰ ጠብቁ መልዕክታችን ነው።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!