የሰማንያዎቹ | የሁለገቡ ዮሴፍ ሰለሞን (ለጉዴ) የእግርኳስ ህይወት

ለሁለቱም የሸገር ቡድኖች ተጫውቷል። ለየትኛውም አጨዋወት የሚሆን፣ በትኛውም ቦታ ላይ ቢሰለፍ ኃላፊነቱን በብቃት የሚወጣ በሰማንያዎቹ ውስጥ ከተመለከትናቸው እጅግ ምርጥ ከሚባሉት የመስመር ተከላካዮች አንዱ የሆነው አመለሸጋው ኮከብ ተጫዋች ዮሴፍ ሰለሞን (ለጉዴ) ማነው?

የአዳማ እግርኳስ ሲነሳ የዚህን ድንቅ ሰው ስም አለማንሳት አይቻልም። ከብዙ ጠንካራ ሰዎች ጀርባ ይህ መልካም ሰው አለ። የቀድሞ ባለግራ እግሩ ድንቅ ተጨዋች ተድላ በላቸው በአዳማ አስራ ሁለት ቀበሌ በሚገኝ ሜዳ ታዳጊዎችን ሰብስቦ ያሰለጥን ነበር። ከሁሉም ታዳጊዎች ጉራማይሌ የሆነ አስቸጋሪ ባህሪ የነበረው አመፀኛ አንድ ልጅ ነበር። በሆነው ባልሆነው ለፀብ የሚጋበዝ ፣ የሚደባደብ ፣ ፀብ ባለበት ቦታ ሁሉ የማይጠፋ ፣ እንኳን ሰው ይቅርና ፊቱ የጦር መሳርያ ቆሞ የማይፈራ ደፋር ነው። ሲያሻው ጠፍቶ ሲፈለግ ዛፍ ላይ ወጥቶ ብቻውን ተቀምጦ የሚደበቅ በፍፁም አስቸጋሪ የሆነ ልጅ ነበር። በዚህ የተነሳ የአካባቢው ሰው አንተ ምን ይሻልሀል ለጉድ የተፈጠርክ (ለጉዴ) የሚል ቅፅል ስም እስከ ማውጣት ደርሰዋል። ታዲያ ቤተሰቦቹ ሂድ ብለው ሁልጊዜ ተድላ ጋር ይልኩት ነበር። ተድላም ይህን ልጅ ተቀብሎ አስቸጋሪ ፀባዩን ተቋቁሞ ሲያጠፋም እየቀጣ ገርቶ አሳድጎታል። ዕድሜው ከፍ እያለ ሲመጣ በአዕምሮው እየበሰለ እና እየተረጋጋ ሲመጣ አስቀድሞ ትኩረት ወደማይሰጠው በውስጡ ያመቀውን የእግርኳስ ችሎታ ወደ ማውጣት ትኩረቱ አደረገ። ምስጋና ለተድላ በላቸው ይግባና ያ አመፀኛ የሆነው ብላቴና በኢትዮጵያ እግርኳስ አንቱታን ያተረፈ ድንቅ ተጫዋች መሆን ችሏል። የዛሬው የሰማንያዎቹ ኮከብ እንግዳችን ዮሴፍ ሰለሞን ይባላል።

ዮሴፍ የተወለው አዲስ አበባ ኳስ ሜዳ አካባቢ ቢሆንም ዕድገቱ ናዝሬት ከተማ አስራ አምስት ቀበሌ ነው። የእግርኳስ ህይወቱን በክለብ ደረጃ እዛው አዳማ ለሚገኘው ትግል ፍሬ ለሚባል ቡድን ሁለት ዓመት በመጫወት አሳልፏል። በኋላም በመቀጠል ሰባት ልጆችን ይዞ ተድላ በላቸው ወደ አዲስ አበባ ለሙከራ የአሰልጣኝ አስራት ኃይሌ ቡድን ለነበረው ጉሙሩክ (ፊናስ) ይዟቸው ይመጣል። ስድስቱ ለጊዜው አስራት ኃይሌን አሳምነው ሲያልፉ በልጅነቱ አመፀኛ የነበረው ዮሴፍ ሰለሞን ሙከራውን ሳያልፍ ይወድቃል። በነገራችን ላይ ካለፉት ስድስት ተጫዋቾች መካከል የወቅቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ይገኝበታል። ይህ የአስራት ኃይሌ ውሳኔ ያልተዋጠለት ተድላ በላቸው ለቀድሞ ድንቅ ተጫዋች ኃይሌ ካሴ ስልክ ይደውላል። ” አስራት ኃይሌ ከመረጣቸው ስድስት ልጆች ይልቅ የቀነሰው አንዱ ልጅ የተሻለ ነው። ስድስቱን ጥሎ እርሱን ቢይዝ ይሻላል ስለዚህ በድጋሚ የሙከራ ዕድል እንዲሰጠው ይህን ለአስራት ንገረው።” ይለዋል። ኃይሌ ካሴም ለአስራት ነግሮት ዮሴፍ በድጋሚ የሙከራ ዕድሉን ያገኛል። አስራትም በድጋሚ ሲያየው በችሎታው ተገርሞ “ይህን የመሰለ ልጅ ተሳስቼ አምልጦኝ ነበር”። በማለት በ1984 ለሁለት ዓመት ለጉሙሩክ እንዲጫወት ሆኗል።

በሁሉም አሰልጣኞችና ተመልካቾችም እጅጉን ይወደድ የነበረው ኳሰኛው፣ ሁሉን ያሟላው ምርጡ ተጨዋች ዮሴፍ ሰለሞን በመቀጠል በሁለት አሰልጣኞች ትኩረት ውስጥ ይገባና አስቀድሞ በማስተር ቴክኒሻን ሀጎስ ደስታ ቡድን ለነበረው ኢትዮጵያ መንድ ለመጫወት ተስማምቶ ለቅድመ ውድድር ዝግጅት ወንጂ በነበረበት ወቅት አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ በ1986 ጊዮርጊስን ለማሰልጠን ሲረከብ የሴፍን ደውሎለት በተሻለ የገንዘብ ጥቅም ቅዱስ ጊዮርጊስን እንዲቀላቀል አድርጎታል። በአራት ዓመት የፈረሰኞቹ ቤት ቆይታው በክለቡ ከተሰሩ ታሪኮች አንዱ የሆነውን ከ1986–88 ድረስ ለተከታታይ ሦስት ዓመት በሀገሪቱ አሉ የሚባሉ ዋንጫዎችን ጠራርጎ በወሰደበት ዘመን የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች መሆኑን አሳይቷል።

የያኔው አመፀኛ ብላቴና የዛሬ ኮከብ ተጫዋች የሆነውን የሴፍ ሰለሞንን ከፈጠረው ባለውለታው ተድላ በላቸው ጋር ቆይታ አደረግን። ዮሴፍን ዛሬ ላይ ሆኖ ሲያየው ምን እንደሚሰማው ጠየቅነው እርሱም እንዲህ ብሎናል ” እውነት ነው የምነግርህ ዮሴፍን በልጅነቱ እግርኳስን እንዲጫወት እስኪሰለቸኝ ድረስ እየገረፍኩ ሳሳድገው አንድ ቀን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንደሚጫወት እርግጠኛ ሆኜ ነበር። ዮሴፍ በልጅነቱ ፀብ የማይፈራ ፣ የማያስደነግጠው በጣም አስቸጋሪ ልበ ሙሉ ጀግና ልጅ ነበር። በእግርኳስ ህይወቱም ትልቅ አቅም ነበረው።አፌን ሞልቼ የምናገረው አሁን ላይ የተሻሉ ከምትላቸው ተጫዋቾች ዮሴፍ በዚህ ዘመን ቢኖር ኖሮ ይበልጣቸው ነበር። ጎበዝ በግራም በቀኝም እግሩ የሚጫወት በተፈጥሮ እግሩ ይሄነው የማትለው፣ አማካይ ሆኖም መጫወት የሚችል ፣ ኳስን የመረዳት አቅሙ እና አዕምሮው ከፍተኛ የሆነ ከሜዳም ውጪ በጣም ዘናጭ የሆነ ልጅ ነው።” ይለዋል።

ዮሴፍ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ጣፋጭ አራት ዓመታትን ቆይታ ካደረገ በኃላ ልቡ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ሸፍቶ በ1990 ቡናማዎቹን ተቀላቅሏል። ሆኖም ሁሉም ነገር እንዳሰበው ሳይሆን በኢትዮጵያ ቡና በመጀመርያው ጨዋታ ከቀድሞ ክለቡ ጊዮርጊስ ጋር በነበረው ጨዋታ ከፍተኛ የሆነ የጉልበት ጉዳት አስተናግዶ ለሁለት ዓመት ከእግርኳስ እንዲገለል ሆኗል። በዚህም በእግርኳስ ህይወቱ ፈተኙን ጊዜ አሳልፏል። በግብፅ ሀገር የቀዶ ጥገና በማድረግ ወደ እግርኳሱ ለመመመስ ጥረት ቢያደርግም በስተመጨረሻ እንደተወደደ ሳይጠገብ ባለቤቱ ወደ አለችበት ሀገር ኑሮውን ሊያደርግ ወደ አየርላንድ ተጉዟል።

በክለብ እና በብሔራዊ ቡድን አብሮት የተጫወተው የቀድሞ ድንቅ ተጫዋች የአሁኑ የባህር ዳር ከተማ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ስለ ዮሴፍ ሰለሞን ይሄን ይናገራል ” ዮሴፍ በጣም ጎበዝ ኳስ የሚችል ተጫዋች ነበር። በብልጠት የሚጫወት ፣ ጠንካራ ፣ በጣም አስጥሎ የሚጫወት ፣ አካባቢዎቹን በደንብ መቆጣጠር የሚችል ፣ ፈጣን አዕምሮ ያለው ከሁሉም በላይ ለመሐል ሜዳ ተጫዋቾች የተመቸ ነው። ከሜዳ ውጪ ባለው ባህሪም ለማንም ተጫዋች ጓደኛ ለመሆን የተመቸ ፣ በጣም ጀንተል ያለ ዘናጭ ፣ ቀልድ ጨዋታ የሚወድ ፣ ስራው ላይ ግን ቀልድ የማያውቅ ተጫዋች ነው።”

ሌላው ወርቃማው ተጫዋች የወቅቱ የመቐለ አሰልጣኝ ገብረመድን ኃይሌ ስለ ዮሴፍ ሰለሞን ሲናገር ” ዮሴፍ ምርጥ ተጫዋች ነበር። ጊዮርጊስን ከተቀላቀልኩ ከሁለት ሦስት ዓመት በኃላ ነው የተቀላቀለን። በሜዳም ከሜዳም ውጪም በጣም ጥሩ ሰው ነው። ሜዳ ላይ ከዕድሜው በላይ የሆነ ጠንካራ ተከላካይ ነበር። እሱ ከተቀላቀለን በኃላ ተከላካይ ክፍላችን ጥሩ ሆኖ ነበር። ከሜዳ ውጪ ደግሞ ጥሩ ባህሪ የነበረው ፣ ግልፅ እና በቀላሉ ተግባቢ ዓይነት ሰው ነበር። እንደ ዕድሜው አይደለም ጠንካራ ነው። ከእኔ ጋርም ጥሩ ቅርርብ ነበረን። ከቤተሰቦቻቸው ርቀው ከሚኖሩ የክፍለ ሃገር ተጫዋቾች ጋር ቅርብ ግንኙነት ነበረኝ። ምክንያቱም እኔም ከቤተሰብ ርቆ የመኖሩን ጣዕም ሰለማውቀው ቀርቤ እመክራቸው እና አበረታታቸው ነበር። የባይተዋርነት ስሜን እንዳይሰማቸው የተቻለኝን አደርግ ነበር። የጆሲም ቅርርብ ከዛ ነው የጀመረው። በጊዮርጊስ ጥሩ ቆይታ ነበረን። ፎቶዋንም አስታውሳለው ከድል በኃላ የተነሳናት ፎቶ ናት።” በማለት ይናገራል።

ብሔራዊ ቡድን ከታዳጊ እስከ ዋናው ቡድን መጫወት የቻለው የሴፍ ሰለሞን ከሀገሩ ከወጣ ከረጅም ዓመት በኃላ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ሚዲያ ብቅ ብሎ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ጥሩ ቆይታ አድርጓል።

“በመጀመርያ ከረጅም ጊዜ በኋላ ፈልጋችሁኝ በማግኘት ኘከምወደው የሀገሬ ህዝብ ጋር ስላገናኛችሁኝ እናተን በቅድሚያ አመሰግናለው። ከሀገሬ ከወጣው ረጅም ዓመት ሆኖኛል። ሁሌም ወደ ኋላ ሳስብ በእግርኳስ ህይወቴ በጣም ደስተኛ ነኝ። በሁለቱ ትልልቅ ክለቦች መጫወቴም ኩራት ይሰማኛል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ከገባሁበት ዓመት ጀምሮ ለተከታታይ ሦስት ዓመት በሀገሪቱ የሚገኙትን ዋንጫዎች በሙሉ ጠራርገን ነው የወሰድነው። ይህ ለኔ ትልቅ ስኬት ነው። በብሔራዊ ቡድን ከታዳጊ እስከ ዋናው ቡድን ድረስ የመጀመርያ ተመራጭ ሆኜ ተጫውቻለው፣ ኢትዮጵያ ቡናም ከምፈልገው አጨዋወት አንፃር ሄጄ ሌላ ታሪክ ለመስራት ባስብም ጉዳት አጋጥሞኝ የማስበውን መሆን አልቻልኩም እንጂ ቡና የነበረኝ ቆይታ አሪፍ ነበር።

“በእግርኳስ ህይወቴ የምቆጨው ብዙ ነገር ባይኖርም ከሀገር ውጪ ተጫዋችነትን ባለማሳካቴ እስካሁን በጣም ይቆጨኛል። አውሮፓ በቅርበት ጨዋታዎችን ስታይ ውጪ የመጫወት አቅሙ እንዳለኝ አስቤ እቆጭ ነበር። ሌላው ጊዮርጊስ እያለው አንድ አምስት ልጆች እኔ ተስፋዬ ኡርጌቾ ነፍሱን ይማረው ፣ ፍስሀ በጋሻው፣ ገዛኸኝ እና ደሳለኝ ገብረጊዮርጊስ ግብፅ ክለብ ለመጫወት የሁለት ዓመት ለሁላችንም ሃምሳ ሺህ ዶላር ፈርመን ሁሉ ነገር አልቆ ፓስፖርት ልከን በምን መልኩ እንደተኮላሽ እስካሁን አላውቅም ብቻ ፈጣሪ ይወቀው ፤ ይህ በጣም ይቆጨኛል።

“በሁለቱ የሸገር ቡድኖች መጫወቴ ይሄ ለኔ ታሪኬ ነው። የታሪክ ትንሽ የለውም በህይወቴ በሁለቱ ክለብ በመጫወቴ የሚሰማኝን ደስታ ልነግርህ አልችልም። በጣም ነው ደስታ የሚሰማኝ ትልቁ ታሪኬ ነው። ቤቴ ብትመጣ ባለቤቴ በሁለቱ ክለብ በብሔራዊ ቡድን ስጫወት የተነሳሁትን ፎቶ በፍሬም አሰርታ ቤቴ ስትገባ የመጀመርያ የምታየው እርሱን ነው። በጣም ነው ደስታ የሚሰማኝ። ሁሌም ወደ ኃላ ሳስበው በጊዮርጊስ እና በቡና በመጫወቴ ደስ ይለኛል። በአጠቃለይ የእግርኳሰ ህይወቴ በጣም ደስተኛ ብሆንም በሁለቱ ክለቦች ተጫውቼ በማለፌ ይበልጥ ደስተኛ ነኝ። ለልጆቼ ስለ እግርኳስ ህይወቴ ታሪክ ስነግራቸው በሁለቱ ክለቦች የነበረኝን ቆይታ ነው የምነግራቸው። ይገርምሀል አሁንም ድረስ ምን አለ ወደ ኃላ ተመልሼ አሁን ያለኝን ከፍ ያለ አመለካከት ይዤ ለምን አልጫወትም እላለው።

“ቅዱስ ጊዮርጊስን ለቅቄ ቡና የሄድኩበት ምክንያት ብዙ ሰው ማወቅ ይፈልጋል። እንግዲህ አሁን ላይ ሆኜ ሳስበው የዛን ጊዜ የነበረኝ አስተሳሰብ እና አሁን ያለኝ አመለካከት ይለያያል። በጊዜው በነበሩ ሚዲያዎች ምክንያቴን ገልጬ ለሚወደኝ ደጋፊ የለቀኩበትን ምክንያት ቁጭ ብዬ አለማስረዳቴ እስካሁን ይቆጨኛል። ግን አወጣጤ ዋናው ምክንያት በትላልቅ ደረጃ ለመጫወት ከነበረኝ ፍላጎት የተነሳ ፣ ቡና በአፍሪካ ክለቦች ውድድር ዕድገት እያሳየ በመምጣቱ እና ጥሩ እግርኳስ እየተጫወተ ውጤት እያመጣ ስለነበረ ነው ፤ የኔ የውስጥ ፍላጎት አጨዋወት ነው። እኔ ወደ ቡና እንድሄድ ያደረገኝ አጨዋወቱ እንጂ በዋንጫ ስኬት በፈይናስ አቅም የጊዮርጊስ የተሻለ ነው። ግን የውስጥ ፍላጎቴና መጫወት የምፈልገው አጨዋወት ቡና በመኖሩ ነው የሄድኩት። ይህን ስል ግን ጊዮርጊስ ቤት ኳስ አንጫወትም የሚችሉ ልጆች የሉም ማለቴ አይደለም። በጣም ጎበዝ የኳስ ሊቆች ጊዮርጊስ ነበሩ። ሆኖም ምርጫዬን ቡና ባደርግም አልተሳካም። በገባው በመጀመርያ ጨዋታዬ አርባ አምስት ደቂቃ ነው የተጫወትኩት ጉልበቴን ተጎዳው ፤ለሁለት ዓመት ከሜዳ ተገልዬ ቆየሁ።

” የማታ ጨዋታ እና ዝናብም ነበር። ሜዳውም ጭቃ ሆኗል። አንድ ኳስ ከአሸናፊ ሲሳይ ጋር ሄደን ተጋጭቼ ነው የተጎዳሁት ለረጅም ጊዜ አሸናፊ ሆን ብላ ነው የጎዳችህ ይሉ ነበር። እስካሁንም እንደዚህ የሚያስብ አለ ፤ ብዙ ጊዜ ለማስረዳት ሞክሬአለው። ሁለታችንም ለጋራ ኳስ ነው የሄድነው ፤ አጋጣሚ የሆነ ነው። አሸናፊ ሆን ብላ ያደረገችው የሚባለው ነገር ትክክል አይደለም። አሸናፊ በባህሪው ተጨዋች ለመጉዳት ሆን ብሎ የሚያደርግ ተጫዋች አይደለም። እንግዲህ በደረሰብኝ የጉልበት ጉዳት ለሁለት ዓመት ከሜዳ እንድርቅ አድርጎኛል። ከዚህ በኃላ አንድ የቡና ደጋፊ ፑፒ የሚባል በራሱ ተነሳሽነት ‘የሆነ ፕሮግራም አዘጋጅቼ ለህክምናህ ወደ ውጪ ሄደህ ትታከማለህ ‘ ብሎ የሆነ ፕሮግራም አዘጋጅቶ ገንዘብ አሰባሰበ ፤ በዚህ አጋጣሚ አመሰግነዋለው። አብርሀም መብራቱም የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ፌዴሬሽን ሄዶ ሜዳ እንዲፈቀድልኝ እንዲሁም ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ነፃ የአውሮፕላን ትኬት አስጨርሶልኛል ፤ እሱንም ከልብ አመሰግናለው። የማነህ የሚባል የቡና ደጋፊ በግሉ ረድቶኝ እኔም የራሴ ያስቀመጥኩት ብር ነበር ግብፅ ሄጄ ሰርጀሪ ተሰራው። በሆቴል በነበረኝ ቆይታ አበራ ቃጫ የሚባል በወጣት ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች የነበረ ሆቴል አታርፍም ብሎ ቤቱ አቆይቶኛል። በአጠቃለይ ብዙዎች መልካም ፍቃዳቸውን ስላሳዩኝ በዚህ አጋጣሚ አመሰግናለው።

“እኔ በተፈጥሮዬ አንድ ነገር ከሆነ በኋላ ለማይመለስ ነገር ብዙም ማሰብ አልፈልግም። ተመልሼ የምቆጭበት የማስበው ነገር የለም። በጣም ነገሮችን በትዕግስት በተረጋጋ ሁኔታ የማየት ዕድል ያለኝ ሰው ነኝ። በጉዳቱ ምንም ጥያቄ የለውም ብዙ መጫወት የምችልበትን ዕድል ነው ያጣሁት። ያው ይህ አልፏል ብዙም የማስበው ጉዳይ አይደለም።

“ገጠመኝ በብሔራዊ ቡድንም በክለብም ነበረኝ። ከክለብ ስጀምር በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ከግብፁ አል አህሊ ጋር አዲስ አበባ ላይ ስንጫወት የአል አህሊው ተጫዋች በቀይ ሲወጣ እኔንም በቀይ ይዞኝ ሲወጣ በወቅቱ አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ እንዴት እንደተበሳጨ እንደተቆጣ አጠይቀኝ። ይህን ጨዋታ አሸንፈን ባናልፍ ኖሮ አስራት ቁርጥምጥም እንደሚያደርገኝ እርግጠኛ ነበርኩ። መጨረሻ ጌትነት ሞት ባይኖር ባስቆጠረው ጎል አሸንፈን የወጣንበት አጋጣሚ አልረሳውም። በብሔራዊ ቡድን ለሴካፋ ዋንጫ ዩጋንዳ ሄደን እንዳሳለፍኩት ጊዜ በእግርኳስ ህይወቴ በጣም ስቄ ተዝናንቼ የመጣሁበት ጊዜ የለም። በጊዜው እኛን በመወከል የእንግሊዘኛ ቋንቋ አስተርጓሚ የነበሩት አሸናፊ በጋሻው እና ብሩክ እስጢፋኖስ (ካንቶና) ነበሩ። አሁን ሳስታውሰው ምን ዓይነት እንግሊዘኛ ቋንቋ ቢያወሩ ነው እንዲህ የተግባቡት እያልኩ ያስቀኛል። በጣም ብዙ አስቂኝ ትዝታ ነበር።

“ለጉዴ የሚለውን ስም ያወጣልኝ የተድላ በላቸው ጓደኛ ነው። በልጅነቴ በጣም አመፀኛ ስለሆንኩ በዚህ ምክንያት ለጉድ የተፈጠርክ ለጉዴ እየተባልኩ መጠራት ጀምሬአለው። በዚህ አጋጣሚ ለእኔ እግርኳስ መነሻ የሆነኝ እንደወንድም አባት የማየው ተድላ በላቸውን ማመስገን እፈልጋለው እርሱ በኔ እግርኳስ ህይወት ትልቅ ቦታ ያለው የማከብረው ሰው ነው።

“ከሀገሬ ከወጣው አስራ ዘጠኝ ዓመት ሆኖኛል። ወደ አየርላንድ ብዙ ስፖርተኛ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያውያን የሉም። የኔ አጋጣሚ ሆኖ አስቀድማ የቀድሞ ጓደኛዬ የአሁኗ የትዳር አጋሬ ቤተሳይዳ ለሥራ አየርላአንድ መጥታ ስለነበረ ከሰባት ወር በኃላ እኔን ወስዳኛለች። በጊዜውም እኔ እርሷን አጥቼ ስለነበር ሄድኩኝ። አሁን ሦስት ልጅ ወልደን እየኖርን እንገኛለን። የመጀመርያዋ ሴት ልጄ ኤፍራታ 18 ዓመቷ ነው። ሁለተኛ ልጄ ቢታንያ 13 ዓመት ሆኗቷል። ትንሹ ወንዱ ልጄ ናሆም ስድስት ዓመት ሆኖታል።

“ከሀገሬ ከወጣው በኃላ የኢትዮጵያ እግርኳስን እየተከታተልኩ አይደለም ። ምክንያቱም ያለሁበት ሀገር ብዙ ሀበሻ የለም። በዚህ ምክንያት ብዙም መረጃው የለኝም ግንኙነቱ ስለሌለ መከታተል አልቻልኩም። ሌላ የስራ ሁኔታ የቤተሰብ ኃላፊነት ስላለብኝ አብዛኛውን ጊዜ ትኩረቴ እዛ ላይ በመሆኑ የሀገሬን እግርኳስ የመከታተሉ ዕድሉ የለኝም። ይሄም ቢሆን የኢትዮጵያ እግርኳስ ሁሌም በልቤ የሚኖር ነው።

” አየርላንድ እንደመጣሁ ለሁለት ዓመት ተጫውቻለው። የምጫወተውም በአጥቂነት ነበር። በኃላ የመጀመርያ ልጄ ስትወለድ በዚህ ሀገር ልጅ በጋራ ነው እና የምታሳድገው ምንም እግርኳሱን የምቀጥልበት ጊዜ አጠቼ አቁሜዋለው። ይህም ቢሆን በግሌ በጂም የተለያዩ ልምምዶችን እሰራለው። አሁን ደግሞ ወደ አሰልጣኝነቱ በመጨረሻው ልጄ ምክንያት እየገባው ነው። እርሱ እግርኳስን ስለሚወድ በእኛ አካባቢ አንድ የእግርኳስ አካዳሚ አለ በሳምንት አንዴ ቅዳሜ እየሄድኩኝ ተሳትፎ ማድረግ ጀምሬያለው።

“በመጨረሻም በክለብ እና በብሔራዊ ቡድን አብረውኝ ለተጫወቱት ሁሉ ፣ ለባለቤቴ እና ለልጆቼ ፣ ለተድላ በላቸው እና ለቤተሰቦቼ በጠቅላላ ያለኝን አክብሮት እና ምስጋና በዚህ አጋጣሚ መግለፅ እፈልጋለው።”

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!