አሰልጣኝ ዘነበ ፍስሀ የት ይገኛል?

በተለያዩ ምክንያቶች ከእግርኳስ የራቁ ግለሰቦች የምናቀርብበት የት ይገኛሉ አምዳችን ባለፈው ሳምንት የወጣቱ አሰልጣኝ ምንተስኖት ጌጡ ወቅታዊ ሁኔታ ማቅረባችን ይታወሳል። ለዛሬ ደግሞ የወላይታ ድቻ አሰልጣኝ የነበረው ዘነበ ፍስሀን ይዘንላችሁ ቀርበናል።

በ2009 የውድድር ዓመት አጋማሽ ለረጅም ጊዜ ቡድኑን የመራው መሳይ ተፈሪን ተክቶ የድቻ አሰልጣኝ የሆነው ዘነበ ቡድኑ በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ ዛማሌክን ጥለው ወደ ሁለተኛው ዙር እንዲያልፉ በመርዳት ድንቅ ጊዜ ያሳለፈ ሲሆን ከሊጉ ላለመውረድ ሲጫወት የነበረውን ቡድንም ከመውረድ አትርፎታል። ሆኖም በቀጣዩ የ2010 የውድድር ዓመት የተጠበቀውን ያህል ውጤታማ አለመሆኑን ተከትሎ ከወላይታ ድቻ ጋር በስምምነት ከተለያየ በኃላ ከአሰልጣኝነት ርቆ የሚገኘው ይህ አሰልጣኝ በወቅታዊ ሁኔታው ዙርያ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረገውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበንላችኃል።

አሁን የሚገኝበት ሁኔታ

አሁን ራሴን በማሻሻል ላይ ብሆንም ከወላይታ ድቻ ከተለያየሁ በኃላ ክለቦች ማግኘት አልቻልኩም። መንገዱን በደምብ ስለማላውቀው እስካሁን ድረስ ወደ ክለብ እግርኳስ መመለስ አልቻልኩም። ለጊዜው ግን በማንበብ እና በመማር ጊዜዬን እያሳለፍኩ ነው።

የሥራ ሁኔታ

ምንም ስራ እየሰራሁ አይደለም። አሁን ራሴን ማሻሻል ላይ ነው ትኩረቴ። በቅርቡ የአቅም ማሳደጊያ ስልጠናዎች እየተጠባበቅኩ ነው። ትምህርትም በቅርቡ እጀምራለው።

ከአሰልጣኝነት የራቀበት ምክንያት

በኢትዮጵያ እግርኳስ ከአቅም በላይ ልምድ ነው እንደ ትልቅ መስፈርት የሚታየው። እኔ ደግሞ ጀመሪ አሰልጣኝ ነው የምመስላቸው። ሆኖም ከ1996 ጀምሮ ለፕሮጀክት አሰልጣኝነት ጀምሬ ለረጅም ጊዜ አሰልጥኛለው። የክልል ምርጥ ቡድኖች ለሦስት ግዜ ያክል አሰልጥኛለው ፣ በፕሮጀክት ደረጃ በርካታ ስኬቶች አሉኝ። ስልጠና በታዳጊ ደረጃ ብጀምርም አቅሙ አለኝ። ወላይታ ድቻን የለቀቅኩበት ምክንያት ጫና በዝተውብኝ ነው። ክለቦች ስትይዝ ከፍተኛ ሊግ ስትሆን ወደ ፕሪምየር ሊግ አሳድግልን፤ ፕሪምየር ሊግ ከሆንክ ደግሞ ዋንጫ አምጣልን ነው የሚሉህ። ይሄ ደግሞ በአንዴ የሚሆን አይደለም፤ እግርኳስ ሂደት ነው። ወጣት አሰልጣኝ ስትሆን ደግሞ ጫናዎች ይበዙብሃል።

በወላይታ ድቻ ቆይታዬም ጫናዎች ሲበዙብኝ ነው በራሴ ፍቃድ የለቀቅኩት። የሰራሁት ሥራም እንደ ውለታ ሳይቆጠር ሲቀር ትንሽ ቅሬታ ይፈጥራል። ሌላው ደግሞ ከወላይታ ድቻ ከተለያየው በኃላ መንገዱን ብዙም አላወቅኩትም። እሱም ከአሰልጣኝነት የመራቄ ሌላው ምክንያት ነው።

ወደ አሰልጣኝነት ለመመለስ… ?

እኔ ወደ ሥራ ለመመለስ ዝግጁ ነኝ፤ እየጠበቅኩም ነው። ከማንም ክለብ በጋራ ለመሥራት ዝግጁ ነኝ፤ አቅሙም አለኝ። ዋናው ነገር እምነት አሳድሮና ከነፃነት ጋር ኃላፊነት የሚሰጥህ ማግኘት ነው።

በመጨረሻ…

ብዙ ሰዎች ማመስገን እፈልጋለው። ከአሰልጣኝነት ከራቅኩ በኃላ ነገ የተሻለ ቀን ይመጣል ብለው ላበረታቱኝ ከጎኔ ለሆኑ ለሀዋሳ ጤና ቡድን እና ከጎኔ ለሆኑ በሙሉ አመሰግናለሁ። በቅርበት ግን ለአካሉ ካሳ፣ ወንድሜ ልደቱ ፍስሀ፣ ታደሰ ከበደ፣ ምንውየለት ለማ እና ከሊፋን ማመስገን እፈልጋለሁ።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!