የደጋፊዎች ገፅ | ቆይታ ከድሬዳዋ ከተማ ደጋፊዎች ማኀበር ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ጀማል ጋር

👉 “የድሬ ህዝብ ክለቡን ሊደግፍ ወደ ሜዳ ገብቶ የተሻለ ለተጫወተ ቡድን ሳይቀር ድጋፍ ሰጥቶ የሚወጣ ነው”

👉 “ሌሎች የሚሄዱበትን የተሳሳተ መንገድ እንዲያስተካክሉ ፌዴሬሽኑ ጥብቅ ክትትል ማድረግ፣ መቆጣጠር አለበት”

👉” ተራራ እና ዛፍ ላይ ወጥቶ ጨዋታ የሚመለከት ደጋፊ ነው ያለን”

👉”አሸናፊ፣ ዮርዳኖስ፣ ስምዖን፣ አሕመድ ጁንዲ፣ አሰግድ እና ሌሎቹም ባፈራችው ከተማ አሁን ያን ያህል እያገኘን አለመሆኑ ያሳስባል”

የቡድኑ ውጤት ሚዛን የሚደፋ ባይሆንም በሊጋችን ካሉ እና መልካም ከሚባል የአደጋገፍ ሥርዓታቸው በምሳሌነት ከሚጠቀሰው ድሬዳዋ ከተማ የደጋፊ ማኀበር ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ጀማል ጋር በ”ደጋፊዎች ገፅ” አምዳችን ቆይታ አድርገናል።

በየትኛውም የእግርኳስ ውድድር ወደ ድሬዳዋ ተጉዘው ለመጫወት፣ ለመከታተል እና ቡድናቸውን ለመደገፍ የሚሄዱ በጠቅላላ ስለ ድሬዳዋ ከተማ እንግዳ ተቀባይነት እና ስለደጋፊዎቿ መልካምነት ሳይመሰክሩ አያልፉም ቢባል ማጋነን አይሆንም። ይህ የድሬዳዋ ማኀበረሰብ መልካም መገለጫ የሆነው እንግዳ ተቀባይነት በበተለያዩ መድረኮች በጨዋታ ታዛቢ ኮምሽነሮች እና በዳኞች ሳይቀር ምስክርነት ሲሰጥ የሰማንበት አጋጣሚ አንደነበረም የሚታወስ ነው።

በድሬዳዋ እግርኳስ አፍቃርያን ዘንድ አንድ የሚባል አባባል አለ “ኳሱን ተጫውቶ በልጦ ላሸነፈ ቡድን ደግፍ” የሚል። ይህን አባባል በተግባር ከምንመለከትባቸው የሀገራችን እግርኳስ ከተሞች ድሬዳዋ ቀዳሚውን ትወስዳለች። የቡድኑ ውጤት የቱንም ያህል አስደሳች ባይሆንም የሚመጡ የተቃራኒ ክለብ ደጋፊዎችን በፍቅር ተቀብሎ የሚሸኙት ድሬዳዋ ደጋፊዎችን በመወከል ያለፈውን አንድ ዓመት ማኅበሩን እየመራ ይገኛል። በማኅበሩ ውስጥ እየተፈጠረ ያለውን ለውጥ በቁርጠኝነት እየመራ የሚገኘው ወጣት በዛሬው የደጋፊዎች ገፅ አምዳችን እንግዳ ነው። ሳሙኤል ጀማል ይባላል። የደጋፊ ማኅበሩን አደረጃጀት እና ተያያዥ ጉዳዮች አስመልክቶ ቆይታ አድርገናል። መልካም ንባብ!

በኮሮና ምክንያት ውድድር ባለመኖሩ ድሬዳዋ ከተማን አለማየት ስሜቱ እንዴት ነው?

በጣም ከባድ ነው። እግርኳስን ለሚወደው እና በኳስ ለሚደሰተው የድሬዳዋ ህዝብ ከሜዳ መራቅ አስቸጋሪ ነው። ድሬ ለእግርኳስ ያላት ፍቅር የተለየ ነው። የእነኔም ከዚህ የተለየ አይሆንም። እንደሚታወቀው ለወራት የምንወደውን ክለብ ሳናይ መቆየታችን ከባድ ቢሆንም በዓለም የመጣ ስለሆነ ችግሩ ትቀበለዋለህ። ፈጣሪ ኮሮና የሚባለውን በሽታ ከሀገራችን አጥፍቶ ሁላችንም ተሰባስበን ለማየት ያብቃን ነው የምለው።

ውድድሮች በኮሮና ከተቋረጡ ጀምሮ እንደ ደጋፊ ማኅበር ምን ሥራዎችን ስታከናውኑ ቆያችሁ?

ኮሮና የሰጠን ትልቁ ጠቀሜታ የምለው በጎ ነገሮችን በኅብረት እንድንሰራ ረድቶናል። የድሬዳዋ ህዝብ ለወትሮም ለተቸገረ የሚረዳ፣ አብሮ ተካፍሎ የሚበላ ማኀበረሰብ ያለበት ህዝብ ቢሆንም የበለጠ በዚህ በኮሮና ምክንያት የአቅም ውስንነት ያለባቸውን እንደ ደጋፊ ማኅበር በመንቀሳቀስ የተለያዩ በጎ ተግባሮችን ከተለያዩ ተቋማት እና ከክለቡ ጋር በመሆን በማስተባበር በመሥራት ቆይተናል።

ከኮሮና ውጭ ያለውን ጥያቄዬ ማንሳት ልጀምር። የድሬዳዋ ከተማ ደጋፊ ማኅበር ፕሬዝደንት መቼ ሆንክ? የደጋፊ ማኅበሩ አደረጃጀት ምን እንደሚመስልም ግለፅልኝ?

እኔ ከተመረጥኩ ገና አንድ ዓመት ገደማ ቢቆጠር ነው። አጭር ጊዜ ነው ወደ ኃላፊነቱ ከመጣሁ። የድሬዳዋ ደጋፊ ማኅበር አደረጃጀቱ ከሁሉም የድሬዳዋ ቀበሌ በተወጣጣ ተወካይ አማካኝነት ጠቅላላ ጉዳዔ ይካሄዳል። በመቀጠል የደጋፊ ማኅበሩን የሚመሩ 20 አባላት ይመረጣሉ። ከእነዚህ ሃያ አባላት መካከል ሦስቱ ተለይተው ፕሬዝደንት፣ ም/ ፕሬዝደንት እና ዋና ፀሀፊ ይሆናሉ። የተቀሩት አስራ ሰባቱ የኮሚቴ አባል በመሆን ይሰራሉ ማለት ነው።

የድሬዳዋ ከተማ ደጋፊ ማኅበር በክለቡ የውሳኔ ሰጪ የመጨረሻ አካል፤ ማለትም በቦርድ ውስጥ ድምፅ አለው?

አንድ ድምፅ አለን። ግን እስካሁን አልሰራንበትም። ቅድም እንዳልኩህ ከተመረጥን ገና አንድ ዓመታችን ነው። ከእኛ በፊት የነበሩ የደጋፊ ማኅበር ኃላፊዎች በቦርዱ ውስጥ ተካተው ድምፅ ይሰጡ ነበር። ልክ እኛ ተመርጠን በቦርዱ የሚወከል ሰው ልንልክ ስንል የኮሮና በሽታ መጥቶ ውድድሩ በመቋረጡ በቦርዱ ውስጥ ሳንገባ ቀርተናል።

ስለዚህ በ2013 የክለቡ እቅድ እና እንቅስቃሴ ላይ በቦርዱ ውስጥ ተሳትፎ አልነበራችሁም ማለት ነው ?

ነበርን። በተለያዩ ሥራዎች ውስጥ ተሳትፎ ነበረን። ለምሳሌ በማልያ ህትመት(ዝግጅት)፣ በፊት መሸፈኛ ጭንብል (ማስክ)፣ የተጫዋቾች ዝውውር ግዢ ውስጥ እና የመታሰቢያ ፕሮግራም ላይ በክለቡ ቦርድ ውስጥ ባንገባም ከክለቡ አመራሮች ጋር አብሮ የመስራት የመነጋገር እድሉ ነበረን።

ድሬዳዋን በቅርብ አውቃታለው። በተለያዩ አጋጣሚዎች ለዘገባ መጥቻለሁ። ደጋፊው እግርኳስን የሚወድ እና ጥሩ ለተጫወተ ቡድን አድናቆት የሚቸር የሚሰጥ ደጋፊ ነው። ይህ የድሬዳዋ ደጋፊ መገለጫ የሆነውን የአደጋገፍ መንገድ እንዴት ታየዋለህ ?

እውነት ነው። ስለ ራስ እንዲህ ነው ብሎ መናገር ባንፈልግም። የድሬዳዋ ደጋፊ ጨዋ፣ ሰው አክባሪ ህዝብ ነው። እውነት እንዳልከው ድሬዳዋን ሊደግፍ ማልያውን ለብሶ ገብቶ የተሻለ ለተጫወተ ቡድን ሳይቀር ድጋፍ ሰጥቶ የሚወጣ ነው። እኛ እንደ አንድ ተሞክሮ የምንወስደው የተሻለ ለተንቀሳቀሰ ቡድን ቆሞ የሚያጨበጭብ ደጋፊ መሆኑ ነው። ይህ ደግሞ እኛ ሳንሆን የጨዋታ ዳኞች ሳይቀር የመሰከሩልን ነው። የድሬዳዋ ህዝብ ኳስ ያውቃል። የሀገር ውስጥም የውጭ ሀገር ሊግን በትኩረት፣ በእውቀት ይከታተላል። ጥሩ ከተጫወትክ አንተን ነው የሚደግፈው። ይህ ብቻ አይደለም የድሬዳዋ ተጫዋች ሆኖ ተገቢ ያልሆነ ባህሪ አሳይቶ በቀይ ካርድ ከሜዳ ቢወጣ ተጫዋቹ ለሰራው ስህተት በማንም ላይ ተቃውሞ ሳያሰማ ውሳኔው ትክክል መሆኑን አምኖ የሚቀበል የበሰለ ደጋፊ ነው ያለን። ይሄንንም ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ የተናገረችው ነው። ደጋፊዎቻችን ላይ ከሌላው ደጋፊ ኮራ ብለን የምንናገረው መገለጫችን ነው።

ይህን የደጋፊውን መገለጫ የሆነውን መልካም ባህሪ ለማስቀጠል ምን ታስባላችሁ? አንዳንዴ የሚፈጠሩ ጥሩ ያልሆኑ ነገሮች ስላሉ ?

እኛ ባለፈው ዓመት ደጋፊው በሚታወቅበት የመደገፍ ባህል እንዲቀጥል ዋናው እቅዳችን እና አላማችን ነበር። ደጋፊውን ወደ ሜዳ ማምጣት፤ ሜዳ ሲመጣ ደግሞ በነበረው መልካም የድጋፍ ሥርዓት እንዲቀጥል ብዙ ሠርተን ነበር። ይሄም ውድድሩ እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ ተሳክቶልናል ብለን እናስባለን። ግን ገና ብዙ ሥራ ይጠብቀናል። ባሉን ሃያ አባላት እና በሥሩ ካሉት ወደ ታች ተበትኖ አልፎ አልፎ የዲሲፕሊን ችግር ያለባቸው ልጆች፤ ያልሆነ ነገር ወስደው የሚመጡ ተመልካቾች አሉ። እነርሱን ለማስተካከል እየሰራን ነበር። ከዚህ ውጭ የድሬ ደጋፊ ላይ ያን ያህል የሚያሳስብ ነገር አላየንም።

የዘንድሮ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ታኅሣሥ ላይ እንደሚጀመር ይፋ ሆኗል። በኮሮና ምክንያት ውድድሮቹ ደግሞ ያለ ደጋፊ በዝግ እንደሚደረጉ ተወስኗል። ይህ በመሆኑ ክለቡ ከተመልካች ገቢ የሚያገኘውን ጥቅም እንዳያጣ ምን ለማድረግ አሰባችሁ?

የድሬዳዋ ደጋፊ በጣም ኳስ የሚወድ ህዝብ ነው። የዛሬ ሦስት ዓመት ካስታወስክ ድሬደዋ በሜዳው ከወልዲያ ጋር የነበረው ጨዋታ በዝግ እንዲሆን በመወሰኑ ምክንያት ደጋፊው ተራራ፣ ዛፍ ላይ ወጥቶ ጨዋታ ሲከታተል የነበረ ደጋፊ ነው። ያው ዓለም ላይ የመጣ በሽታ በመሆኑ በዝግ መሆኑ ተገቢ ነው። አሁን ደግሞ የተሻለ አማራጭ መጥቷል። በዲኤስ ቲቪ፣ በሬዲዮ መከታተል ይቻላል። ኮሮና ጠፍቶ ጨዋታዎቹ ለተመልካች ክፍት እስኪሆን ድረስ እንደ ደጋፊ ማኅበር ያስቀመጥናቸው እቅዶች አሉ። ደጋፊውን ቁጭ አድርገን በመሰብሰብ እንዴት ደጋፊውን ወደ ሀብት መቀየር ይቻላል በሚለው ጉዳይ ላይ ብዙ እየሰራን ነው።

ወደ ግል ጥያቄ ልምጣ፤ ድሬዳዋን መደገፍ ከጀመርክ ምን ይህል ጊዜ ሆነህ?

የሚገርምህ የተወለድኩት ኮኔል ሜዳ አካባቢ ስለሆነ እግርኳስን እየተጫወትኩ ነው ያደግኩት። ልጅ ሆኜ ስታዲየም በመሄድ የባቡር እና የጨርቃጨርቅ ጨዋታን እመለከት ነበር። ዮርዳኖስ ዓባይ፣ አሸናፊ ግርማ፣ አህመድ ጁንዲ፣ ኤልያስ፣ ዶቃ… እየተመለከትኩ ነው ያደግኩት። ከዛ ጊዜ ጀምሮ የእግርኳስ ፍቅሩ እየጨመረ መጥቶ እስካሁን ድሬዳዋ ከተማን መደገፍ ችያለሁ።

በድሬዳዋ ደጋፊነትህ የተደሰትክበት ጊዜ የቱ ነው?

በሁለት አጋጣሚዎች በተለየ ሁኔታ በድሬዳዋ ከተማ ተደስቻለሁ። አንደኛው ከጅማ አባቡና ጋር ላለመውረድ ተጫውተን ካሸነፍን በሊጉ የምንቆይበት ጨዋታ ነበር። ጨዋታውን ደጋፊው በጉጉት ነበር የሚጠብቀው። በስታዲየሙ የነበረው የደጋፊ ብዛት ድባቡ ልነግርህ አልችልም። ሁላችንም በጭንቀት ተውጠን ባለንበት ሰዓት በመጨረሻው ደቂቃ ባሰረቆጠርነው ጎል በሊጉ መቆየት የቻልንበት፤ ደጋፊው የተደሰተበት አጋጣሚን መቼም አረሳውም። ሁለተኛው አሸናፊ ግርማ ድሬ ከተማ እያለ ጊዮርጊስ ላይ ከመሐል ሜዳ ያስቆጠራት ጎል መቼም የማልረሳት አስደሳች ጎል ነበረች።

ድሬዳዋ የብዙ እግርኳሰኛ መፍለቂያ ከተማ ሆና ሳለ ክለቡ አሁንም በተጫዋች ግዢ ላይ ትኩረቱን አድርጓል። ክለቡ በአካባቢው ባሉ ጥሩ ተጫዋቾች ላይ እንዲያተኩር እንደ ደጋፊ ማኅበር ምን ታስባለህ?

ትክክል ነው። እኛም እንደ ደጋፊ ማኅበር ሁሌም የምናወራው ነገር ነው። ድሬዳዋ ብሔራዊ ቡድን ላይ የነበራት የተጫዋች ብዛት፣ ብዛት ብቻ ሳይሆን የነበራት ጥራት ልዩ ነበር። እነ አሸናፊ ግርማ፣ ዮርዳኖስ ዓባይ፣ ስምዖን ዓባይ፣ አህመድ ጁንዲ፣ አሰግድ ተስፋዬ እና ሌሎቹንም ያፈራች ከተማ አሁን ያን ያህል እያገኘን አለመሆኑ ያሳስባል። አሁን ግን ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ጥሩ እየተሰሩ ነው፤ ለውጦችም አሉ። ሙሉ ለሙሉ ባይሆንም ትንሽ ብልጭ የማለት ነገር አለ። ቢያንስ ባለፈው ዓመት ወደ አስራ ስድስት ተጫዋች ከዚሁ አካባቢ የተገኙ ናቸው። ይህ እሰየው የሚያስብል ነገር ነው። ግን ብዛት ያለው ነገር ሳይሆን ጥራት ያለው ተጫዋች ማፍራት እንዳለብን የምናምነው ጉዳይ ነው። ወደ ሜዳ በቋሚነት ገብተው የሚጫወቱ ተጫዋቾችን በጥራት መጨመር አለብን። የክለቡም ቦርድ ይሄንኑ ነው የሚያምነው። አሁን ክለቡ እየሠራበት ያለው ከ20 እና ከ17 ዓመት በታች የሚል ፕሮግራም አለ። እርሱን እንደ አካዳሚ ቅርፅ ያለው ሁሉ ነገር ያሟላ የታቀደ እቅድ አለ አንድ፣ ሁለት ዓመት ሊፈጅ ይችላል። በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገባ አምናለው። በዚህም ያጣነውን ትውልድ እናገኘዋለን ብዬ አስባለው። አሁን ያሉ ወቅታዊ ነገሮች እንዳንሠራ ነው እያደረገን ያለው። ኮሮና መጣ እንጂ የቀበሌ ውድድሮች ቢኖሩ ለመመረጥ ይቻል ነበር። በአጠቃላይ ግን ጥሩ እንቅስቃሴ አሁን አለ።

በመጨረሻም የምታስተላልፈው መልዕክት አለህ? በስፖርታዊ ጨዋነት እና ሌሎችም ካሉህ ሀሳብህ አካፍል..

ያው እኛ ሀገር ጥሩ እግርኳስ ተጫውተን አይደለም ደጋፊው የበዛው፤ ህዝቡ እግርኳስን ስለሚወድ ነው። ድሬዳዋን ለማየት ባህርዳር፣ ጎንደር አዲስ አበባ ሄጄ ተመልክቼ አውቃለው። ያለው የተመልካች ብዛትና ድባብ በጣም ደስ የሚል ነው። ይህ ነገር ጥሩ ሆኖ ሳለ አንዳንዴ የሚፈጠሩ አላስፈላጊ ነገሮች በእግርኳሳችን እድገት ላይ ተፅእኖ አሳድረዋል። እግርኳስ ማለት መዝናኛ ነው። ህዝባዊ ትስስር የምትፈጥርበት፣ በገንዘብ አቅምም ትልቅ የገቢ ምንጭ ነው። ስለዚህ ሁከቱ እና ብጥብጡ እግርኳሳችንን የተሻለ ቦታ እንዳይደርስ የሚያደርግ በመሆኑ እግርኳሳችን የተሻለ ደረጃ እንዲደርስ ከፈለግን ኳስ እና ኳስን ያማከለ ድጋፍ እንዲኖረን ያስፈልጋል።

ሌላው ማስተላለፍ የምፈልገው ነገር አለ። አንዳንድ በተጫዋቾቻችን የማየው ነገር አለ። ፌዴሬሽኑ ያስቀመጠው የደቦዝ ጣርያ ገደብ አለመከበሩ በተለይ እኛ ድሬዳዋን እየጎዳ ነው። በሌሎች ቡድኖች ከስር ከስር ከጀርባ የሚሰራው ሥራ ክለባችን እየጎዳ ነው። ፌዴሬሽኑ ባስቀመጠው መመርያ መሠረት እየሄድን ነው። ሌሎች የሚሄዱበትን የተሳሳተ መንገድ እንዲያስተካክሉ ደግሞ ፌዴሬሽኑ ጥብቅ ክትትል ማድረግ መቆጣጠር አለበት መልዕክቴ ነው። ኮሮና ከዓለማችን እና ከሀገራችን ጠፍቶ ተሰባስበን፣ እየጨፈርን፣ እየተዝናናን የምናይበት ዓመት እንዲሆን እመኛለሁ።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!