ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | አዳማ ከተማ ስምንት አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈርሟል

በአሰልጣኝ ሳሙኤል አበራ የሚመሩት አዳማ ከተማዎች ስምንት አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈርመዋል፡፡

የ2011 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ቻምፒዮኑ አዳማ ከተማ ባጣቸው ወሳኝ ተጫዋቾቹን ምትክ አዳዲስ ተጫዋቾችን ማስፈረም ጀምሯል፡፡ ክለቡ የአሰልጣኝ ሳሙኤል አበራን ውል ካራዘመ በኃላ የሣራ ነብሶ፣ ናርዶስ ጌትነት፣ እምወድሽ ይርጋሸዋ እና ሀና ኃይሉን ውል ለተጨማሪ ዓመት ያራዘመ ሲሆን አሁን ደግሞ ከተለያዩ ክለቦች ስምንት አዳዲስ ተጫዋቾችን ማስፈረሙን ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል፡፡

ከአዳዲስ ፈራሚዎቹ መካከል ከጂንካ አካባቢ በአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው መልማይነት ከተገኘች በኃላ ከአራት ዓመት በፊት ንግድ ባንክን በመቀላቀል ተጠባባቂ ግብ ጠባቂ በመሆን ስታገለግል የነበረችው እየሩሳሌም ቶሌራ፣ የቀድሞዋ የሀዋሳ ከተማ እንዲሁም በንግድ ባንክ ያለፉትን ሁለት ዓመታት ቆይታ የነበራት ተከላካይዋ ሰብለ ቶጋ፣ ከኢትዮጵያ ወጣቶች አካዳሚ ተገኝታ በመከላከያ ያለፉትን ሁለት ዓመታት ቆይታ ያደረገችው አማካይዋ ሲሳይ ገብረዋህድ ክለቡን ከተቀላቀሉት መካከል ሲሆኑ ከአቃቂ ቃሊቲ አማካዮቹ ፀባኦት መሐመድ እና ማህሌት ታደሰ እንዲሁም ተከላካዮቹ ሳምራዊት አሰፋ (ከቦሌ ክፍለ ከተማ)፣ ምህረት ተክለልዑል (ከአዲስ አበባ ከተማ) እና ዝናሽ መንክር (ከአቃቂ ቃሊቲ) በሁለት ዓመት ውል አዳማ ከተማን የተቀላቀሉ ተጫዋቾች ሆነዋል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!