“…በፍፁም ሆንብዬ ያደረኩት አይደለም” ታፈሰ ሰለሞን

ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር በዝግጅት ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቡናው ድንቅ አማካይ ታፈሰ ሰለሞን ስለ ወቅታዊው አነጋጋሪ ጉዳይ ይናገራል።

በኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ኒያላ፣ ሀዋሳ ከተማ የእግርኳስ ህይወቱን በተሳካ ሁኔታ ከመራ በኃላ ከዓምና ጀምሮ ኢትዮጵያ ቡናን እያገለገለ የሚገኘው አማካይ ታፈሰ ሰለሞን በአሁኑ ሰዓት ለብሔራዊ ቡድኑ ጥሪ ቀርቦለት አያት አካባቢ በሚገኘው የካፍ ልህቀት ማዕከል በዝግጅት ላይ ይገኛል። ከሰሞኑን በማኅበራዊ ሚዲያ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች ጋር በመሆን የተነሳው ፎቶ ከተለቀቀ በኃላ ድርጊቱ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎችን እንዳላስደሰተ በተለያዩ መንገዶች ሲገለፅ መቆየቱ ይታወቃል። ይህን ተከትሎ በዛሬው ዕለት የብሔራዊ ቡድኑን ልምምድ ለመቃኘት በሄድንበት አጋጣሚ የተፈጠረውን ሁኔታ እንዲያጋራን ጠይቀነው ተከታዩን ምላሽ ሰጥቶናል።

” የተወሰኑ ልጆች ከቡድኑ ጋር አልነበሩም። አብረውን ተቀላቅለው ልምምድ ሲጀምሩ ያው ከረጅም ወራት በኃላ ስለተገናኘን ለማስታወሻ ያህል ፎቶ እንነሳ ተበብለን መጀመርያ እኔ፣ አስቻለው ታመነ እና ጋዲሳ መብራቴ ተነስተን ነበር። እነርሱ በራሳቸው ምልዕክት እኔም በኢትዮጵያ ቡና ምልክት ተነሳን። በኃላ ሌሎች ተጫዋቾች ተጨምረው ሲመጡ ‘ባክህ አንድ አይነት እንነሳ’ ብለው ሲጠይቁኝ በኃላ ምን ሊሆን እንደሚችል ስላልገመትኩ እሺ ብዬ ተነሳው። ምሳ በልተን ተኝቼ እረፍት አድርጌ ስነሳ ይሄን ነገር መሆኑን ሳይ ደንግጬ አስቻለው ታመነ ያለበት ክፍል በመሄድ ‘ይህን ለምን አደረክ፣ እኔ በቡና ምልክት የተነሳሁትን ፎቶ አታደርገውም ነበር?’ አልኩት። ‘አይ እርሱ ስለ ደበዘዘብኝ (ጥራት የሌለው በመሆኑ) ሌላ ፎቶ ያደረኩት ለዛ ነው’ አለኝ። የሆነው ይህ ነው። በተፈጠረው ነገር በጣም አዝኛለው። የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ በሌላ መንገድ እንዳይመለከትብኝ እጠይቃለው። በፍፁም ሆን ብዬ ያደረኩት አይደለም። አንዳንዴ ነገሮችን አቅልለህ የምታደርጋቸው ምን ያህል አስቸጋሪ ነገር ይዘው እንደሚመጡ ትምህርት ወስጄበታለው።”

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!