ሶከር ሜዲካል | እግር ኳሳችን እና ህክምና …

ከእግርኳስ ጋር የተገናኙ የህክምና መረጃዎችን ወደ እናንተ በምናደርስበት የሶከር ሜዲካል ዓምዳችን በቅርቡ ወደ ልምምድ ወደተመለሰው እና ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎችን ወዳደረገው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ትኩረታችንን ለማዞር ወደድን።

በዚህ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የህክምና አባል የሆነችው ዶክተር ቃልኪዳን ዘገየን አናግረናል። ከቆይታችን ብዙ እንደምትማሩ ተስፋ እናደርጋለን። ዶክተር ቃልኪዳን በፈቃደኝነት ለሰጠችን መልስ እና ስለ ትብብሯ በእናንተ ክቡር አንባቢዎቻችን ስም እናመሰግናለን።

በመጀመሪያ ራስሽን አስተዋውቂልን አያይዘሽም። ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ጋር መቼ መሥራት እንደጀመራችሁ እና ኃላፊነታችሁ ምን እንደሆነ ብትገልጪልን ?

በመጀመሪያ ይህን ዕድል ስለሰጣችሁኝ ላመሰግናችሁ እወዳለው። ዶ/ር ቃልኪዳን ዘገየ እባላለሁ። በራስ ደስታ ሆስፒታል የድንገተኛ ክፍል ውስጥ ነው የምሰራው። በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስር በተቋቋመው የህክምና ኮሚቴ ውስጥም አባል ሆኜ በማገልገል ላይ እገኛለው። ባለፉት ሁለት ዓመታት በሁለቱም ፆታዎች በተለያዩ የዕድሜ እርከኖች ባሉ ብሔራዊ ቡድኖች ውስጥ በሀኪምነት እና በሌሎች ስራዎች በበጎ ፍቃደኝነት እሰራለሁ።

በእግር ኳሱ እና በህክምናው መካከል ያለውን ክፍተት ለመድፈን ምን እየሰራችሁ ነው ? ለወደፊትስ ምን መሰራት አለበት ?

የህክምናው ቡድን ድሮም የነበረ ነው። አሁን እኛ ከገባን በኋላ አዳዲስ ያደረግናቸው ነገሮች ግን አሉ። ስፖርት ወዳድ የሆኑ ባለሙያዎች በብዛት እንዲሳተፉ አድርገናል። ምክንያቱም ከተለያየ ስፔሻሊቲ የተዋቀረ ቡድን ሲሆን እንጠነከራለን። አንዱ ከአንዱ ሀሳብ የማንሸራሸር እና የመደጋገፍ ነገር ይኖራል ብለን ስላሰብን ነው። ኒውትሪሽኒስቶች ፣ ሳይካትሪስቶች ፣ ሪሀቢሊቴሽን ስፔሻሊስቶች ፣ ኦርቶፔዲሺያኖች ፣ ኢንተርኒስቶች እና ብዙዎችን አካተናል። በአጠቃላይ ስፖርቱን የሚወዱ እና በፍቃደኝነት የሚሰሩ ብዙ ባለሙያዎችን ማሰባሰብ ችለናል። ሀሳብ ከማዋጣቱ ባለፈ ከጎረቤት እና ከሌሎች ሀገራትም ልምድ በመውሰድ ስራውን ለማጠናከር እየሞከርን ነው። ምክንያቱም እኛ ብንወጣ እንኳን ለሚቀጥሉት ባለሙያዎች ጥሩ ነገር መተው አለብን። ይህን በመስራት ላይ ሳለን ነው የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ የተከሰተው። ያው የኮሮና ቫይረስ በስፖርቱ ላይ ትልቅ ተፅዕኖ አሳድሯል። ስፖርቱ በባህሪው በንክኪ የሚተገበሩ እንቅስቃሴዎችን ያካተተ እና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አንድ ጊዜ የሚሳተፉበት በመሆኑ በቀላሉ እንዲታለፍ ያደርጋል በሚል ታግዶ ነበር። አሁን ግን ዓለምአቀፋዊ እና አህጉራዊ ውድድሮች እየቀጠሉ ይገኛሉ። ስለዚህ በዛ መሰረት ‘እኛ እንደኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የህክምና ቡድን በምን መልክ ነው መዘጋጀት ያለብን ?’ ብለን እየተወያየን ነበር። ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት በኮሚቴያችን ስለኮቪድ 19 ጥንቃቄ አወሳሰድ ግንዛቤን ከማስጨበጥ አንፃር የማስፈፀሚያ ዕቅዶችን ማውጣት እንዳለብን ተነጋግረናል። ከፊፋ እና ከካፍ የውድድር ማስቀጠያ አቅጣጫዎችን በማየት ገመገምን ወደ እኛ ሀገር አምጥተን መሬት ላይ ማውረድ የምንችልበትን መንገድ ተወያየን። በእርግጥ የእነሱን ሀሳብ ሙሉ ለሙሉ ለመተግበር ከፋይናንስ እና ከባለሙያ እጥሩት አንፃር ከባድ ነው። የቫይረሱን ስርጭት ገድበን ውድድሮችን ማስቀጠል የምንችልበትን ዕቅድ ፣ ከፌዴሬሽኑ እና ከህክምና ኮሚቴው የሚጠበቁ ኃላፊነቶች እና ውጤቶችን ፣ የሚከናወኑ ተግባራትን በመዘርዘር አዘጋጅተናል። ከዚህ በተጨማሪ ይደረጋሉ ተብለው በሚታሰቡ ውድድሮችን በበላይነት የሚቆጣጠር ፣ የሚገመግም እና እዛ አካባቢ የሚከናወኑ ነገሮችን የሚከታተል የኮቪድ ኦፊሰር አቋቁመናል። ከኦፊሰሩ ጋር መረጃዎችን በመለዋወጥ ፣ በመወያየት እና በአካል በመጎብኘት ጭምር የጎደሉትን ነገሮች በማሟላት እየሰራን እንገኛለን። ሌላ ያደረግነው አዲስ ነገር ከጤና ሚኒስትር እና ከማሕበረሰብ ጤና ኤኒስቲቲውት ጋር በተጓዳኝነት እየሰራን እንገኛለን። ምክንያቱም ካለእነሱ ምንም ነገር ማከናወን አንችልም። በዚህ አጋጣሚም ለእነሱ ምስጋናዬን ማቅረብ እፈልጋለው። ምርምራ ሲባል ደስተኛ ሆነው በመምጣት በፈለግንበት ቦታ እና ጊዜ ምርመራዎችን ያደርጉልናል። የጨዋታ ቦታዎችን መገምገም እና የፀረ ተዋስያን ርጭት ማድረግ ሲያስፈልግ የመከላከያ ዕቃዎችን በማቅረብ ባለሙያዎቻቸውን በመላክ አብረውን እየሰሩ ይገኛሉ። በወቅታዊነት እነዚህን ነገሮች እየሰራን ነው። ለወደፊት ከዚህም በላይ ብዙ መሰራት አለበት። ኮሚቴውንም በደንብ ማጠናከር ይኖርብናል። በበጎ ፍቃድ የሚሰራ ስለሆነ የሚሄድ ሰው እንኳን ቢኖር እንዳይፈርስ በደንብ መሰረቱን ባለሙያዎችን በማሳተፍ እና ለስፖርቱ ቅርብ በማድረግ ማደራጀት እንዳለብን ይሰማኛል።

ክለቦች እንዴት የጤና ባለሙያዎችን ማካተት አለባቸው ብለሽ ታስቢያለሽ ?

ግዴታ ቅጥር መፈፀም ነው ያለባቸው። ለምሳሌ ትምህርት ቤቶች በአብዛኛው የጤና ባለሙያ እየቀጠሩ ነው ፤ በተለይ በወረርሺኙ ምክንያት። እኛም በዕቅዳችን የኮቪድ ኦፊሰርን ቅጥርን አካተናል። ኮቪድ ላይ ብቻ ስናተኩር ሌሎች ነገሮችም እንዳይረሱ አብሮ በተጨማሪ ጤና ነክ ኃላፊነቶች ይኖሩታል። እኛ እንደ ህክምና ቡድን ይህን ማድረግ ግዴታ መሆን አለበት ባዮች ነን።

በሥራ ላይ የታዘባችሁት እና ቢሻሻል የምትሉት ነገር ምን አለ? ከፌደሬሽን፣ ከጤና ባለሙያ ፣ ከአሰልጣኝ ፣ ከተጫዋቾች እና ከሚዲያው ምን ይጠበቃል?

የህክምና ኮሚቴ በራሱ ተነሳሽነት ሀገሩን ለማገልገል የመጣ በመሆኑ ለሚሰራው ስራ ዕውቅና መስጠት እና ማበረታት ከፌዴሬሽኑ ይጠበቃል። የፓናል ውይይቶች ፣ አህጉራዊ እና ዓላምአቀፋዊ የልምምድ ልውውጦች ፣ ሲምፖዚየሞች ማናቸውም ይህን ዘርፍ የሚጠቅሙ መድረኮች ሲኖሩ ባለሙያውን በመላክ እና በማሳተፍ እዚህ ደግሞ ይዘውት የመጡትን ልምድ ከስፖርት አመራሩ ፣ ከስፖርተኛው እና ከህክምና ኮሚቴ አባላት ጋር እንዲያካፍሉ በማድረግ እዛ ከባቢ ላይ ጥሩ ግንኙነት እንዲፈጠር ማድረግም አስፈላጊ ነው። በአጠቃላይ የህክምና ባለሙያው እንዳይሰላች መደገፍ ፤ በፋይናንስ ብቻ ሳይሆን በሀሳብ ደረጃም። ቁሳቁሶችን ከማሟላት እና ከሌሎች ኃላፊነቶች ናሻገር በዋነኝነት እነዚህ ነጥቦች ከፌዴሬሽኑ ይጠበቃሉ። ከጤና ባለሙያው ደግሞ እንደስከዛሬው ሁሉ በበጎ ፍቃደኝነት፣ በሙሉ ልብ እና ተነሳሽነት መስራት ይጠበቃል። ሌሎች ባለሙያዎችን በመጋበዝ ኮሚቴውን በማስፋት ያስፈልጋል። በቅርብ ከምናያቸው እንኳን እንደ ኬኒያ እና ዩጋንዳ በመሳሰሉ ሀገራት ስፖርታዊ የህክምና መዋቅሮቻቸው በጣም የሰፉ ናቸው። እኛም በዛ መጠን እንድንሰራ ዓመታዊ የልምድ ልውውጥ መድረኮች እና የግንዛቤ ማስጨበጫዎችን በመፍጠር ፣ በዘርፉ ያሉ አዳዲስ ነገሮችን በማወቅ ፣ ጥናቶችን በማድረግ ኮሚቴውን ማጠናከር ይጠበቅበታል። ከአሰልጣኞች እና ተጫዋቾች እንደህክምና ባለሙያነታችን ከእኛ የሚደርሳቸውን ነገሮች በሚገባ ተረድተው በተግባር ማዋል ይጠበቃል። በተጨማሪም ከእኛ ጋር ጥሩ የሆነ ግንኙነት እንዲኖረን በግልፅ መወያየት እና መስተካከል ያለባቸውን ነገሮች በመጠቆም ሀሳብ ማንሸራሸር ይጠበቃል። በሚዲያው በኩል ደግሞ ትኩረት በመስጠት መረጃ ከማስተላለፍ በተጨማሪ የትኛውም መሻሻል ያለባቸውን ነገሮች ከመጠቆም እና ስፖርቱን አንድላይ ከመገንባት አንፃር ብዙ ይጠበቃል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!