ኬንያ ጋናን በማሸነፏ ሴራሊዮን የምድቡ መሪ ሆናለች

በ2019ኙ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ኢትዮጵያ በምትገኝበት ምድብ 6 ሁለተኛ ጨዋታ ጋናን ያስተናገደችው ኬንያ 1-0 በማሸነፍ የመጀመሪያ 3 ነጥቧን አሳክታለች። በጨዋታው የመጨረሻ 30 ደቂቃዎች በ10 ተጫዋች ለመጫወት የተገደዱት የሃራምቤ ከዋክብቱ ኒኮላስ ኦፖኩ በራሱ ግብ ላይ ባስቆጠረው ግብ ሃያሏን ጋና ማሸነፍ ችለዋል።

በናይሮቢው ካሳራኒ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ተመጣጣኝ የሆነ እንቅስቃሴ የተስተዋለ ሲሆን ኬንያዎች በኦቬላ ኦቼንግ እና ኢስማኤል አቱማን ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን አድርገዋል። በጋና በኩል ደግሞ አጥቂው ማጅድ ዋሪስ በተደጋጋሚ አፈትልኮ ለመውጣት የሚያደርጋቸው ሙከራዎች ለኬንያ የተከላካይ መስመር ፈተና ነበሩ።

በ39ኛው ደቂቃ ኤሪክ ጆሃና ያሳለፈውን ኳስ ለማግኘት ሚካኤል ኦሉንጋ በጋናው ተከላካይ ኒኮላስ ኦፖኩ ጋር ጫና በሚያደርግበት ጊዜ ተከላካዩ በራሱ መረብ ላይ ግብ አስቆጥሯል።

ጋናዎች ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ሙሉ በሙሉ በማጥቃት የተጫወቱ ሲሆን የሃራምቤ ከዋክብቱ ደግሞ መሪነታቸውን ለማስጠበቅ አፈግፍገዋል። የኬንያው ተከላካይ ጆአሽ ኦንያንጎም በ63ኛው ደቂቃ በሁለተኛ ቢጫ ከሜዳ ተወግዷል። አሰልጣኝ ሰባስቲያን ሚኜ ክፍተቱን ለመሙላት የመከላከል ባህሪ ያላቸውን ዴቪድ ኦቼንግ እና አንቶኒ አኩሙ ቀይረው በማስገባት የኋላ መስመሩን አጠንክረዋል።

የአቻነት ግብ ላለማስተናገድ እስከመጨረሻው ደቂቃ በትኩረት የተጫወቱት ኬንያዎች እቅዳቸው ሰምሮ ጨዋታውን በአሸናፊነት ማጠናቀቅ ችለዋል።

ውጤቱን ተከትሎ ለእርስ በርስ ግንኙነት ከግብ ክፍያ በላይ ዋጋ በሚሰጥበት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ነገ ከኢትዮጵያ ጋር የምትጫወተው ሴራሊዮን በ3 ነጥብ እና አንድ የግብ ክፍያ የምድቡ መሪ መሆን ችላለች። ኬንያ እና ጋና በተመሳሳይ 3 ነጥብ በእርስ በርስ ግንኙነት ውጤት ተበላልጠው ሁለተኛ እና ሶስተኛ ሲሆኑ ያለ ምንም ነጥብ 5 የግብ ዕዳ ያለባቸው ዋሊያዎቹ የመጨረሻውን ደረጃ ይዘዋል።

በምድብ ማጣሪያው ሁለተኛ ዙር ሌላው ጨዋታ ነገ 10 ሰዓት ላይ ኢትዮጵያ እና ሴራሊዮን በሐዋሳ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ይጫወታሉ።