ወላይታ ድቻ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከሷል

ዛሬ ረፋድ ያለ ጎል ጨዋታውን ከወላይታ ድቻ ጋር ፈፅሞ የነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስ የተጫዋች ተገቢነት ክስ ቀርቦበታል፡፡

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ23ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ ረፋድ 04፡00 ላይ መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወላይታ ድቻ ተገናኝተው ያለ ጎል ጨዋታቸውን መፈፀማቸው ይታወሳል፡፡ ከዚህ ጨዋታ ጋር በተያያዘ ከደቂቃዎች በፊት የወላይታ ድቻ ክለብ በቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ከተጫዋች ተገቢነት ጋር በተያያዘ ቅሬታ አለኝ በማለት ለፕሪምየር ሊጉ አወዳዳሪ አካል የቅሬታ ደብዳቤ ማስገባቱን የክለቡ ቡድን መሪ አቶ ዘላለም ለሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጠዋል፡፡

ክለቡ “ቅዱስ ጊዮርጊስ በጨዋታው ላይ ሦስት ጊዜ ብቻ አምስት ተጫዋቾችን መቀየር ሲኖርበት ክለቡ ይሄን ህግ በመጣስ ከዕረፍት በፊት ከነዓን ማርክነህን በሀይደር ሸረፋ ፣ ከዕረፍት መልስ ደስታ ደሙን በሱለይማን ሀሚድ ፣ ቡልቻ ሹራን በዳግማዊ አርአያ እና ጋቶች ፓኖምን በናትናኤል ዘለቀ በአራት የቅያሬ ጊዜ የለወጠበት ሂደት ከተቀመጠው ደንብ ውጪ በመሆኑ የጨዋታው ውጤት ይገባናል።” በማለት አቤቱታውን ማቅረቡን የቡድን መሪው ጨምረው ገልፀውልናል፡፡