​አማረ በቀለ የ6 ወራት እገዳ ተላለፈበት

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዲሲፕሊን ኮሚቴ በ8ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ተጫዋቾች በፈፀሙት የስፖርታዊ ጨዋነት ግድፈቶች ላይ የቅጣት ውሳኔ አሳልፏል፡፡

አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ኢትዮጵያ ቡና ከ ወልዲያ ባደረጉት ጨዋታ ኤልያስ ማሞ ያስቆጠረው የፍጹም ቅጣት ምት እንዲሰጥ ምክንያት የሆነው አማረ በቀለ ከፍጹም ቅጣት ምቱ ውሳኔ በኋላ ከዳኛው ጋር በገባው እሰጥ እገባ 62ኛው ደቂቃ ላይ በቀይ ካርድ ከሜዳ መውጣቱ ይታወሳል፡፡ የእለቱ አመራሮች ባቀረቡት ሪፖርት መሰረትም አማረ ዳኛውን ለመማታት ሙከራ ማድረጉ በመገለፁ 6 ወራት ከእግርኳስ እንዲታገድ እና 10 ሺህ ብር እንዲከፍል ተወስኖበታል፡፡

በተመሳሳይ አማረ በቀለ ከሜዳ ከወጣ ከ3 ደቂቃ በኋላ የቀይ ካርድ የተመዘዘበት ብሩክ ቃልቦሬ የተጋጣሚ ተጫዋችን በቡጢ መማታቱ በሪፖርት በመገለፁ ለፈፀመው ጥፋት 4 ጨዋታ እና 4ሺህ ብር ቅጣት ተላልፎበታል፡፡

ጎንደር ላይ ፋሲል ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ጭማሪ የጨዋታ ደቂዎች ላይ የእለቱን ዳኞች አፀያፊ ስድብ እንደተሳደበ በጨዋታ አመራሮች ሪፖርት የተደረገበት ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን 3 ጨዋታ ቅጣት እና 3 ሺህ ብር ቅጣት ተላልፎበታል፡፡

በተያያዘ የቅጣት መረጃ በ7ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አዲግራት ላይ ወልዋሎ ከ መከላከያ ባደረጉት ጨዋታ እርስ በእርስ በመደባደባቸው በቀይ ካርድ ከሜዳ የተወገዱት የመከላከያው ሳሙኤል ሳሊሶ እና የወልዋሎው እንየው ካሳሁን እያንዳንዳቸው 4 ጨዋታ እና 4ሺህ ብር ቅጣት ተላልፎባለቸዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *