ሴራሊዮን በፊፋ እገዳ ተጣለባት 

የእግር ኳስ የበላይ አስተዳደር የሆነው ፊፋ ዛሬ ባስታወቀው መሰረት በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ምድብ ስድስት ከኢትዮጵያ፣ ጋና እና ኬንያ ጋር የተደለደለችው ሴራሊዮን የእግር ኳስ ፌደሬሽን ላይ የእገዳ ውሳኔ አስተላልፏል። ፊፋ ውሳኔው ላይ የደረሰበት ምክንያት የመንግስት ጣልቃ ገብነት መሆኑን እና የሴራሊዮን እግር ኳስ ፌደሬሽን በስሩ የሚተዳደሩ ተቋማት ከመንግስት ነፃ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ከሆነ እገዳው ሊነሳ እንደሚችል በድረ ገፁ አስታውቋል።

የሴራሊዮን እገዳ የማይነሳ ከሆነ ብሔራዊ ቡድኑ ከኬንያ እና ኢትዮጵያ ጋር ያደረጋቸው ጨዋታዎች የማይቆጠሩ ይሆናል። ኢትዮጵያ ሴራሊዮንን አሸንፋ ያገኘችው ሶስት ነጥብም አይያዝም። ይህን ተከትሎም ጋና 3 እና ኬንያ ነጥቦች ሲኖራቸው ኢትዮጵያ ያለምንም ነጥብ ግርጌውን የረዛ ትቀጥላለች። 

የፊፋ እገዳ በቋሚነት የሚፀና ከሆነ ሶስት ቡድኖች ከሚቀሩበት ምድብ 6 ወደ አፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ ከባድ ፈተና ይጠበቃል። ኢትዮጵያ መስከረም 30 እና ጥቅምት 4 ከኬንያ ጋር የምታደርጋቸው ሁለት ተከታታይ የምድብ ጨዋታዎችም እጅጉን ወሳኝ ይሆናሉ ማለት ነው።