ኬንያ ከኢትዮጵያ ለምታደርጋቸው ጨዋታዎች 21 ተጫዋቾችን መርጣለች

ፈረንሳዊው የኬንያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሰባስቲየን ሚኜ በ2019ኙ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በጥቅምት ወር ኬንያ ከኢትዮጵያ ጋር ለምታደርጋቸው ሁለት ጨዋታዎች 21 ተጫዋቾችን ሲጠሩ ለእንግሊዙ ቶተንሃም የሚጫወተው አማካይ ቪክተር ዋንያማ ከጉዳት መልስ በቡድኑ መካተት ችሏል።

በቅድመ ውድድር ዘመን ዝግጅት ወቅት ባጋጠመው የጉልበት ጉዳት ምክንያት ኬንያ ጋናን ያስተናገደችበት ጨዋታ ያመለጠው ቪክተር ዋንያማ ከሳምንታት ቆይታ በኋላ ወደ ሜዳ መመለስ ችሏል።

ለደቡብ አፍሪካው ማሪትዝበርግ ዩናይትድ የሚጫወተው እና የጋናው ጨዋታ በቅጣት ያለፈው ተከላካዩ ብራያን ማንዴላ ካጋጠመው ጉዳት አገግሞ በጥሩ ጤንነት መገኘት ለአሰልጣኝ ሚኜ ሌላ መልካም ዜና ሲሆን የቡድኑን የተከላካይ መስመር ይበልጥ ያጠናክረዋል ተብሏል።

ሁለቱ ተጫዋቾች ከጉዳት መልስ መጠራታቸውን ተከትሎ የሃራምቤ ኮከቦቹ ኬንያን 1-0 ባሸነፉበት ጨዋታ የቡድኑ አባል የነበሩት እና ለዛምቢያው ዜስኮ ዩናይትድ የሚጫወቱት ዴቪድ ኦዊኖ እና ጄሲ ዌሬ ከስብስቡ ውጪ ሆነዋል።

አሰልጣኝ ሰባስቲየን ሚኜ በተጨማሪም ለተጠሩት ተጫዋቾች መጠባበቂያ እና ጉዳት ለሚያጋጥማቸውም ተተኪ የሚሆኑ ዘጠኝ በሃገር ውስጥ የሚጫወቱ ተጫዋቾችን በጥሪያቸው አካተዋል።

ዋልያዎቹ መስከረም 30 በሚደረገው የምድብ ማጣሪያው ሶስተኛ ጨዋታቸው ኬንያን በባህርዳር ዓለምአቀፍ ስታዲየም የሚያስተናግዱ ሲሆን ከቀናት በኋላም ጥቅምት 4 ቀን በናይሮቢው ካሳራኒ ስታዲየም ሁለተኛውን ጨዋታ የሚያደርጉ ይሆናል። በ2019ኙ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ምድብ 6 ጋና፣ ኬንያ፣ ሴራሊዮን እና ኢትዮጵያ በእኩል 3 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ተቀምጠዋል።

የተመረጡ ተጫዋቾች ዝርዝር

ግብ ጠባቂዎች

ፓትሪክ ማታሲ (ተስካር)፣ ፋሩክ ሺካሎ (ባንዳሪ)

ተከላካዮች

ፊሌሞን ኦቴኖ (ጎር ማሂያ)፣ ጆኪንስ አቱዶ ( ፖስታ ሬንጀርሰ)፣ ሙሳ መሐመድ (ንካና/ዛምቢያ)፣ ብሪያን ማንዴላ (ማሪትዝበርግ/ደቡብ አፍሪካ)፣ አቡድ ኦማር (ሰርክል ብሩዥ/ቤልጅየም)፣ ዴቪድ ኦቼንግ (ብሮማፖካርና/ስዊድን)፣ ኤሪክ ኦውና (ቫሳለንድ/ስዊድን)፣ ጆሴፍ ኦኩሙ (ሪል ሞናርክ/አሜሪካ)

አማካዮች

ዴኒስ ኦዲያምቦ (ስፋካፓ)፣ ፍራንሲስ ካሀታ (ጎር ማሂያ)፣ ኢስማኤል ጎንዛሌዝ (ላስ ፓልማስ/ስፔን)፣ ቪክቶር ዋንያማ (ቶተንሀም/እንግሊዝ)፣ አንቶኒ አኩሙ (ዜስኮ/ዛምቢያ)፣ ዮሀና ኦሞሎ (ሰርክል ብሩዥ/ቤልጅየም)፣ ፖል ዌሬ (ካይሰር/ካዛኪስታን)

አጥቂዎች

ፒስቶን ሙታምባ (ሶፋካፓ)፣ ሚካኤል ኦሉንጋ (ካሺዋ ሬሶል/ጃፓን)፣ ኤሪክ ዮሀና (ብሮማፖካርና/ስዊድን)፣ ኦቬላ ኦቼንግ (ቫሳላንድ/ስዊድን)