መጣባቸው ሙሉ ማረፊያው ታውቋል

የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ መጣባቸው ሙሉ በፋሲል ከነማ ካሳደጉት አሠልጣኝ ጋር ዳግም የተገናኘበትን ዝውውር አጠናቋል፡፡

በዛሬው ዕለት መሳይ ጳውሎስ እና ማማዱ ሲዲቤን ወደ ስብስቡ የቀላቀለው ድሬዳዋ ከተማ መጣባቸው ሙሉን የክለቡ አምስተኛ ፈራሚ አድርጎ በሁለት ዓመት ውል ወደ ቡድኑ ማምጣቱ ታውቋል፡፡ መጣባቸው ከፋሲል ከነማ የወጣት ቡድን በወቅቱ የክለቡ አሠልጣኝ በነበሩት ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ አማካኝነት ካደገ በኋላ ለዋናው ቡድን ከ2008 ጀምሮ ሲጫወት ቆይቷል፡፡

በመሐል 2009 ላይ በውሰት ለጅማ አባጅፋር ከመጫወቱ በቀር አምስት ዓመታት ከግማሽ ወራት ያህሉን በአሳዳጊው ክለብ ፋሲል ከነማ ያሳለፈው ተጫዋቹም በተጠናቀቀውን የውድድር ዘመን ከክለቡ ጋር የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ካነሳ በኋላ በፋሲል ከነማ ያሰለጠኑትን አሠልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስን ጥሪ ተቀብሎ ወደ ድሬዳዋ ተጉዟል፡፡