ምንያህል ይመር ወደ ድሬዳዋ አመራ

የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ምንያህል ይመር ኤሌክትሪክን ለቆ ወደ ድሬዳዋ ከተማ አምርቷል።

የዮሀንስ ሳህሌው ቡድን በዝውውር መስኮቱ በርካታ ተጫዋቾችን በማስፈረም ላይ የሚገኝ ሲሆን መቐለ ላይ በተስናገደው የትግራይ ዋንጫ ላይ ተሳታፊ የነበረው ድሬዳዋ ከተማ በውድድሩ ላይ የታየበትን የአማካይ ፈጣሪ ችግር ለመቅረፍ በማሰብ ምንያህል ይመርን ወደ ክለቡ ቀላቅሎታል።

ምንያህል ከኤሌክትሪክ ወጣት ቡድን ካደገ በኋላ ኤሌክትሪክን ሲያገለግል ቆይቶ ወደ ዳሽን በማምራት ክለቡ እስከፈረሰበት ጊዜ ድረስ ተጫውቷል። በ2009 ወደ ወልዲያ አምርቶ የአንድ ዓመት ቆይታን ካደረገ በኃላ በድጋሚ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በአሳዳጊ ቡድኑ ኤሌክትሪክ ተመልሶ ካሳፈ በኃላ ወደ ምስራቁ ክለብ ድሬዳዋ በአንድ ዓመት ውል አቅንቷል፡፡

ድሬዳዋ ከተማ የምንያህል የቡድን አጋር የነበረው ኃይሌ እሸቱን ጨምሮ 13 አዳዲስ ተጫዋቾችን በዚህ ክረምት አስፈርሟል።