ሴናፍ ዋቁማ እና ሰናይት ቦጋለ ለሙከራ ወደ ስዊድን አምርተዋል

ሁለቱ የአዳማ ከተማ ተጫዋቾች ሴናፍ ዋቁማ እና ሰናይት ቦጋለ ለአስር ቀናት ሙከራ ወደ ስውዲን ትላንት ተጉዘዋል ፡፡

በዘንደሮው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ዲቪዚዮን በአዳማ ከተማ የሴቶች ቡድን ውስጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ የነበራቸው እና ከክለቡ ጋር የ2011 የሊጉ ቻምፒዮን በመሆን ዓመቱን በድል የጨረሱት አማካዩዋ ሰናይት ቦጋለ እና የኮከብ ግብ አስቆጣሪነት ክብርን ያገኘችሁ አጥቂዋ ሴናፍ ዋቁማ ለአስር ቀናት የሙከራ ጊዜን በስውዲን ለማሳለፍ ትላንት አመሻሽ ወደ ስፍራው አቅንተዋል፡፡ ይህን ዕድል እንዲያገኙ ያስቻለው አሰልጣኝ ዐቢይ ካሳሁን እንደሆነ ለሶከር ኢትዮጵያ የተናገሩት ተጫዋቾቹ በሙከራ ጊዜያቸው የተሻለ ቆይታን አሳልፈው በስውዲን ሊግ ውስጥ ለመታየት ጥረት እንደሚያደርጉ ገልፀዋል፡፡

በአዳማ ከተማ ወጪያቸው ተሸንፍኖላቸው ወደ ስፍራው የሚያመሩት ሁለቱ ተጫዋቾች ለስውዲኑ ክለብ አይኤፍ ኬ አልካማር በተባለ ክለብ ነው የሙከራ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት። በቅርቡ ቱቱ በላይ እና ሎዛ አበራ ረዘም ያለ የሙከራ ጊዜን ያሳለፉ ሲሆን ከገንዘብ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ሳይስማሙ በመቅረታቸው መመለሳቸው ይታወሳል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በኢንተርኔት መቋረጥ ምክንያት በድረ-ገጻችን ላይ የወጡ ጽሁፎች መዘግየት ሊታይባቸው ይችላል።