ሀምበሪቾ ሦስት ተጫዋቾችን አስፈርሟል

አዲስ አዳጊው ሀምበሪቾ ዱራሜ ሦስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል።

ከፕሪምየር ሊግ ክለቦች የቅድመ ውድድር ዝግጅትን በመጀመር ረገድ የዘገየው ሀምበሪቾ በዝውውር መስኮቱ ከከፍተኛ ሊጉ እና ከፕሪምየር ሊጉ ወደ ዘጠኝ የሚጠጉ አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈርሞ የነበረ ሲሆን በዛሬው ዕለት ደግሞ ተጨማሪ ሦስት ተጫዋቾችን በመጨመር የአዳዲስ ፈራሚዎቹን ቁጥር አስራ ሁለት ስለ ማድረሱ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

ኤፍሬም ዘካሪያስ ሀምበሪቾን ተቀላቅሏል። የቀድሞው የመተሐራ ስኳር ፣ ኢትዮጵያ ቡና ፣ ሀዋሳ ከተማ እና ወልቂጤ ከተማ የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ወደ ቀድሞው ክለቡ አዳማ ዳግም በመመለስ በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ለክለቡ ፊርማውን አኑሮ ልምምድ ሲሠራ የነበረ ቢሆንም ከክለቡ ጋር በተፈጠረ የክፍያ አፈፃፀም ክፍተት ከደቂቃዎች በፊት በስምምነት ውሉን በማፍረስ ሀምበሪቾን ተቀላቅሏል።

ሌላኛው የክለቡ ፈራሚ ቁመታሙ የመሐል እና የመስመር ተከላካይ ቴዎድሮስ በቀለ ነው። በመቻል ፣ በአዳማ ከተማ ፣ ሀድያ ሆሳዕና እና ኢትዮጵያ ቡና ተጫውቶ ያሳለፈው ተከላካዩ በኢትዮጵያ መድን የተጠናቀቀውን ዓመት ያሳለፈ ሲሆን በክለቡ ቀሪ የአንድ ዓመት ውል እየቀረው ከሰሞኑ በስምምነት ከተለያየ በኋላ ወደ ሀምበሪቾ አምርቷል። በክለቡ ውስጥ ካለው አጥቂው ታናሽ ወንድሙ ዳግም በቀለ ጋር በአንድ ክለብ አብረው የሚጫወቱም ይሆናል።

ሌላኛው ፈራሚ በመሆን ወደ ክለቡ ያመራው ግብ ጠባቂው ደረጀ ዓለሙ ነው። በሰበታ ከተማ ፣ ዳሽን ቢራ ፣ አዲስ አበባ ከተማ ፣ ወልድያ ከተማ  ፣ ወላይታ ድቻ ፣ አዳማ ከተማ እና ድሬዳዋ ተጫውቶ ያሳለፈው ደረጀ ያለፈውን ዓመት በከፍተኛ ሊጉ ሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን ሲጫወት ቆይቶ በድጋሚ ወደ ፕሪምየር ሊግ የተመለሰበትን ዝውውር በሀምበሪቾ ፈፅሟል።