ሽረ እንዳሥላሴ በመቐለ አቀባበል እና የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶለታል

በከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ ባህርዳር ከተማን ተከትሎ በሁለተኛነት በማጠናቀቅ በመጨረሻ የመለያ ጨዋታ ጅማ አባ ቡናን 2-1 በማሸነፍ ወደ ፕሪምየር ሊግ መግባቱ ያረጋገጠው ሽረ እንዳሥላሴ መቐለ ከተማ ሲደርስ ደማቅ አቀባበል ሲደረግለት በርከት ያለ ሽልማትም ተበርክቶላቸዋል።

ክለቡ ወደ ፕሪምየር ሊግ መግባቱ ካረጋገጠ በኋላ ሽልማት በማበርከት ቀዳሚ የሆነው የትግራይ መልሶ ማቋቋም ድርጅት (ኤፈርት) አባል የሆነው ሱር ኮንስትራክሽን ሲሆን ለቡድኑ አሰልጣኛች እያንዳንዳቸው 75 ሺህ፣ ለቋሚ ተሰላፊዎች 50 ሺህ እና ለተቀሩት የቡድኑ ተጫዋቾች 25 ሺህ ሲያበረክት ለቡድኑ ለቀጣይ ዓመት በጀት የሚውል 10 ሚልዮን ብር ለግሷል። አንድ ለቡድኑ ማመላለሻ የሚውል አውቶቡስ ለመስጠትም ቃል ገብቷል።

የትግራይ ክልል መስተዳድር በበኩሉ 15 ሚልዮን ሲያበረክት በቀጣይ ዓመትም ቡድኑን መደገፍ እንደሚቀጥል ገልጿል። ከዚ በተጨማሪ የትግራይ ክልል ከ 3ቱ ነባር ክለቦች በተጨማሪ በቅርቡ መቀመጫው ወደ ትግራይ ክልል ላዞረው ደደቢትም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተገልጿል።