በታቀደው ልክ እየተጓዘ የማይገኘው አዳማ ከተማ ከሰሞኑ ተደጋጋሚ ስብሰባ በማድረግ ውሳኔዎችን አሳልፏል

በአሰልጣኝ ስዮም ከበደ እየተመራ ቡድኑ ከዚህ ቀደም ከሚያስመዘግቡት ውጤት በተሻለ በዋንጫ ፉክክር ውስጥ የሚቆይ ቡድን ለመስራት ጠንካራ ዝውውር ቢፈፅምም ሜዳ ላይ የሚመዘገበው ውጤት ያላስደሰተው የአዳማ ከተማ የበላይ ጠባቂ በአዳማ ራስ ሆቴል አስቸኳይ ስብሰባ አድርጎ አጠናቋል።
ከትናንት በስቲያ ከረፋድ ጀምሮ የቡድኑን ተጫዋቾች እና የአሰልጣኝ አባላትን በጋራ ጠርተው ያናገሩ ሲሆን በቡድኑ ችግር እና መፍትሔ ዙሪያ በሰፊው ሲወያዩ ቆይተዋል። በማስከተልም የተናጥል ውይይት በማድረግ ስብሰባው የቀጠለ ሲሆን ተጫዋቾችን ብቻ በመለየት ያናገው የክለቡ የበላይ ኃላፊ ተጫዋቾችም አሉ የሚሏቸውን ችግሮች እንደገለፁ ሰምተናል።
በማስከተል የቡድኑን አሰልጣኝ አባላትን ጠርተው ያናገሩት የክለቡ የቦርድ አመራሮች በወጥነት ቡድኑ መጓዝ ያልቻለበትን ምክንያት የአሰልጣኞቹ የቡድን አባላት ማብራሪያ አድምጧል። ከዚህ ቀደም ከነበሩ ስብሰባዎች ጠንከር ያለ እንደነበር በተሰማው ስብሰባ የሁለቱ አካላት ያቀረቡን ሀሳብ መነሻ በማድረግም ዛሬ ውሳኔ ለመስጠት ቀጠሮ ተይዞ ነበር።
ሶከር ኢትዮጵያ ከውስጥ ምንጮቿ አሁን እንዳገኘችው መረጃ ከሆነም አሰልጣኝ ስዮም ከበደ በአዳማ ከተማ አሰልጣኝነታቸው መሰናበታቸውን እርግጥ መሆኑን አውቀናል።
በጊዛዊነትም ምክትላቸው በመሆን ሲሰሩ የቆዮት አሰልጣኝ ዳዊት ታደለ እና ዳዊት ሀብታሙ ቡድኑን እንዲመሩ መሾማቸውንም አውቀናል።

