ዋልያዎቹ የቻን ማጣርያ ዝግጅታቸውን በድሬዳዋ ቀጥለዋል

የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን በ2018 በኬንያ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የቻን ማጣርያ ዝግጅቱን በድሬዳዋ ከተማ እያደረገ ይገኛል፡፡

በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የሚመራው የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን ከጅቡቲ አቻው ጋር ላለበት የመጀመርያ የማጣርያ ጨዋታ ይረዳው ዘንድ ለጅቡቲ ሞቃታማ አየር ተቀራራቢ የአየር ንብረት ወዳላት ድሬደዋ በማቅናት ካሳለፍነው ቅዳሜ ጀምሮ ማረፈያውን ሰመረት ሆቴል በማድረግ በቀን ሁለት ጊዜ ልምምዱን በመስራት ላይ ይገኛል ።

ዛሬ ማለዳ ላይ የመጀመርመርያ ልምምዱን አከናውኖ 10:00 ላይ በድሬደዋ ስታድየም ለአንድ ሰአት በቆየ ሁለተኛ ጊዜ ልምምዳቸው 16 ተጨዋቾች ሲሳተፉ ፣ የቦታ አጠባበቅ እና አሸፋፋን እንዲሁም በግማሽ ሜዳ ለሁለት ተከፍሎ መጫወት የልምምዳቸው አካል ነበር። በዛሬው ልምምድ ወቅት ግብ ጠባቂው ለአለም ብርሃኑ እና አጥቂው ምንይሉ ወንድሙ ተነጥለው ቀለል ያለ ልምምድ ይሰሩ እንደነበረ ለማወቅ ሲቻል የግራ መስመር ተከላካዩ አምሳሉ ጥላሁን በጠዋቱ ልምምድ ላይ ቢገኝም ረፋድ ላይ በነበረው ልምምድ በግል ጉዳይ ልምምድ ያልተገኘ ተጨዋች ነው።  ምክትል አሰልጣኙ ዘሪሁን ሸንገታ እና ስድስቱ የቅደስ ጊዮርጊስ ተጨዋቾች አስቻለው ታመነ ፣ ሳላዲን በርጌቾ ፣ ምንተስኖት አዳነ ፣ ናትናኤል ዘለቀ ፣ ባሀይሉ አሰፋ እና ሳላዲን ሰይድ  ክለባቸው የፊታችን እሁድ ላለበት የካፍ ቶታል የቻምፒየንስ ሊግ የምድብ የመጨረሻ ጨዋታ ምክንያት ከቡድኑ ጋር ያልተቀላቀሉ ተጨዋቾች ሲሆኑ ከቀናት በኋላ ከቡድኑ ጋር ይቀላቀላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከልምምዱ መጠናቀቅ በኋላ ለድሬደዋ መገናኛ ብዙሀን ጋዜጠኞች አስተያየታቸውን የሰጡት አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ከጋናው ሽንፈት አገግመው በጥሩ ተነሳሽነት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ ” እንደምታዩት አብዛኛዎቹ ተጨዋቾች ወጣቶች ናቸው፡፡ እግር ኳስ ነው ፤ ሽንፈቱም አልፏል፡፡ ስላለፈው ሳይሆን ስለ ወደ ፊቱ ነው የምንሰራው። በልጆቼም ዘንድ ጥሩ ተነሳሽነት ይታይባቸዋል፡፡ ” ያሉት አሰልጣኝ አሸናፊ ቀዳሚ ተመራጭ ግብ ጠባቂ የነበረው አቤል ማሞ መቀነስን ምክንያት እና ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች ቡድኑን አለመቀላቀልም ተናግረዋል፡፡ ” አቤል የቡድኑ ወሳኝ ተጨዋች አይደለም ፤ እንደማንኛውም ተጨዋች ነው። ወቅታዊ ብቃትን መሰረት ባደረገ ሁኔታ እሱን በሌላ ተተኪ ግብ ጠባቂ ለውጥ አድርገናል።”

” የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች ባለባቸው የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ ምክንያት አልተቀላቀሉም፡፡ እነሱ እስኪመጡ እኛ ተገቢውን ስራ እየሰራን እንገኛለን። በቅርብ ቀናት ውስጥ ከቡድኑ ጋር ተቀላቅለው ይጀምራሉ ብለን እንጠብቃለን፡፡”

አሰልጣኝ አሸናፊ በመጨረሻም ስለ ጅቡቲው ጨዋታ በሰጡት አስተያየት ለጨዋታው ዝቅተኛ ግምት እንደማይሰጡ ገልጸዋል፡፡

“የጅቡቲ ብሔራዊ ቡድን ደቡብ ሱዳንን ማሸነፉ ይታወሳል። ስለዚህ ጅቡቲን አሳንሰን አንመለከታትም፡፡ ብዙዎች ለጅቡቲ ያነሰ ግምት ይሰጣሉ ፤ እግር ኳስ ግን ይሄን አያስተምረንም፡፡ ስለዚህ ለጅቡቲ በከፍተኛ ሁኔታ ትኩረት ሰተን ነው የምንጫወተው፡፡”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *