ቻን 2018: ዋልያዎቹ ያለ በቂ ተጫዋቾች ሱዳንን ገጥመዋል

በ2018 በኬንያ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የቻን ውድድር የመጨረሻ ማጣርያ ጨዋታ በሀዋሳ ዓለም አቀፍ ስታድየም ከሱዳን ጋር የተጫወተው የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን ከመመራት ተነስቶ በአብዱራህማን ሙባረክ ጎል 1-1 በሆነ አቻ ውጤት አጠናቋል።

የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ እና ለቻን ማጣርያ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለን ዋና አሰልጣኝ አድርጎ ቅጥር ከፈፀመ አንስቶ ከነ በርካታ ችግሩ መቀጠሉን ተያይዞታል። ለአብነት ያህል ተጨዋቾች የሚመረጡበት እና የሚቀነሱበት ሁኔታ ፣ አማራጭ ተጨዋቾችን በስፋት መያዝ እየተቻለ ቁጥሩ አነስተኛ የሆነ ስብስብ በመያዝ መዘጋጀት ፣ የአሰልጣኙ ገና በሁለት ጨዋታ የመልቀቂያ ደብዳቤ ማስገባት እና በወቅቱ ስለ ቡድን አጠቃላይ እንቅስቃሴ ለሚዲያው ጋዜጣዊ መግለጫ አለመስጠት ፣ የፌዴሬሽኑ ጣልቃ ገብነት እና ሌሎች ችግሮች እየተፈራረቁበት ይገኛል።

ዛሬም የተከሰተው ሁኔታ የችግሩን ስፋት የሚያሳይ ነው። ብሔራዊ ቡድኑ ከሱዳን ጋር ለነበረው የቻን ማጣሪያ ጨዋታ 18 ተጨዋች ማስመዝገብ ሲገባው ያስመዘገበው 17 ተጨዋች ነበር። ምክንያቱ ደግሞ (ረቡዕ) ዘግይቶም ቢሆን ብሔራዊ ቡድኑን የተቀላቀለው ፍሬው ሰለሞን ፓስፖርቱ ጊዜ ያለፈበት በመሆኑ ትኩረት ሰጥቶ አስቀድሞ በፍጥነት ባለመታደሱ ነው። ታዲያ ይህ ጉዳይ አስቀድሞ መሰራት ሲገባው ባለመሰራቱ ለተፈጠረው ችግር ማነው ተጠያቂው?

ብሔራዊ ቡድኑ ከጅቡቲው ጨዋታ መልስ ለሱዳኑ ጨዋታ ዝግጅት ሲያደርግ የቆየው ከ20 በሚያንሱ ተጫዋቾች ሲሆን ተጨማሪ ተጫዋቾች ሲጠሩ የነበረውም በጉዳት እና ሌሎች ምክንያቶች ከስብስቡ ውጪ ሲሆኑ ነው፡፡ ይህ ጉዳይም በዛሬው ጨዋታ ላይ ዋጋ አስከፍሎት ለአንድ ጨዋታ የሚሆኑ 18 ተጫዋቾችን እንኳ መያዝ ሳይችል ሱዳንን ገጥሟል፡፡

ቡድኑ በዛሬው ጨዋታ የአማካይ ክፍሉ እጅግ ደካማ የነበረ ሲሆን ለአጥቂዎች የመጨረሻ ኳሶችን የሚያቀርብ አማካይ እጥረት እንደነበረበት ተስተውሏል፡፡ አሰልጣኝ አሸናፊም በተጠባባቂ ወንበር ላይ የአጥቂ አማካይ አለመያዛቸውን ተከትሎ በአንድ ጊዜ ሁለት የተከላካይ አማካይ ተጨዋቾችን ቀይረው ለማስገባት ተገደዋል፡፡ሌላው አግራሞት የሚያጭረው ነገር ደግሞ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በቀጣይ ሳምንት ከሱዳን ጋር ለሚኖረው ወሳኝ የመልስ ጨዋታ ቡድኑን ለማጠናከር ምንም አይነት ተጨማሪ ተጨዋቾች ከቡድኑ ጋር እንደማይቀላቅሉ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ መናገራቸው ነው።

በአጠቃላይ ብሔራዊ ቡድኑ በተረጋጋ ሁኔታ መቀጠል እንደሚገባው እየገለፅን ከቡድኑ ጋር ተያይዘው እየተፈጠሩ ያሉት መቋጫ የሌላቸው ችግሮች መፈታት ይገባቸዋል መልክታችን ነው ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *