ከፍተኛ ሊግ ለ | ኢትዮጵያ መድን መሪነቱን ሲረከብ ወልቂጤ ከተማ ነጥብ ጥሏል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ የሁለተኛ የውድድር ዘመን አጋማሽ እሁድ በተደረጉ ጨዋታዎች ሲጀምር ኢትዮጵያ መድን እና ሀላባ ከተማ አሸንፈዋል። ወልቂጤ ከተማ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

አሜድላ ሜዳ ላይ የካ ክፍለ ከተማ ከወልቂጤ ያደረጉት ጨዋታ 1-1 ሲጠናቀቅ ከፍተኛ ሁከት ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ተስተናዶበታል። በርካታ የወልቂጤ ከተማ ደጋፊ የተገኙበት ይህ ጨዋታ ይጀመራል ከተባለበት ከ30 ደቂቃዎች በኋላ ዘግይቶ የጀመረ ሲሆን በቂ የፀጥታ ኃይል አለመገኘቱ ለመዘግይቱ መክንያት ሆኗል።

የጨዋታው የመጀመሪያ ክፍለ ጊዜ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ታይቶበታል። ገና ከጅምሩ የወልቂጤን ጎል መፈተሽ የጀመሩት የካዎች ግብ ለማስቆጠር ብዙ ደቂቃ አላስፈለጋቸውም። 3ኛው ደቂቃ ላይ ማቲያስ ሹመቴ ከመሀል ሜዳ በረጅሙ የተሻገረለትን ኳስ በመቆጣጠር ከሳጥኑ ጫፍ የመታው ኳስ ወደ ግብነት በመለወጥ መሪ መሆን ችለዋል።

ከግቡ መቆጠር በኋላ ወልቂጤዎች የአቻነት ግብ ፍለጋ ተጭነው ለመጫወት የተሻለ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም ከመሐል ሜዳ የበላይነት በዘለለ የባለሜዳውን የተከላካይ ክፍል ሰብሮ ለመግባት ተቸግረው ተስተውለዋል። በ8ኛው እና 13ኛው ደቂቃ አዲሱ ፈራሚ ሰለሞን ጌታቸው ከርቀት መትቶ ወደ ውጪ የወጣባቸው ኳሶች በመጀመሪያው 15 ደቂቃዎች ውስጥ የተደረገ የግብ ሙከራ ነበሩ። በ26ኛው ደቂቃ አብዱልከሪም ወደፊት የጣለውን ኳስ አክዌር ግብ ጠባቂውን በማለፍ ወደግብነት ለወጠው ሲባል ግብ ጠባቂው ደርሶ ከግብ ሲያድነው በ36ኛው ደቂቃ ሰለሞን ጌታቸው ያሻገረውን ኳስ ከደደቢት በቅርቡ ክለቡን የተቀላቀለው አክዌር ቻሞ ተቆጣጥሮ ወደግብ አክርሮ የመታት ኳስ መረብ ላይ በማረፍ እንግዳውን ቡድን አቻ ማድረግ ችላለች።

ወልቂጤዎች ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር ያለሙ የጎል ሙከራዎችን በቀሪዎቹ የመጀመርያ አጋማሽ ደቂቃዎች አድረገዋል። አህመድ ሁሴን አቀብሎት አኩዌር ይዞት መግባት ሲችል ከርቀት አክርሮ የመታው እንዲሁም አህመድ ሁሴን በግራ መስመር ሁለት ተከላካዮችን በማለፍ የመታውና ደጠውጪ የወጣበት እንግዳውን ቡድን መሪ ሊያደርግ የሚችልበት አጋጣሚ ነበር። የመጀመርያው አጋማሽ በዚህ መልኩ ሲጠናቀቅ የሜዳው መስመር ቅርጹን የጠበቀ ባለመሆኑ የወልቂጤ አምበል ብስራት ገበየሁ ክስ አስይዟል።

እጅግ የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ በታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ረጃጅም ኳሶች የበዙበት ሆኖ አልፏል። በ51ኛው ደቂቃ ተመስገን ደረሰ ያሻማውን ኳስ አህመድ ሁሴን በግንባር ገጭቶ ግብ ጠባቂው ያዳነበት ኳስ የሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ግብ ሙከራ ነበር። ብስራት ገበየሁ በ63ኛው ደቂቃ ሰለሞን ጌታቸው ላይ በተሰራ ጥፋት ያገኘውን ቅጣት ምት በግቡ አናት ላይ የወጣችበት፣ በ68ኛው ደቂቃ አኩዌር ቻሞ አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ያዳነበት እንዲሁም በመጨረሻዎቹ ደቂቃቸች ቢንያም ጌታቸው በግንባር ገጭቶ ግብ ጠባቂው የመለሰበት የግብ ሙከራዎች ተጠቃሽ የወልቂጤ አጋጣሚዎች ነበሩ። የካዎች ማቲያስ ሹመቴ በግሉ በሚደርጋቸው ጥረት ታግዘው ሁለት ጊዜ የግብ ሙከራ ማድረግ ቢችሉም ግዙፉ ግብ ጠባቂ ቤሊንጋ በቀላሉ አድኖባቸዋል።

የጨዋታው መጠናቀቂያ ፊሽካ ከተሰማ በኋላ የወልቂጤ ደጋፊዎች ከየካዎች ግብ ጀርባ የወሰዱትን ኳስ ለማስመለስ የተደረገው ጥረት አቅጣጫውን ስቶ ከፌዴራል ፖሊስ እና ከአአ ፖሊስ አባላቶች ጋር ግጭቶች እስከመፍጠር የደረሰ ሲሆን በደጋፊዎች በኩል የድንጋይ ውርወራ፤ በፀጥታ ኃይሉ በኩል ደግሞ በአፀፋው በርካታ ደጋፊዎችን ለጉዳት የዳረገ እርምጃ ተስተውሏል። በዚህ አጋጣሚ ከደጋፊዎች ጋር ተመሳሳይ መለያ የለበሱት የወልቂጤ ተጫዋቾች የፖሊስ ዱላ ሰለባ የሆኑ ሲሆን በተለይም አምበሉ ብስራት ገበየሁ መሐል ሜዳ ላይ በቆመበት ያረፈበት ዱላ ከፍተኛ ጉዳት እንዳስከተለበት አስተውለናል።

ገና ከጅምሩ በቂ የፀጥታ ኃይል ሳይኖር ተጨማሪ ኃይል ይመጣል በሚል ሀሳብ የተጀመረው ጨዋታ ለብዙ የወልቂጤ ደጋፊዎች እንዲሁም ለፀጥታ ኃይል አባላት የመፈንከት እና የመጎዳት አጋጣሚ በር ከፍቶ አልፏል። የፌዴሬሽኑ የፀጥታ ኮሚቴ ኃላፊዎች ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያታቸውን እንዲሰጡን ብንደውልም ሳይሳካ የቀረ ሲሆን የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኃይለሱስ ፍስሀ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት የፀጥታ ዘርፉ ለየክልሎቹ በኃላፊነት ሲሰጥ ለአዲስ አበባ ይህ ኃላፊነት እንዳልተሰጠ በመጠቆም ጉዳዩ የሚመለከተው የብሔራዊ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የፀጥታ ኮሚቴ እንደሆነ ገልፀዋል።

መድን ሜዳ ላይ አስቀድሞ ሊደረግ መርሐ ግብር ወጥቶለት የነበረው የኢትዮጵያ መድን እና ነገሌ አርሲ ጨዋታ ወደ አዲስ አበባ ስታድየም ተዘዋውሮ ሲከናወን መድን 4-1 በማሸነፍ መሪነቱን ከወልቂጤ ተረክቧል። መድኖች በ30ኛው ደቂቃ ኤርምያስ ዳንኤል ግብ አስቆጥረው መሪ መሆን ቢችሉም እንግዳው ቡድን በ44ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረው ወደ እረፍት አምርተዋል። ከእረፍት በኋላ መድን አይሎ በመቅረብ አብዱለጢፍ ሙራድ በ52ኛው እና 70ኛው ደቂቃ ሁለት ጎሎችን ሲያስቆጥር ሰለሞን ወዴሳ በ59ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው መድን 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ሀላባ ላይ ሀላባ ከተማ ከናሽናል ሴሜንት ያደረጉት ጨዋታ በሀላባ አሸናፊነት ተጠናቋል። በ20ኛው ደቂቃ አቡበከር ወንድሙ ግብ አስቆጥረው መሪ ቢሆንም ናሽናል ሲሜንት በቢንያም ግብ አቻ መሆን ችሎም ነበር። ሀላባዎች ቴዎድሮስ አሙ በ76ኛው ደቂቃ ላይ እንዲሁም ልመነህ ታደሰ በ84ኛው ደቂቃ ላይ ባገቧቸው ተጨማሪ ሁለት ግቦች 3-1 በማሸነፍ በአዲሱ አሰልጣኛቸው ካሊድ መሐመድ መሪነት ሁለተኛውን ዙር በድል መጀመር ችለዋል።© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

error: