አሰልጣኝ ካሳዬ ስለአማራጭ የጨዋታ እቅድ እና ተጫዋቾቻቸው ስለሚገኙበት ጫና ይናገራሉ

በ13ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኢትዮጵያ ቡና በአሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛው በሚመሩት ወልቂጤ ከተማዎች እጅጉን ተፈትኖ አንድ አቻ ተለያይቷል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ዘለግ ያለ ድህረ ጨዋታ ቃለምልልስ ያደረጉት አሰልጣኙ ከጋዜጠኞች ስለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። በአሰልጣኞች አስተያየት ዘገባችን ላይ ያላካተትናቸው አንኳር ሀሳቦችንም በተከታይ መልኩ አቅርበናቸዋል።

ቡድኑ በሜዳው የላይኛው ክፍል ጫና ሲደርስበት በጣም እየተቸገረ ነው። ይህን ለመቅረፍ አማራጭ የጨዋታ እቅድ ያስፈልግ ከሆነ?

“ሁሉም ቡድኖች በዛ መልክ እየመጡ አይደለም ፤ ለምሳሌ ወልቂጤ በመጀመሪያውና በሁለተኛው አጋማሽ የተለያየ አቀራረብ ነበራቸው። በተጋጣሚ ቡድኖች ጫና ውስጥ ለመውጣት የሞከርንበት መንገድ በረከት አህመድን ለማግኘት የሚሄድበት መንገድ ነበር ይህም የቅብብል ስህተት ነው እንጂ ጥለዛ አልነበረም። ሁለተኛ አማራጭ ለሚባለው ነገር የሰው ለውጥ ያስፈልጋል፤ ሁለተኛ እቅድ ካስፈለገ ተጫዋቾችን መለወጥ ያስፈልጋል። ግን ለማፈን በሚደረገው ሒደት ውስጥ ለመውጣት በምናረገው ሂደት ውስጥ የቅብብል ስህተቶች ይኖራሉ ፤ እነዛን ደግሞ መታገስ ያስፈልጋል።

” በቅድሚያ ለመጀመር ስንሞክር ግብ ክልላችን ውስጥ ገብተው እንዳያፍኑን ህጉም ስለሚከለክል ማድረግ አይችሉም፤ ቢያንስ ለመጀመር የምትሆን 16.50 አለች። ሒደቱን ለማስቀጠል ግን ስህተቶች ይኖራሉ። እነዛን ስህተቶች ደግሞ መታገስ ያስፈልጋል። ሌላው ምናልባት አንዳንዴ የሚለጉ ኳሶች አስፈላጊ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ምክንያቱም ተጋጣሚ የቆመበትን ቅርፅ ለማጥፋት እድሉም ከተገኘ ተጠቃሚ እንሆናለን። ግን በዋናነት ቅርፃቸውን ለማጥፋት ኳሶቹ ይጠቅማሉ። በተደጋጋሚ ልጆቹ ያንን ያደርጉ የነበሩት የመጀመሪያውን ሒደት መታገስ ስላልተቻለ ነው።”

የውጤት መጥፋቱ ተጫዋቾቹ ላይ ስለፈጠረው ጫና

“በትክክል ልጆቹ ላይ የሚፈጥረው ጫና ይኖራል ፤ የነጥብ መራራቅ ስላለ እንድንጠጋ ይፈለጋል። እንድንጠጋ የሚፈለገው ደግሞ ጎል በማግባት ነው፤ ጎል እንድናገባ ደግሞ ሒደቱን የመታገስ ነገር የለም። ቶሎ ቶሎ ተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ ኳሶችን ማየት ይፈለጋል። ስለዚህ ይህ ነገር ልጆቹን ጫና ውስጥ ይከታቸዋል። የመጨረሻዎቹ 25 ደቂቃዎች ላይ ጥድፊያ ነበር፤ ጫና መፈጠሩ የግድ ነው። አንደኛ ቡና ትልቅ ቡድን ነው ሁለተኛ ልጆቹ ከተለያየ ቦታ ነው የመጡት። በዚህ አይነት ጫና ውስጥ ተጫውተው አያውቁም። እርግጥ ልጆቹ ከጫና እንዲወጡና በሚፈለገው ነገር እንዲቆዩ የማድረግ የኛ ግዴታ ቢሆንም ጫና መፍጠሩ ግን አይቀርም።”

በእስካሁኑ የሊጉ ቆይታው ቡድኑ ላይ ስለተመለከተው ክፍተት

” የቡድኑ ክፍተት ሳይሆን አስቸጋሪ የሜዳ ክፍሎች አሉ፤ እነዛ አስቸጋሪ የሜዳ ክፍሎች እንደተጋጣሚ አቀራረብ የሚወሰኑ ናቸው። ተጋጣሚ አንተ ሜዳ ላይ መጥቶ የሚያፍንህ ከሆነ ያ አስቸጋሪ የሜዳ ክፍል ሊሆን ይችላል፤ ተጋጣሚ በራሱ ሜዳ ተሰብስቦ የሚጫወት ከሆነ ደግሞ ያ አስቸጋሪ የሜዳ ክፍል ሊሆን ይችላል። ስለዚህ እንደተጋጣሚ አመጣጥ እነዛን አስቸጋሪ የሜዳ ክፍሎች ለማለፍ የራሳችን ሥራ ጠንቅቀን መስራት ይኖርብናል።”

© ሶከር ኢትዮጵያ