“ሌስተር ሲቲ ለመግባት የነበረኝ ዕድል በአንድ ሰው ምክንያት ነበር የተጨናገፈብኝ ” ስንታየሁ ጌታቸው (ቆጬ)

ባለፉት ቀናቶች የስንታየው ጌታቸው ቆጬ የእግርኳስ ዘመንን በተለያዩ አምዶች መቃኘታችን ይታወሳል። በዛሬው መሰናዷችን ደግሞ ወደ ሌስተር ሲቲ ለማምራት ያገኘው ዕድል ስለ ተጨናገፈበትን ገጠመኝ ከራሱ አንደበት ይህን አጋርቶናል።

“ከሃገር የወጣሁበት ምክንያት የተለያዩ ቢሆኑም በዋናነት ግን በሰዓቱ በነበረኝ የፍቅር ህይወት ነው። ልክ እንግሊዝ እንደመጣሁ ሌስተር ከተማ ውስጥ ኢንተርናሽናል በሚባል ሆቴል ውስጥ አረፍኩ። በሆቴሉ ውስጥ ተቀምጬ ሳለው የሌስተር ሲቲ የእግርኳስ ቡድን ወሬ ሰማሁ። ከዛ ሆቴሉ ውስጥ ባሉ አንዳንድ ሠዎች ምክንያት ክለቡ አካባቢ ልደርስ ቻልኩ። ወደ ክለቡ ከቀረብኩ በኋላ ልክ እንደ ምርጫ አይነት ጨዋታ በዋናው የሌስተር ስታዲየም (ኪንግ ፓወር) አደረግኩ። ከኢትዮጵያ እንደመጣሁ ሰለሆነ እና በግሌም አንዳንድ ልምምዶችን ስሰራ ስለነበር አልከበደኝም ነበር። በጨዋታውም በጣም ጥሩ ተጫወትኩ። እንደውም የግቡ ብረት የመለሰብኝ ኳስ ሁሉ አስታውሳለው። የሚገርምህ ከጨዋታው በኋላ ሌስተሮች የሰጡኝ ሜዳልያ ሁሉ ነበር። ወደ ሆቴሌ በመኪና አድርሰውኝ እንደሚፈልጉኝ ነገሩኝ። በሌላም ቀን እኔ ሆቴል እያለሁ በተለያየ ጊዜ እየመጡ ይጠይቁኝ ጀመር። በአስቸኳይ ከቀድሞ ክለብህ እና ሀገር ፌደሬሽን መልቀቂያ አምጣ አሉኝ። እኔም ሀገር ቤት በነበሩኝ ጓደኞች (ጌታ ዘሩ እና ተስፋዬ ዲጋጋ) መልቀቂያ ለማስላክ ተንቀሳቀስኩ። ጌታ ዘሩም ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፅህፈት ቤት ሄዶ መልቀቂያ እንዲሰጡኝ ጠየቀ። በወቅቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት አቶ ሠለሞን የተባሉ ግለሰብ ነበሩ። ጌታ ዘሩም እኚን ግለሰብ መልቀቂያውን ሲጠይቅ በጣም አስገራሚ እና አሳፋሪ መልስ ነው የሰጧቸው። ‘እኛ መልቀቂያ አንሰጥም። ስንታየሁ ሲሄድ ማሊያ ይዞ ሄዷል’ የሚል መልስ ነበር የሰጡዋቸው።

“እኔ ለጊዮርጊስ ያደረግኩት ነገር ይታወቃል። ደምቻለው፣ ቆስያለው፣ ከእነ ህመሜ ለክለቤ ባለኝ ፍቅር መስዋዕትነት ከፍያለው። ክለቡንም ጠልቼ አይደለም የለቀኩት። እርግጥ ስለቅ ከቡና ጋር የነበረን ጨዋታ ላይ አልተሰለፍኩም ነበር። ይህንንም አንዳንድ ሠዎች ይዘው ነገሩን ለማባባስ እና ለማጋነን ሞከሩ። እውነት ለመናገር ግን ” ማሊያ ወስዷል” ያሉት ነገር ሐሰት ነው። እኔ ምንም ማሊያ አልወሰድኩም። አሁን እራሱ የቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ ማሊያ ነው ያለኝ። እሱንም አንድ ጓደኛዬ በቅርቡ እንደ ማስታወሻ የሰጠኝ ነው። ከብሔራዊ ቡድኑ ግን መልቀቂያው ተልኮልኝ ነበር። ከዛ ምንም ማድረግ ስለማልችል የደረሰኝን የብሔራዊ ቡድን ወረቀት ብቻ ለሌስተር እግርኳስ ክለብ አስገባሁ። እነሱም ሙሉ ወረቀቴን ያመጣሁ መስሏቸው ደስተኛ ሆነው ነበር። ነገር ግን ይህ ከብሔራዊ ቡድን ብቻ የመጣው ወረቀት በቂ እንዳልሆነ እና የግድ ከቀድሞ ክለብ መልቀቂያ እንዳመጣ ነገሩኝ። ደግሞም በሰዓቱ የመኖሪያ ፈቃድም ስላልነበረኝ ትንሽ ነገሩ ከበድ አለ። ግን መልቀቂያውን ከጊዮርጊስ ባመጣ ኖሮ የመኖሪያ ፈቃዴን እራሱ እነሱ ሊያስወጡልኝ ነበር። ነገር ግን በአቶ ሠለሞን ምክንያት ሌስተር ልገባ የነበርኩት ልጅ ሳይሳካልኝ ቀረ። ሌስተሮች ቢቀበሉኝም መልቀቂያ ባለመውሰዴ ሁሉ ነገር ከሸፈ። ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው ደግሞ አቶ ሠለሞን ናቸው። ጊዮርጊስ ውስጥ ያሉት ሁሉም ሰዎች እንደሚወዱኝ እና እንዲሳካልኝ እንደሚፈልጉ አውቃለሁ። ነገር ግን አንዳንድ ሰዎች አሉ በእግርኳሱ እና በሰው ህይወት ላይ እየቀለዱ የሚኖሩ። የሆነው ሆኖ ሳይሳካ ቀርቷል። ከሌስተር በተጨማሪ ሌሎች ክለቦች ውስጥም ለመግባት ሙከራ አድርጌ ነበር። ነገር ግን ክለቦቹ ቢወዱኝም ከመልቀቂያ እና ከመኖሪያ ፍቃድ ጋር በተገናኘ ሳይሳካ ቀርቷል። ከዚህ በኋላ እግርኳሱን ለማቆም ተገደድኩኝ።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ

error: