በአራት ነጥቦች የሚበላለጡት ዐፄዎቹ እና ነብሮቹ የሚያደርጉት ጨዋታ 9:00 ይጀመራል።
ቡድኑ በደረጃ ሰንጠረዡ እንዲመነደግ ካስቻሉት ሦስት ተከታታይ ድሎች በኋላ በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ሽንፈት ያስተናገደው ፋሲል ከነማ በሰላሣ ሦስት ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ዐፄዎቹ በደረጃ ሰንጠረዡ አካፋይ ላይ ቢቀመጡም በነጥብ ረገድ ስናየው ያሉበት ደረጃ አሁንም አስተማማኝ አይደለም፤ በ15ኛ ደረጃ ላይ ወራጅ ቀጠናው ላይ ካለው ሀዋሳ ከተማ ያላቸው የነጥብ ልዩነትም ስድስት ብቻ ነው። ይህንን ተከትሎ በቀረው የውድድር ጊዜ ቅርቃር ውስጥ ላለመግባት ዳግም ወደ ድል መንገድ መመለስ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። ይህ እንዲሆንም የቀደመው የማጥቃት አጨዋወቱ ጥንካሬ መመለስ ይኖርባቸዋል፤ ከቅርብ ሳምንታት በፊት አስፈሪ የነበረው እና በሦስት ጨዋታዎች ስምስት ግቦችን ያዘነበው የፊት መስመሩ ከቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ በኋላ ግቦችን እያስቆጠረ አለመሆኑ ከነገው ጨዋታ በፊት መሻሻል የሚገባው የቡድኑ ደካማ ጎን ሲሆን በነገው ጨዋታ የተጠቀሰውን ድክመት አርሞ መግባትም ቡድኑን ወደ አሸናፊነት መንገድ ሊመልሰው ይችላል።
ወላይታ ድቻን ሦስት ለአንድ በማሸነፍ የ2ኛው ዙር የመጀመርያ ድላቸውን ያስመዘገቡት ሀድያ ሆሳዕናዎች በሰላሣ ሰባት ነጥቦች 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
በአንድ ወቅት ለስድስት የጨዋታ ሳምንታት ተከታታይ ድሎች አስመዝቦ ሊጉን እስከመምራት ደረጃ ደርሶ የነበረው ሀድያ ሆሳዕና ከነበረው እጅግ ውጤታማ ጉዞ አሽቆልቁሏል። በ16ኛው ሳምንት ከብዙዎች ግምት ውጭ በወልዋሎ ሽንፈት ካስተናገደ ጀምሮ በብዙ ረገድ የተዳከመው ቡድኑ ከመጨረሻው ጨዋታ በፊት በተከናወኑ አስር ጨዋታዎች ያስመዘገባቸው ውጤቶች ከዋንጫ ፉክክሩ በእጅጉ ያራቀው ሲሆን ነገ የመጨረሻ ሳምንት ጣፋጭ ድሉ ማስቀጠል የሚችል ከሆነ ግን ደረጃውን የሚያሻሽልበት ዕድል አለ። ወላይታ ድቻን ሦስት ለአንድ ባሸነፉበት ጨዋታ ውጤታማ የማጥቃት አጨዋወት የነበራቸው ነብሮቹ በዕለቱ ከረዥም ጊዜያት በኋላ በቡድኑ የተስተዋለው ስኬታማ የመልሶ ማጥቃት በነገው ዕለት መቀጠል የሚገባው አወንታዊ ጎን ነው። በ2ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው ባህርዳር ከተማ በሦስት ነጥብ ርቀት ላይ የሚገኘው የነብሮቹ ስብስብ በሰንጠረዡ የላይኛው ክፍል ላይ ባለው የነጥብ መቀራረብ መነሻነት ደረጃውን የሚያሻሽልበት ዕድል አሁንም አለ፤ ሆኖም በውጤት ረገድም ይሁን በሜዳ ላይ እንቅስቃሴው የሚታየው የወጥነት ችግር መቀረፍ የሚገባው የቡድኑ ድክመት ነው።
በፋሲል ከነማ በኩል እዮብ ማቲያስ ፣ ሀብታሙ ተከስተ እና ኪሩቤል ዳኜ በጉዳት በነገው ጨዋታ ላይ አይኖሩም። በነብሮቹ በኩል መለሰ ሚሻሞ ለህክምና ወደ ውጭ ሀገር የሚሄድ መሆኑን ተከትሎ ከዚህ ዓመት ውድድር ውጭ ሆኗል፤ በጉዳት የከረመው ጫላ ተሺታም አሁንም በህክምና ላይ ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪ ጉዳት ላይ የሰነበቱት አንበሉ ሄኖክ አርፊጮ እና በረከት ወንድሙ ወደ መደበኛ ልምምድ የተመለሱ ቢሆንም ለነገው ጨዋታ የማይርሱ ይሆናል። ግብ ጠባቂው ያሬድ በቀለም በቅጣት ምክንያት የነገው ጨዋታ የሚያመልጠው ሌላው ተጫዋች ነው። በጉዳት ምክንያት ባለፉት በጨዋታዎች ያልነበሩት ሰመረ ሀፍታይ እና ቃልአብ ውብሸት ጨምሮ የተቀረቱት የቡድኑ አባላት ግን ለነገው ጨዋታ ዝግጁ መሆናቸውን ታውቋል።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ9 ጊዜያት ተገናኝተው 4 ጨዋታዎች በአቻ ተጠናቀው ፋሲል ከነማ 4 ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ 1 ጊዜ አሸንፈዋል። በጨዋታዎቹም ዐፄዎቹ 12 ነብሮቹ ደግሞ 8 ጎሎችን ማስቆጠር ችለዋል