ወልዋሎን ለመቀላቀል ተስማምቶ የነበረው ተጫዋች ወደ መቐለ 70 እንደርታ ለማምራት ተስማምቶ ወደ መቐለ ከተማ ጉዞ ጀምሯል።
በዝውውር መስኮቱ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ላይ ከሚገኙ ክለቦች የሚጠቀሱት መቐለ 70 እንደርታዎች ቡድናቸውን መጠናከር ተያይዘውታል። ከዚህ ቀደም ሱሌይማን ሐሚድ፣ መሐሪ አመሀ፣ አብዲ ዋበላ፣ አሰጋኸኝ ጴጥሮስ፣ ብርሃኑ አዳሙ፣ ጊት ጋትኮች እና ፍፁም ዓለሙን ለማስፈረም ተስማምተው የአራት ነባር ተጫዋቾች ውል ለማራዘም የተስማሙት መቐለ 70 እንደርታዎች አሁን ደግሞ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ወልዋሎን ለመቀላቀል ተስማምቶ የነበረው ፍሬዘር ካሳን ለማስፈረም ተስማምተዋል።
ፍሬዘር ካሳ ባለፉት ሁለት ዓመታት በባህር ዳር ከተማ የመከላከል ጥንካሬ ጉልህ ድርሻ ከተወጡ ተጫዋቾች አንዱ ሲሆን በተጠናቀቀው የውድድር ዓመትም በ28 ጨዋታዎች ተሳትፎ 2431′ ደቂቃዎች ቡድኑን ማገልገል ችሏል። በቅዱስ ጊዮርጊስ ታዳጊ እና ዋናው ቡድን፣ ድሬደዋ ከተማ፣ ሃዲያ ሆሳዕና፣ ባህር ዳር ከተማ እንዲሁም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን መጫወት የቻለው ተከላካዩ በአሁኑ ሰዓት የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ለመቀላቀል ወደ መቐለ ከተማ ጉዞ የጀመረ ሲሆን በነገው ዕለት ልምምድ ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል።