አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ አቡበከር ኑራ ጉዳት ማስተናገዱን ተከትሎ በምትኩ አንድ ግብ ጠባቂ ጠርተዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ ማጣርያ ከጊኒ ቢሳው እና ቡርኪና ፋሶ ጋር ለሚያደርጋቸው የመጨረሻ የምድብ ጨዋታዎች ዝግጅት አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ባልተለመደ ሁኔታ ለ20 ተጫዋች ጥሪ ማድረጋቸው ይታወሳል። ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች ዛሬ በጁፒተር ሆቴል ተገኝተው የሚሳባሰቡ ሲሆን ዝግጅታቸውን ነገ እንደሚጀምሩ ይጠበቃል።
ሆኖም ጥሪ ከተደረገላቸው ተጫዋቾች መካከል የወቅቱ የሊጉ ኮከብ ግብ ጠባቂ አቡበከር ኑራ ባጋጠመው ከበድ ያለ ጉዳት ለሳምንታት ከሜዳ እንደሚርቅ እና ለሀገሩም ሆነ ለብሔራዊ ቡድን ለቀጣዮቹ ሳምንታት አገልግሎት እንደማይሰጥ ጠቁመን ነበር።
አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪም ማምሻውን በአቡበከር ቦታ ለድሬዳዋ ከተማ የግብ ዘብ ፍሬው ጌታሁን ጥሪ ማድረጋቸውን እና ፍሬው ዛሬ አመሻሽ ከድሬዳዋ በመነሳት ብሔራዊ ቡድኑን እንደሚቀላቀል አረጋግጠናል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጊኒ ቢሳውን በሩዋንዳው አማሆሮ ስታዲየም መስከረም 28 ቀን ሲያስተናግድ ከቡርኪናፋሶ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ዋጋዱጉ ላይ ጥቅምት 2 ቀን ይከናወናል።