በአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ የሚመሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ግብ ጠባቂ ለማስፈረም ከስምምነት ደርሰዋል።
በዝውውር መስኮቱ በረከት ወልደዮሐንስ፣ ቤዛ መድህን፣ ሀሰን ሑሴን እና ሀቢብ ጃለቶን አስፈርሞ የስምንት ነባር ተጫዋቾች ውል ያራዘመው ኢትዮ ኤሌክትሪክ አሁን ደግሞ ግብ ጠባቂ ለማስፈረም ተስማምቷል። ቡድኑን ለመቀላቀል የተስማማው ተጫዋች ደግሞ የቶጎ ዜግነት ያለው ግብ ጠባቂው ዮሱፍ ሞሮይ ነው።
በቅርብ በተከናወኑ የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎች ላይ በቶጎ ብሔራዊ ቡድን ስብስብ ውስጥ የነበረው ይህ የ24 ዓመት ግብ ጠባቂ ላለፉት ሁለት የውድድር ዓመታት በሀገሩ ክለብ ጎሚዶ ቆይታ የነበረው ሲሆን ከዛ በፊትም በኮንጎው ሴንት ኤሎይ ሉፖፖ፣ ‘Future Stars Agoè’ ፣ ‘Jeunesse Club d’Agoè-Nyivé’ ፣ Dynamic Togolais Lomé’ መጫወት የቻለ ሲሆን አሁን ደግሞ በአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ለሚሰለጥነው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ለመፈረም ከስምምነት ደርሷል። የግብ ዘቡም አዲስ አበባ የገባ ሲሆን የመጀመርያ ልምምዱን ከቡድኑ ጋር ትናንት መሥራት መጀመሩን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።