ኢትዮጵያ ቡናዎች ዩጋንዳዊውን አጥቂ ለማስፈረም ከስምምነት ደርሰዋል።
በአሰልጣኝ አብይ ካሳሁን የሚመሩት እና በዝውውር መስኮቱ በረከት ብርሀነ፣ ዘላለም አባቴ፣ እንደሻው እሸቴ፣ ፉአድ ኢብራሂምን እና አቡበከር አዳሙን ያስፈረሙት ኢትዮጵያ ቡናዎች አሁን ደግሞ ከሳምንታት በፊት የኬንያውን ክለብ ጎር ማህያ ለመቀላቀል ከስምምነት ደርሶ የነበረውን ዩጋንዳዊው አጥቂ መሓመድ ሻባን ጃጋሶንን ለማስፈረም ተስማምተዋል።
በክረምቱ የዝውውር መስኮት በርከት ካሉ ክለቦች ጋር ስሙ ሲያያዝ ከቆየ በኋላ ከአራት ሳምንታት በፊት የኬንያውን ክለብ ጎር ማህያ ለመቀላቀል ተስማምቶ የነበረው ተጫዋቹ ከዚህ ቀደም በአሳዳጊ ክለቡ ኦንዱፓራካ፣ ራጃ ካዛብላንካ፣ ቫይፐርስ፣ ‘Kcca’ እንዲሁም በሊብያዎቹ አልሂላል እና አል አንዋር መጫወት የቻለ ሲሆን በተለያዩ የዕድሜ እርከኖችም የሀገሩ ዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድንን ወክሎ ተጫውቷል። በዓለም ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎች ላይ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ሁለት ግቦችን ያስቆጠረው አጥቂው ዛሬ አመሻሽ ኢትዮጵያ ይገባል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ነገ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋች ለመሆን በይፋ ፌርማውን ያኖራል።