ሰሞነኛ የመነጋገሪያ ጉዳይ የነበረው የሲዳማ ቡናው ግብ ጠባቂ ኢማኑኤል ካል ወደ ሀገሩ መሄዱ ተሰማ።

ከጨዋታ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ ፉፋ (የዩጋንዳ እግርኳስ ፌዴሬሽን) የመጨረሻ ውሳኔ እስኪተላለፍ ድረስ ከማንኛውም እግርኳሳዊ እንቅስቃሴዎች እንዲታገድ ውሳኔ የተደረሰበት የሲዳማው የግብ ዘብ ኢማኑኤል ካል ወደ ሀገሩ መጓዙን አውቀናል።
ከትናንት በስትያ ወደ ሀገሩ ያቀናው የግብ ዘቡ በዋናነት የተወሰነበትን ማንኛውንም እግርኳሳዊ እንቅስቃሴ እንዳያደርግ የተላለፈበትን ዕግድ ይግባኝ ለመጠየቅ መሆኑን የሰማን ሲሆን ከሲዳማ ቡና ጋር ያለውን ውል አቋርጦ ወደ ሀገሩ ሄዷል።
ሲዳማ ቡና ከዚህ በኋላ የኢማኑኤልን ግልጋሎት የማያገኝ መሆኑን ተከትሎ ቀሪዎቹን የሊጉን አስራ አራት ሳምንታትን ግብ ጠባቂዎቹ መስፍን ሙዜ እና አላዛር መርኔ ኃላፊነቱን የሚወጡ ይሆናል።
ሲዳማ ቡና በአርባ አምስት ነጥብ ከተከታዩ ሀዋሳ ከተማ በአምስት ነጥብ ርቆ ሊጉን በቀዳሚነት እየመራ መሆኑ ይታወቃል።

