አፍሪካ፡ የቻምፒየንስ ሊግ የምድብ ጨዋታዎች ዛሬ ይጀምራሉ

የ2016 ኦሬንጅ ቻምፒየንስ ሊግ ዛሬ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይጀመራል፡፡ ዛሬ ሶስት ጨዋታዎች ሲደረጉ በምድብ አንድ የዛምቢያው ዜስኮ ዩናይትድ የካይሮውን ሃያል አል አሃሊን እንዲሁም አሴክ ሚሞሳስ ዋይዳድ ካዛብላንካን ያስተናግዳሉ፡፡ በምድብ ሁለት ብቸኛ ጨዋታ የአልጄሪያው ሴቲፍ ማሜሎዲ ሰንዳውንስን ይገጥማል፡፡

በውድድር ዓመቱ የዛምቢያ ሊግ ጥሩ ደረጃ ላይ የሚገኘው ዜስኮ ዩናይትድ ከ2009 በኃላ ለመጀመሪያ ግዜ ወደ ቻምፒየንስ ሊጉ ምድብ ሲመለስ የስምንት ግዜ አሸናፊው አል አሃሊ ደግሞ ከሁለት ዓመታት በኃላ ወደ ቻምፒየንስ ሊጉ ተመልሷል፡፡ ዜስኮ በጨዋታው የኬንያዊውን ኢንተርናሽናል ጄሲ ጃክሰን ዌሬን ግልጋሎት አያገኘም፡፡ ዌሬ ዜስኮን በውድድሩ ዓመቱ መጀመሪያ ላይ ከተቀላቀለ በኃላ የክለቡ ወሳኝ ተጫዋች ለመሆን ግዜ አልፈጀበትም፡፡ አል አሃሊ ከማሊክ ኤቮና ጉዳት በቀር የከፈ የተጫዋች ጉዳት የለበትም፡፡ የፊት መስመሩን አምር ገማል ወይም ጆን አንቲው ይመሩታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በምድቡ ሌላ ጨዋታ የሞሮኮ ቦቶላ የሊግ ክብሩን ለመዲናዋ ክለብ ፉስ ራባት አሳልፎ የሰጠው ዋይዳድ ካዛብላካ በአሴክ ሚሞሳስ ይፈተናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የኮትዲቯሩ ክለብ በሚሊኒየሙ መጀመሪያ ላይ የነበረው አስፈሪነቱ አሁን ላይ ባይኖርም በሜዳው የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች የማሸነፍ ጥንካሬ አለው፡፡

በምድብ ሁለት ብቸኛ ጨዋታ በአልጄሪያ ሊግ ሞቢሊስ ክብሩን በዩኤስኤም አልጀር የተነጠቀው ሴቲፍ ማሜሎዲ ሰንዳውንስን ይገጥማል፡፡ ከሻምፒዮኑ በ14 ነጥቦች ርቆ 5ኛ በመሆን ሊጉነ የጨረሰው ሴቲፍ ከዓመት ወደ ዓመት ማሽቆልቆልን አሳይቷል፡፡ በፒትሶ ሞሴሜኔ የሚሰለጥነው ሰንዳውንስ የደቡብ አፍሪካ አብሳ ፕሪምየርሺፕ ዋንጫን ያነሳ ሲሆን የዲ.ሪ. ኮንጎው ቪታ ክለብ ያልተገባ ተጫዋች በማሰለፉ ምክንያት ዳግም ወደ ቻምፒየንስ ሊጉ ምድብ ሊመለስ ችሏል፡፡

 

ቅዳሜ ሰኔ 11/2008

15፡30 – ዜስኮ ዩናይትድ (ዛምቢያ) ከ አል አሃሊ (ግብፅ) (ሊቪ ማዋናዋሳ ስታዲየም)

15፡30 – አሴክ ሚሞሳስ (ኮትዲቯር) ከ ዋይዳድ አትሌቲክ ክለብ (ሞሮኮ) (ስታደ ሮበርት ቻምፕሮ)

22፡15 – ኢኤስ ሲቲፍ (አልጄሪያ) ከ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ (ደቡብ አፍሪካ) (ስታደ ሜይ 8 1945)

ዕሁድ ሰኔ 12/ 2008

16፡00 – ኢኒምባ ኢንተርናሽናል (ናይጄሪያ) ከ ዛማሌክ (ፖርት ሃርኮት ስታዲየም)

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *