​የኢትዮዽያ ቡና ስፖርት ክለብ የደጋፊዎች ማህበር መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ተካሄደ

የኢትዮዽያ ቡና ስፖርት ክለብ የደጋፊዎች ማኀበር መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ እና የ2 አመት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ዛሬ ከ04:00 ጀምሮ በአምባሳደር አዳራሽ ተካሂዷል፡፡
የክለቡ የቦርድ ተወካይ ፣ የደጋፊዎች ማህበር ሰብሳቢዎች እንዲሁም ደጋፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙበት ጉባኤ የተጀመረው በ2009 ከዚህ አለም በሞት ለተለዩ የክለቡ የልብ ደጋፊዎች የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማሰብ ነበር፡፡

ጉባኤውን በንግግር የጀመሩት አቶ ክፍሌ አማረ ካለው የጊዜ እጥረት አንፃር ጠቅለል ያለ የ2 አመት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ሲያቀርቡ ‹‹ በስፖርታዊ ጨዋነት ዙርያ ያለፉት ሁለት አመታት ለደጋፊዎቻችን ጥሩ ጊዜ አልነበረም፡፡ በዚህም ምክንያት ያለፉትን ሁለት አመታት የልማት ስራዎችን ሰርተናል ማለት አይቻልም፡፡ ያም ቢሆን በተወሰነ መልኩ ባለን ውስን የሰው ሀይል የተወሰኑ ስራዎች ሰርተናል›› ብለዋል፡፡ አቶ ክፍሌ በማህበሩ የተሰሩ ስራዎችንም ጠቅሰዋል፡፡ ለአብነት ያህል፡-

-ከተለያዩ ክልሎች እና አቻ ክለቦች ጋር ሰፊው ከስፖርታዊ ጨዋነት ዙርያ ውይይት አድርገናል፡፡ በዚህም ባለፈው አመት የተሻለ ስፖርታዊ ጨዋነት በየሜዳዎቹ ማሳየት ችለናል፡፡

-427 ብቻ የነበረውን የተመዘገቡ የአባላት ቁጥር ወደ 14 ሺህ ከፍ በማድረግ የደጋፊውን ቁጥር አብዝተናል፡፡ በገቢ ደረጃ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል፡፡ ይህም የገንዘብ መጠን የተገኘው በተለያዩ የአአ አካባቢ ቅርንጫፍ በመክፈት ነው፡፡

-ክለቡ በ40 አመት ምስረታ ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች የራቁ ቀደምት ደጋፊዎች ተከታታይነት ያለው ስብሰባዎችን በማድረግ ወደ ክለቡ እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡

-ከ10 ሺህ በላይ ደጋፊዎች የተሳተፉበት ቤተሰባዊ ሩጫ ባመረ ፣ በደመቀ ሁኔታ እንዲካሄድ አድርገናል፡፡ በደጋፊው መሀል የእርስ በእርስ ቤተሰበዊ ግኑኝነት እንዲፈጠርም ተደርጓል።

-የክለቡ መገለጫ የሆነ ቋሚ ሎጎ እንዲኖረው እና ከጊዜያዊ ስራ ከመጠመድ ይልቅ ዘላቂ የሆኑ ሰራዎችን ለመስራት የሚያስችል በአምስት አመት የሚፈፀም እስትራቴጂ ፕላን ተዘጋጅቷል፡፡

-የደጋፊዎች ማህበሩ የሚመራበት መተዳደርያ ደንብ የሌለው በመሆኑ ከተለያዩ ደጋፊ ማህበሮች ጋር የአሰራር ልምድ በመውሰድ ስራ አስፈፃሚው እና ደጋፊው የሚመራበት ደንብ እያዘጋጀን እንገኛለን፡፡

-የማህበራዊ ተሳትፎ ላይ ደጋፊው ይበልጥ በግል ተነሳሽነት የተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች ተሰርተዋል።

-ከሀገር ውስጥ ድሬዳዋ እና ቢሾፍቱ ፣ ከኢትዮዽያ ውጨ በተለያዩ ሀገሮች ቅርንጫፍ ቢሮዎችን በመክፈት የደጋፊውን ቁጥር ለማብዛት እየተንቀሳቀን እንገኛለን፡፡

በሁለት አመት ውስጥ ያጋጠሙ ችግሮች

-የስራ አስፈፃሚ አባላት በራሳቸው ፍቃድ በመልቀቃቸው ተጓድለናል፡፡

-የመዋቅርና የአሰራር ስርአት ያልተዘረጋ በመሆኑ ስራ አስፈፃሚ አባላት ሁሉም ስራ ላይ እንዲገቡ መደረጉ ሌሎች ስራዎችን ለመስራት እንዳይችል አድርጎታል፡፡

-በተለያዩ ባለሙያዎች የቀረቡ ገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮፖዛሎች እንደ ዋዛ በተለያዩ ምክንያቶች  ተግባራዊ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡

-በደጋፊዎች መካከል የነበረው መከፋፈል ለቡድኑ ውጤትም ሆነ ደጋፊ ማህበሩ ስኬታማ እንዳይሆን ቢያደርገውም አሁን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተቀርፎ አሁን በጥሩ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

-የክለቡ ደጋፊውን የሚመጥን ቡድን አለመሰራት እና ውጤት አለመምጣቱ ሰፊ ስራ አቅደን ላለመስራት እንቅፍት ሆኖብናል።
በቀጣይ የአደረጃጀት ሁኔታውን የማሻሻል ጠንካራ ስራ እንዲሰራ ማድረግ ፣ በጎደሉ ምትክ ስራ አስፈፃሚ መተካት እና ከላይ የገለፅናቸውን ስራዎች ለመስራት አቅደናልም ተብሏል።
የኦዲት ሪፖርት በአቶ ታምራት ጠንክር የቀረበ ሲሆን በ2008 ዓም 400ሺ ብር በላይ ገቢ ሲገኝ 2009 በሦስት እጥፍ ጨምሮ 1 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል፡፡ አጠቃላይ በሁለት አመት ውስጥ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ እንደተገኘ ተገልፃል፡፡

በወጪ ደረጃ ከ1ሚሊዮን ብር በላይ እንደወጣ ሲገለፅ ከፍተኛውን ወጪ የሚወስደው ለክልል ጉዞዎች ፣ በስፖርታዊ ጨዋነት ዙርያ ለተሰሩ ስራዎች ፣ የህትመት ስራ ወጪ ፣ ለፅህፈት ቤት ሰራተኞች ደሞዝ እና ማህበራዊ ጉዳይ ላይ የዋሉ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡ ከወጪ ቀሪም 7 መቶ ሺህ ብር በላይ እንዳለ ተገልፃል፡፡
ከተሳታፊ ደጋፊዎች የቀረቡ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች

-በክለቡ ወቅታዊ ጉዳይ ለምናነሳው ጥያቄ መልስ እንዲሰጡን ለምን የክለቡ የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ወይም ሌላ የቦርድ አባል አልተገኙም?

ጠቅላላ ጉባኤው ዘግይቷል ፣ የክ/ከተማ የደጋፊ ማህበር እየተቋቋመ ይገኛል ማነው የሚቆጣጠራቸው ምን ያህልስ ግኑኝነት አላችሁ?

በጄቲቪ እየቀረበ ያለው ፕሮግራም ደጋፊዎችን እያሳተፈ አይደለም፡፡ በጣም መሻሻል እና ደጋፊውንም የሚያሳትፍ መሆን ይገባል።

ለክለቡ እየቀረበ ያለው የደጋፊ ማልያ በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ሁሌ ይመጣል ትሉናላችሁ፡፡ ሆኖም እስካሁን መጥቶ አላየንም፡፡ ምድነው ችግሩ? መቼ ነው የማልያ ጥያቄዎችን የሚመለሰው?

ከክለቡ አመራር ጋር ያላቹ ግኑኝነት ምን ይመስላል?  የምናቀርባቸው ጥያቄዎችን አቅርቡልን፡፡ ክለቡ ጋር በጣም ተራርቀናል፡፡ ስለ ክለቡ ምንም አናውቅም፡፡ በቦርዱ ያለን ድምፅ ሆኗል፡፡ ስለዚህ በአጭር ጊዜ ውስጥ የምንገናኝበት እድል ፍጠሩልን፡፡

የደጋፊ ማህበሩ የገቢ ምንጭ ለማግኘት ከፍተኛ እቅድ አውጥቷል፡፡ ታዲያ ይህ ከክለቡ የገቢ ምንጭ ጋር እንዳይጋጭ ምን እያሰባቹ ነው?

ከደጋፊ ማህበሩ አመራር የተሰጡ ምላሾች

አቶ ክፍሌ አማረ ሰብሳቢ

‹‹የውክልና ጉዳይ ላይ እኛም ያሳስበናል፡፡ በቦርዱ አንድ ውክልና አለን፡፡ ሆኖም ድምፃችንን እየተጠቀምንበት አይደለም፡፡ ይህ ካልሆነ የደጋፊው ማህበር ምንም ጥቅም የለውም። ስለሆነም ቦርዱ ደጋፊውን ድምፅ እንዲሰማ ውክልናችን ትርጉም እንዲኖረው ጥረት እናደርጋለን።››
ክፍሌ ወልዴ  ህዝብ ግንኙነት

‹‹ በየሰፈሩ የሚቋቋሙ ደጋፊዎችን ጥሩ ጎን አለው፡፡ ብዙ ነገሮችንም ያቃልላሉ፡፡ በስፖርታዊ ጨዋነት ላይ በርካታ ስራዎችን በአካባቢያቸው እየሰሩ ነው፡፡ ይህ መልካም ጎን ነው።

‹‹ ማልያን በተመለከተ ክለቡ ከሀበሻ ቢራ ጋር የተዋዋላቸው ውሎች አሉ፡፡ ትጥቅ ፣ ቁሳቁስ የማቅረብ ፣ የደጋፊ ማልያዎችን ጨምሮ ሀበሻ ቢራ 20 ሺህ ጥራት ያለው ማልያ እንደሚመጣ ተገልፆ እስካሁን አልመጣም፡፡ በቅርብ እንዲመጣ እየጣርን ነው። ካልሆነ እኛ ከክለቡ ጋር ተነጋግረን ችግሩን ለመቅረፍ ከፍተኛ ስራ እንሰራለን፡፡
‹‹ የደጋፊ ማህበር መታወቂያ ጥቅም እንዲኖረው እየሰራን ነው፡፡ ፌዴሬሽኑ ድረስ በመሄድ መታወቂያው ዋጋ እንዲኖረውና አስፈላጊውን ነገር ቅድሚያ እንድታገኙ እየሞከርን ነው፡፡

‹‹ በስፖርታዊ ጨዋነት ዙርያ ከሚመለከታቸው የፀጥታ አካላት ፣ ከፌዴሬሽን እና ከሌሎች ደጋፊዎች ማህበር ጋር እየሰራን እንገኛለን፡፡ ቋሚ ኮሚቴም አዋቅረናል፡፡ በተጨማሪም በየበሩ የሚያስተባብሩ 100 አባላትን መርጠን በየቦታው አሰማርተናል፡፡ ለእነርሱ ተገዢ እንሁን፡፡ የስፖርታዊ ጨዋነት ጉዳይ ለኢትዮዽያ ቡና የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ ››
ከምላሾች በኋላ በጎደሉ የስራ አስፈፃሚ አባላት ምትክ ከመድረኩ በቀረበው ጥቆማ መሰረት አቶ በፍቃዱ አባይ እና ናትናኤል ተክሉ በጉባኤው ሙሉ ድምፅ ተመርጠዋል።  አቶ ዳንኤል የቦርድ አባላትን መልዕክት አስተላልፈው እንዲሁም የክለቡ የቦርድ ሰብሳቢ እና ሌሎች አባላት የቀሩበትን ምክንያት ለተሳታፊው በመግለፅ ጠቅላላ ጉባኤው ፍፃሜውን አግኝቷል።

በመጨረሻም በጣም ቀልብን የሚገዙ፣ አትክሮትን የሚስቡ፣ የኢትዮዽያ ቡና ደረጃ ከፍ የሚያደርጉ፣ በደጋፊው መካከል መተማማን የሚያመጡ ፣ ራስን የማረም እና የመገሰፅ ፣ የስፖርት ነውጠኝነት ለመቀየር የሚያስችሉ ጠቃሚ መልክቶች ከመድረኩ ተሳታፊዎች በጥሩ መንገድ ሲገለፁ ተመልክተናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *