ባህርዳር ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ የመጨረሻ ሳምንት ድላቸውን ለማስቀጠል የሚፋለሙበት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
በአርባ ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ባህር ዳር ከተማዎች በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ድል አድርገው ደረጃቸውን ለማሻሻል ነገን ይጠብቃሉ።
በመጨረሻው መርሐ-ግብር ከጨዋታ ብልጫ ጋር መቐለ 70 እንደርታን የረቱት የጣና ሞገዶቹ በዕለቱ ውጤታማ የነበራቸው ውጤታማ የማጥቃት አጨዋወት ወደ ነገው መርሐ-ግብር መሻገር የሚገባው አወንታዊ ጎን ነው። የጣና ሞገዶቹ ቅዱስ ጊዮርጊስን በተመሳሳይ ውጤት አራት ለአንድ ካሸነፉ በኋላ በተከናወኑ አምስት ጨዋታዎች ላይ በሦስቱ ግብ ሳያስቆጠሩ ወጥተዋል፤ እንደ ቡድኑ ውጤት ሁሉ የወጥነት ችግር የሚስተዋልበት የማጥቃት አጨዋወታቸውን ብቃት ማስቀጠልም ከአሰልጣኝ ደግአረግ ቡድን የሚጠበቅ ነው። በነገው ዕለትም ወደ ራሱ የግብ ክልል ተስቦ በመልሶ ማጥቃት ዕድሎች ለመፍጠር የሚታትር እና ድሉን ለማስቀጠል ወደ ሜዳ የሚገባ ቡድን እንደመግጠማቸው በመቐለው ጨዋታ የተስተዋለው እጅግ ውጤታማ የአፈፃፀም ብቃታቸውን ማስቀጠል ግድ ይላቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ በመጨረሻው ጨዋታ መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይ ባልተለመደ መልኩ ለፈጣን ሽግግሮች ተጋላጭ የነበረው የመከላከል አደረጃጀታቸውን ማስተካካል ይኖርባቸዋል።
በሁለተኛው ዙር መጠነኛ መቀዛቀዝ ማሳየታቸው ተከትሎ ወደ አደጋው ክልል ይበልጥ የተቃረቡት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ደረጃቸውን ለማሻሻል በይደር በተካሄደው የመጨረሻው ጨዋታ ያስመዘገቡት ወሳኝ ድል ማስቀጠል በእጅጉ ያስፈልጋቸዋል።
በሰላሣ ሁለት ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኤሌክትሪኮች በመጨረሻው ጨዋታ የቅርብ ተፎካካርያቸው ላይ ሁለት ግቦች አስቆጥረው ማሸነፍ ቢችሉም ከዛ በፊት በተካሄዱ ስድስት ጨዋታዎች ላይ ግን በግብ ማስቆጠሩ ረገድ ጉልህ ድክመት ተስተውሎባቸዋል፤ ከድሉ በፊት በተከናወኑ ስድስት መርሐ-ግብሮች ሁለት ግቦች ብቻ ካስቆጠረ በኋላ በመጨረሻው ጨዋታ ዳግም ወደ ግብ ማስቆጠሩ የተመለሰው የማጥቃት ጥምረቱም በሊጉ ዝቅተኛ ግብ በማስተናገድ 2ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው የባህር ዳር ከተማ የኋላ ክፍል ለሚጠብቀው ፈተና መዘጋጀት አለበት።
በተጠባቂ መርሐ-ግብሮች በአመዛኙ ወደ መከላከሉ ላይ ያዘነበለ እና በመልሶ ማጥቃት ዕድሎች ለመፍጠር የሚሞክር የጨዋታ አቀራረብ የሚከተሉት አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ነገም በተመሳሳይ መንገድ ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፤ ይህንን ተከትሎ ቡድኑ ነገም በሚፈለገው ደረጃ ኳስ መያዝ የሚያስችለውን ነፃነት ላያገኝ ቢችልም ከተጋጣሚው የሚመጣበትን የመስመር ጥቃት ለመመከት ግን የመከላከል ውቅሩን ማስተካከል ሳይኖርበት አይቀርም። በሦስት ጨዋታዎች አምስት ግቦች ካስተናገደ ወዲህ በመጨረሻው መርሐ-ግብር መረቡን አስከብሮ የወጣው የኋላ ክፍሉም መቐለ ላይ አራት ግቦች አስቆጥሮ ወደ ነገው ጨዋታ ለሚቀርበው የተጋጣሚው የፊት ጥምረት በሚመጥን አኳኋን መቅረብ ግድ ይለዋል።
በጣና ሞገዶቹ በኩል ሁሉም የቡድን አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው። በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩልም አጥቂው ፍቃዱ አለሙ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጭ ከመሆኑ በቀር ሁሉም የቡድኑ አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ሆነው ይቀርባሉ።
ሁለቱ ቡድኖቹ በፕሪምየር ሊጉ ከዚህ ቀደም በ3 አጋጣሚዎች የተገናኙ ሲሆን የጣና ሞገዶቹ ሁለት ኢትዮ ኤሌክትሪክ ደግሞ አንድ ጨዋታ በድል ተወጥተዋል። በጨዋታዎቹ ባህርዳር ከተማ 5 ግቦች ሲያስቆጥር ኤሌክትሪክ 3 ማስቆጠር ችሏል።