ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ፋሲል ከነማ ከ ወላይታ ድቻ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ፋሲል ከነማ ከ ወላይታ ድቻ

የወራጅነት ስጋት ያንዣበበባቸው ዐፄዎቹ እና ደረጃቸውን ለማሻሻል ወደ ሜዳ የሚገቡት የጦና ንቦቹ ከናፈቃቸው ድል ጋር ለመታረቅ የሚፋለሙበት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

በሰላሣ ስምንት ነጥብ 13 ደረጃ ላይ የተቀመጡት ፋሲል ከነማዎች ከገቡበት የወራጅነት ስጋት ለማምለጥ ከሦስት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች መልስ ድል ማድረግ ይኖርባቸዋል።

ከድል ጋር ከተራራቁ ስምንት የጨዋታ ሳምንታት ያስቆጠሩት ዐፄዎቹ ሳይታሰብ ከወራጅ ቀጠናው በሦስት ነጥቦች ርቀት ላይ ሲገኙ በነገው ዕለት የሚያደርጉት ጨዋታም በሊጉ የመቆየታቸው ጉዳይ ከሚወስኑ ወሳኝ መርሐ-ግብሮች አንዱ ነው። በቅርብ ሳምንታት በተከታታይ መርሐ-ግብሮች ነጥብ ተጋርቶ መውጣት የቻለው ቡድኑ ከምንም በላይ ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት ከማጠናቀቅ አባዜው መላቀቅ ይጠበቅበታል። ዐፄዎቹ በሊጉ በአስራ አራት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቶ በመውጣት ቀዳሚ ናቸው፤ የቅርብ ተፎካካሪዎቻቸው ተከታታይ ድሎች ባስመዘገቡበት እና በውድድር ዓመቱ ወሳኝ ወቅት ላይ በመደዳ አቻ ተለያይተው ወሳኝ ነጥቦች መጣላቸውም ቡድኑ አጣብቂኝ ውስጥ ከቶታል። ይህንን ተከትሎ ቡድኑ ከናፈቀው ድል ጋር ታርቆ ከአስጊው ቀጠና ለመውጣት የሚያደርገውን ሩጫ ለማፋጠን በርከት ያሉ ለውጦች ማድረግ ግድ ይለዋል። ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር ባደረጉት የመጨረሻ መርሐ-ግብር በኳስ ቁጥጥርም ሆነ ዕድሎች በመፍጠር ረገድ ደካማ እንቅስቃሴ ያደረጉት ፋሲሎች ከተጋጣሚያቸው አቀራረብ አንፃር በነገው ጨዋታ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ ፈተና ይገጥማቸዋል ተብሎ ባይገመትም ዕድሎችን በመፍጠር በኩል ያለባቸውን ድክመት ግን መቀረፍ የሚገባው ጉዳይ ነው።

በአርባ ሁለት ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ወላይታ ድቻዎች ደካማ ውጤቶች ካስመዘገቡባቸው አራት የጨዋታ ሳምንታት መልስ ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ዐፄዎቹን ይገጥማሉ።

ካለፉት አራት መርሐ-ግብሮች አንድ ነጥብ ብቻ ማስመዝገባቸውን ተከትሎ ወደ ሰንጠረዡ አካፋይ የተንሸራተቱት የጦና ንቦቹ ከወራጅ ቀጠናው በሰባት ነጥብ ርቀት ላይ እንደመገኘታቸው ያን ያህል የከፋ ስጋት ባይኖራቸውም ካለው የነጥብ መቀራረብ አንፃር የተሻለ ደረጃ ይዘው የውድድር ዓመቱን ለማጠናቀቅ ከነገው ጨዋታ የሚገኙትን ነጥቦች ይፈልጉታል። ባለፉት አራት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው አስራ ሁለት ነጥብ አንዱን ብቻ ማሳካት የቻለው የአሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ ቡድን በነገው ዕለት ወደ ድል መንገድ ለመመለስ በጨዋታዎቹ አንድ ግብ ብቻ ያስቆጠረውና የቀደመው ቀጥተኛ አጨዋወቱን ጥንካሬ ማስቀጠል ያልቻለው የማጥቃት አቀራረቡን ማሻሻል ይኖርበታል። የነገው ተጋጣሚው ካንዣበበት የወራጅነት ስጋት ለመሸሽ የሞት ሽረት ትግል ማድረግ የሚጠበቅበት ወቅት ላይ እንደገኘቱም ምናልባትም በመከላከሉ ረገድ ፈታኝ ፍልምያ ሊጠብቀው ይችላል፤ ይህንን ተከትሎ መረቡን ካስከበረ ስምንት የጨዋታ ሳምንታት ያስቆጠረው የቡድኑ የተከላካይ ጥምረት ከመቼውን ጊዜ በላይ በተሻለ ብቃት መቅረብ ይኖርበታል።

በፋሲል ከነማ በኩል ባለፈው ጨዋታ ላይ መጠነኛ ጉዳት ኖሮባቸው ወደ ቋሚ አሰላለፍ ገብተው ከነበሩት ሁለቱ ተከላካዮቹ መካከል እዮብ ማቲያስ በጉዳት የማይኖር ሲሆን ምኞት ደበበ ደግሞ መሰለፉ አጠራጣሪ ነው። አማካዩ አቤል እንዳለ እንዲሁም አጥቂው አማኑኤል ገብረሚካኤል ግን በጉዳት ከጨዋታው ውጪ ሲሆኑ ቅጣት ያለባቸው አማካዩ ሀብታሙ ተከስተ እና ማርቲን ኪዛም ነገ የማይኖሩ ይሆናል። በወላይታ ድቻ በኩል ካርሎስ ዳምጠው እና ኬኔዲ ከበደ በቅጣት ብስራት በቀለ ደግሞ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጭ ናቸው። ግብ ጠባቂው ቢንያም ገነቱ እና ያሬድ ደርዛም ወደ ልምምድ ቢመለሱም የመሰለፋቸው ነገር ነገ የሚወሰን ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪ ጉዳት ላይ የነበረው ናትናኤል ናሲሮ ጨምሮ የተቀሩት የቡድኑ አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።

ሁለቱ ክለቦች እስካሁን 15 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ፋሲል ከነማዎች 7 ጊዜ ድል አድርገው 17 ግቦች ሲያስቆጥሩ 15 ግቦች ያሏቸው ወላይታ ድቻዎች 5 ጊዜ አሸንፈዋል፤ 3 ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል።