ላለመውረድ በሚደረገው ትንቅንቅ ከተዋናዮቹ አንዱ የሆነው አዳማ ከተማ ቀድሞ መውረዱን ካረጋገጠው ስሑል ሽረ ጋር የሚፋለምበት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
በሀያ ሁለት ነጥብ 17ኛ ላይ የተቀመጠው ስሑል ሽረ ወደ ከፍተኛ ሊግ መውረዱ ማረጋገጡን ተከትሎ የነገ ጨዋታ ዓላማው ለክብር እና ለክብር ብቻ ይሆናል።
ስሑል ሽረዎች በሀዋሳ ከተማ ቆይታቸው በውድድር ዓመቱ ከነበራቸው በአንፃራዊነት የተሻለ ብቃት አሳይተው በስምንት ጨዋታዎች ውስጥ በአንድ አጋጣሚ ብቻ ሽንፈት ብያስተናግዱም ከሰባት ጨዋታዎች የሰበሰቡት ነጥብ ሰባት ብቻ ነበር። ቡድኑ ውስን መሻሻል ባሳየበት ወሳኝ ወቅት ላይ ድል ለማስመዝገብ መቸገሩ እንዲሁም በ31ኛ እና 32ኛ ሳምንት ላይ ተከታታይ ሽንፈቶች ማስተናገዱም የመውረዱ ጉዳይ እንዲፋጠን አድርጎታል። ቡድኑ በ16ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው የነገው ተጋጣሚው አዳማ ከተማ በአስራ ሦስት ነጥብ መራቁን ተከትሎ ደረጃውን የሚያሻሽልበት ዕድል ዝግ ቢሆንም ብያንስ የውድድር ዓመቱን በተሻለ ውጤት ለማገባደድ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ስምንት ግቦች ያስተናገደው የመከላከል አደረጃጀቱን ማሻሻል ይኖርበታል።
ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች በመደዳ ሙሉ ነጥብ ያስመዘገበው አዳማ ከተማ ያያዘው የድል መንገድ በማስቀጠል ከአስጊው ቀጠና ለመውጣት የሚያደርገው ሩጫ ለማፋጠን መውረዱን ካረጋገጠው ስሑል ሽረ ጋር ይፋለማል። በ ሰላሣ አምስት ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ቡድኑ በነገው ዕለት ድል ማድረግ በ13ኛ ደረጃ ከተቀመጠው ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና 14ኛ ደረጃ ላይ ካለው ፋሲል ከነማ በነጥብ እንዲስተካከል ስለሚረዳው መርሐ-ግብሩ ወሳኝ ነው።
ውድድሩ ወደ መቀመጫ ከተማቸው ከተዘዋወረ በኋላ ጉልህ መሻሻል ያሳዩት አዳማ ከተማዎች ከባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ሙሉ ነጥብ ከማሳካታቸው በተጨማሪ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴያቸው በብዙ ረገድ ጎልብቷል። በተለይም ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ላይ በዘጠኝ ተከታታይ መርሐ-ግብሮች ካስቆጠራቸው ድምር ግቦች የሚልቅ የግብ መጠን ያስቆጠረው የማጥቃት ጥምረቱ እና በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች መረቡን ያላስደፈረው የመከላከል አደረጃጀታቸው በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ ይገኛል። ይህንን ተከትሎ ቡድኑ በእንቅስቃሴም ይሁን በመንፈስ ረገድ ያለው ብርታት ማስቀጠል የአሰልጣኝ አብዲ ቡሊ ቀዳሚ ስራ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
በስሑል ሽረ በኩል ሙላለም መስፍን፣ ሀብታሙ ገዛኸኝ፣ ፋሲል አስማማው እና ሙሴ ዕቋር በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆኑ አምበሉ ነፃነት ገብረመድህን ግን ከጉዳት አገግሟል። በአዳማ ከተማ በኩል ሁሉም የቡድን አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።
በግቦች የተንበሸበሸ የግንኙነነት ታሪክ ያላቸው ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 3 ተገናኝተው አንድ አንድ ጊዜ በእኩሌታ ድል ስያደርጉ አንድ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። በግንኙነቱ አዳማ ከተማ 6 ስሑል ሽረ ደግሞ 4 ግቦች አስቆጥረዋል።