ምዓም አናብስት ከሰባት ሳምንታት በኋላ ከወራጅ ቀጠናው የሚወጡበት ዕድል ለማመቻቸት ቡናማዎቹ ደግሞ ከመሪው ጋር ያላቸውን ልዩነት ለማጥበብ የሚያደርጉት ጨዋታ ረፋድ ላይ ይደረጋል።
በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ በወራጅ ቀጠናው መውጫ በር ላይ የቆመው መቐለ 70 እንደርታ የነገ ጨዋታ ለመትረፍ በሚያደርገው ጉዞ ላይ ያለው ትርጉም ብዙ ነው።
ፀጋዬ ኪዳነማርያምን በዋና አሰልጣኝነት ከሾሙ በኋላ ባደረጓቸው አምስት ጨዋታዎች ሁለት ድል፣ ሁለት አቻ እና አንድ ሽንፈት በማስመዝገብ መጠነኛ መሻሻል ያሳዩት ምዓም አናብስት ውጤቶቹን ተከትሎ በሊጉ የመትረፍ ዕድላቸውን አለምልመዋል። ከወራጅ ቀጠናው ከፍ ብለው ከተቀመጡት ፋሲል ከነማ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እንዲሁም አዳማ ከተማ በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ የተቀመጠው ቡድኑ በነገው ዕለት ሙሉ ነጥብ ማሳካት ከቻለ በጊዝያዊነትም ቢሆን ከሰባት የጨዋታ ሳምንታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ከወራጅ ቀጠናው የመውጣት ዕድል ስለሚያገኝ እንዲሁም በዚህ የጨዋታ ሳምንት የቅርብ ተፎካካሪዎቹ ኤሌክትሪክ እና ፋሲል እርሰ በርስ የሚገናኙ በመሆኑ የነገ መርሐ-ግብሩ እጅግ ወሳኝ ነው።
በተለይም ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች በብዙ ረገድ የተሻሻለ ብቃት ያሳዩት መቐለዎች ከምንም በላይ ጨዋታዎችን የሚቆጣጠሩበት መንገድ ላይ ያስመዘገቡት እመርታ በጉልህ ይጠቀስላቸዋል፤ ከዚህ ቀደም ቀጥተኛ አቀራረብ የነበረው እና በኳስ ቁጥጥር ላይ እምብዛም የነበረው ቡድኑ በቅርብ ሳምንታት ጨዋታን የመቆጣጠር አቅሙ ከፍ ማድረጉን ተከትሎ የሚፈጥራቸው ዕድሎች በቁጥርም ሆነ በጥራት ጨምረዋል፤ ሆኖም ዕድሎች የመጠቀም ክፍተቱ አሁንም እንደቀጠለ ነው። ይህንን ተከትሎ የቡድኑን ድል አድራጊነት መንፈስ ማስቀጠል እንዲሁም ባለፉት ሰባት ጨዋታዎች ላይ አንድ ግብ ብቻ ላስተናገደው የቡና ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት የሚመጥን የማጥቃት አጨዋወት ማበጀት ከቡድኑ ይጠበቃል።
በሀምሳ አምስት ነጥቦች 2ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች ከሁለት የጨዋታ ሳምንታት በኋላ ድል አድርገው ከመሪው ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ ወደ ሜዳ ይገባሉ።
የዋንጫ ጉዞው ላይ ተስፋ ፈንጣቂ ከነበረው መሪው መድንን ያሸነፈበት ጨዋታ በኋላ ከድል ጋር መራራቁ ተከትሎ ከዋንጫ ፉክክሩ ቀስ በቀስ የራቀው ኢትዮጵያ ቡና ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ሦስት ነጥብ አግኝቶ በጊዜያዊነትም ቢሆን የነጥብ ልዩነቱን ወደ ስድስት ዝቅ ለማድረግ የነገውን ጨዋታ ይፈልገዋል። ኢትዮጵያ ቡና ተከታታይ ድሎች ካገኘባቸው አምስት መርሐ-ግብሮች በኋላ ነጥብ ለመጣል ቢገደድም በሁለቱም ጨዋታዎች ለትችት የሚዳርገው እንቅስቃሴ አላደረገም። ቡድኑ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች የገጠሙት ፈተናዎችም በተመሳሳይ መገለፅ የሚችሉ ናቸው፤ የተጋጣሚን ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት የማስከፈት እና የሚገኙ ዕድሎች የመጨረስ ድክመቶች!
ቡናማዎቹ ነጥብ በጣሉባቸው ሁለት ጨዋታዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመውሰድም ሆነ የግብ ዕድሎች በመፍጠር ረገድ ከተጋጣሚያቸው የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረጋቸው ባይካድም እንደነበራቸው ብልጫ በርከት ያሉ የጠሩ የግብ ዕድሎች አልፈጠሩም። ይህንን ተከትሎ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ኳስና መረብ ማገናኘት የተሳነውን የፊት መስመር ማስተካከል ከአሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ ይጠበቃል።
የነገው ጨዋታ ከኢትዮጵያ ቡና ይልቅ ለመቐለ 70 እንደርታ ያለው ወሳኝነት ትልቅ ቢሆንም ጠንካራ ፍልምያ ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህ በተጨማሪም ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ ዕድሎች የመጠቀም ክፍተት ያለባቸው በመሆኑ በሌሎች የሜዳ ክፍሎች ከሚኖረው ፍልምያ በተሻለ በዕለቱ የሚኖራቸው የአፈፃፀም ብቃት ምናልባትም ጨዋታውን ሊወስን ይችላል።
ቡድኖቹ ከዚህ ቀደም 5 ጊዜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ቡና 2 መቐለ 70 እንደርታ ደግሞ 1 ጨዋታ ማሸነፍ ችለዋል። በግንኙነቱ ቡናማዎቹ 5፣ ምዓም አናብስት 2 አስቆጥረዋል። (በ2012 በኮቪድ ምክንያት የተሰረዘውና 1-1 የተጠናቀቀው ጨዋታን አያካትትም)