የዓምና ሻምፕዮኖቹ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ካንዣበበባቸው የወራጅነት ስጋት ለመራቅ ነብሮቹ ደግሞ በጊዜያዊነትም ቢሆን ወደ 4ኛ ደረጃነት የሚያሻግራቸውን ድል ለማግኘት የሚፋለሙበት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
በአርባ ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት የዓምና ሻምፕዮኖቹ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ከተጋረጠባቸው የወራጅነት ስጋት ለመሸሽ ነገ ወሳኝ ጨዋታ ያደርጋሉ፤ ቡድኑ በወራጅ ቀጠናው መውጫ በር ላይ ከቆመው አዳማ ከተማ በሁለት ነጥብ ርቀት ላይ መቀመጡም በነገው ዕለት ድልና ድልን ብቻ እያለመ ወደ ሜዳ እንዲገባ ያስገድደዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከድል ጋር ከተራራቀ ስምንት የጨዋታ ሳምንታት አስቆጥሯል፤ ከአስራ ዘጠኝ ዓመታት ጥበቃ በኃላ ቅዱስ ጊዮርጊስን ካሸነፈበት የ25ኛ ሳምንት ጨዋታ ማግስት በ2ኛ ደረጃ ላይ ከነበረው ባህርዳር ከተማ በሁለት ነጥቦች ብቻ ዝቅ ብሎ 5ኛ ደረጃ ላይ የነበረው ቡድኑ ባለፉት ሳምንታት ከድል ጋር መኳረፉን ተከትሎ በስምንት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ከዋንጫ ተፎካካሪነት ተንሸራቶ ላለመውረድ በሚደረገው ፍልምያ ተገኝቷል።
የአሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ ቡድን በአብዛኞቹ ጨዋታዎች ከተጋጣሚው አንፃር የተሻለ ተንቀሳቅሶ ብልጫ እየወሰደ ቢዘልቅም በግብ ፊት ያለው ጉልህ የግብ ማስቆጠር ድክመት በውድድር ዓመት ጉዞው ትልቁ ፈተናው ነበር፤ በርግጥ ቡድኑ በቀጠናው ካሉ ቡድኖች ተቀራራቢ የግብ መጠን (29) ማስቆጠር ቢችልም በጨዋታዎች ከነበረው ብልጫ አንፃር ቁጥሩ ጥቂት ነው። የቡድኑ የግብ ማስቆጠር ችግር ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ቢሆንም በቅርብ ሳምንታት ግን በብዙ ረገድ ተቀዛቅዟል። ቡድኑ የተሻለ የግብ ዕድሎችን ፈጥሮ ከኤሌክትሪክ ጋር አቻ የተለያየበትን ጨዋታ ጨምሮ ባለፉት አምስት መርሐ-ግብሮች መጥፎ የሚባል ብቃት ባያሳይም በተጠቀሱት ጨዋታዎች ያስቆጠራቸው ግቦች ሁለት ብቻ ናቸው። ይህንን ተከትሎ የማጥቃት አጨዋወቱን ማስተካከል፤ የግብ ዕድሎች በቁጥርም ሆነ በጥራት የሚፈጠሩበት መንገድ ማመቻቸት እና የአፈፃፀም ክፍተቱን ማረም ከሀምራዊ ለባሾቹ የሚጠበቅ ነው።
በአርባ አራት ነጥብ በ9ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሀድያ ሆሳዕናዎች ከላይም ሆነ ከታች እየተደረጉ ካሉ ፉክክሮች ርቀው በሰንጠረዡ አካፋይ ላይ እንደመቀመጣቸው የቀጣይ መርሐ-ግብሮቻቸው ዋና ዓላማ የውድድር ዓመቱ የተሻለ ደረጃ ይዞ ማጠናቀቅ ይሆናል።
በነገው ጨዋታ ወደ ሰንጠረዡ ወገብ የሚገፋቸውን ውጤት ለማግኘት ወደ ሜዳ የሚገቡት ነብሮቹ ራሱን ለማትረፍ በሚያደርገው ጥረት ውስጥ ተስፋ የሚሆኑ ነጥቦችን ፍለጋ ብርቱ ፍልምያ ያደርጋል ተብሎ ከሚጠበቀው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚገጥማቸው ፈተና ከባድ መሆኑ አይቀሪ ነው።
ካለፉት አራት ጨዋታዎች ሦስት ነጥቦችን ብቻ ያገኘው ቡድኑ በሁለተኛው ዙር በተካሄዱ አስራ አራት መርሐ-ግብሮች ውስጥ ሁለት ድሎችን ብቻ በማስመዝገብ የመጀመርያው መንፈቅ ውጤታማነቱን ማስቀጠል ተስኖት ቢገኝም በመጀመርያው ዙር በሰበሰባቸው ነጥቦች የመውረድ ስጋት ውስጥ አልገባም። ሆኖም ከነገ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማግኘት በጊዝያዊነትም ቢሆን ወደ 4ኛ ከፍ ስለሚያደርገው ጨዋታውን በቀላሉ አይመለከተውም።
ቀጥተኛ በሆነ አቀራረብ የፊት አጥቂዎቻቸውን ያማከሉ ኳሶችን በመላክ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት የሚያደርጉት ነብሮቹ በነገው ዕለትም በተመሳሳይ አጨዋወት ይቀርባሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ከመቻል ጋር ነጥብ በተጋሩበት ጨምሮ ባለፉት ጨዋታዎች የተስተዋሉባቸው የአጨራረስ ድክመቶች መቅረፍም ይኖርባቸዋል።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ጉዳት ላይ የሰነበተው ባሲሩ ኡማር እና ናትናኤል ዳንኤል በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጭ ናቸው። ቅጣት ላይ የነበረው ኪቲካ ጅማ ጨምሮ ሌሎች የቡድኑ አባላት ግን ለጨዋታው ዝግጁ እንደሆኑ አውቀናል። በሀድያ ሆሳዕና በኩል ከድር ኩሊባሊ በጉዳት እንዲሁም ረዳት አሰልጣኝ ካሊድ መሀመድ በቅጣት የማይኖሩ ሲሆን ጫላ ተሺታም ከረጅም ጊዜ ጉዳት ወደ ልምምድ ቢመለስም ለነገው ጨዋታ አይደርስም። ከዚህ ውጭ የተቀሩት የቡድኑ ተጫዋቾች ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው።
ቡድኖቹ በሊጉ 5 ጊዜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 3 አሸንፎ 4 ጎሎችን ማስቆጠር የቻለ ሲሆን ሀድያ ሆሳዕናም አንድ ድልና አንድ ግብ አስመዝግቦ በተቀረው አንድ ጨዋታ ነጥብ ተጋርተዋል።