የዋልያዎቹ የዛሬ ረፋድ ልምምድ ቀርቷል

የዋልያዎቹ የዛሬ ረፋድ ልምምድ ቀርቷል

ወደ አሜሪካ ለማቅናት ትናንት የሁለተኛ ቀን ልምምዱን ያደረገው የኢትዮጵያ  ብሔራዊ ቡድን የዛሬ ረፋድ ልምምዱ መቅረቱ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንዳለፈው ለሁለተኛ ጊዜ ወደ አሜሪካ በማምራት ከዲሲ ዩናይትድ ቡድን ጋር ለሚያደርገው የኢግዚቢሽን ጨዋታ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ለ23 ተጫዋቾች ጥሪን በማድረግ ከረቡዕ ጀምሮ ሁለት የልምምድ ቀናቶች ማሳለፉ ይታወቃል። ዛሬም በተለመደው ሰዓት ከረፋድ ጀምሮ ብሔራዊ ቡድኑ ልምምዱን ይሰራል ተብሎ ቢጠበቅም መሰረዙን አረጋግጠናል። ምክንያቱ ምን እንደሆነ ባደረግነው ማጣራት የቡድኑ አባት ዛሬ የኤምባሲ ቀጠሮ ያላቸው በመሆኑ እንደሆነ አውቀናል።

ከሰሞኑን ሶከር ኢትዮጵያ በብሔራዊ ቡድኑ  ልምምድ በአካል በመገኘት እንዳጋራችው መረጃ ከሆነ ወደ አሜሪካ የሚያቀኑት የቡድኑ አባላት የቪዛ ፈቃድ እንዳላገኙ እና ዛሬ ኤምባሲ መግባት እንደሚጀምሩ ጠቁመን ነበር። በዚህ መነሻነት ይህን ዘገባ ወደ እናንተ እያደረስን ባለንበት ሰዓት አብዛኛው የቡድኑ አባላት አዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በር ላይ የቀጠሮ ሰዓታቸውን በመጠባበቅ መግባት መጀመራቸውን አውቀናል። ይህን ተከትሎም የረፋዱ ልምምድ የማይደረግ ሲሆን ምን አልባት ሁኔታዎች ከተመቻቹ አመሻሽ ላይ መደበኛ ልምምዳቸውን ሊያደርጉ የሚችሉበት ዕድል ሊፈጠር እንደሚችል ተገምቷል።

ብሔራዊ ቡድኑ የሀገር ቤት ዝግጅቱን አጠናቆ ማክሰኞ ወደ አሜሪካ እንደሚጓዝ ሲጠበቅ ሐምሌ 26 ቀን ከዲሲ ዩናይትድ ጋር ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናል።