ወደ አሜሪካ አቅንቶ ከዲሲ ዩናይትድ ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ ዝግጅቱን እያደረገ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስብስብ ውስጥ በርካቶች ቪዛ መከልከላቸውን አረጋግጠናል።
ከሰሞኑን ሶከር ኢትዮጵያ በብሔራዊ ቡድኑ ልምምድ በአካል በመገኘት እንዳጋራችው መረጃ ከሆነ ወደ አሜሪካ ሚያቀኑት የቡድኑ አባት የቪዛ ፈቃድ እንዳላገኙ እና ዛሬ ኤምባሲ መግባት እንደሚጀምሩ እንዲሁም አብዛኛው የቡድኑ አባላት አዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካ ኤንባሲ በር ላይ የቀጠሮ ሰዓታቸውን በመጠባበቅ መግባት መጀመራቸውን አሳውቀናችሁ ነበር።
አሁን በደረሰን መረጃ ደግሞ ሰባት ተጫዋቾች እና ሁለት የአሰልጣኞች ቡድን አባላት ወደ አሜሪካ ማቅናት የሚችሉበትን ቪዛ መከልከላቸው ታውቋል። በዚህም መሠረት ወገኔ ገዛኸኝ ፣ መሐመድ አበራ ፣ ያሬድ ካሳየ ፣ ግብጠባቂው ቢኒያም ገነቱ፣ አህመድ ሁሴን ፣ ቢንያም አይተን፣ በረከት ደስታ እና አብዱልከሪም ወርቁ እንዲሁም ምክትል አሰልጣኙ ተመስገን ዳናን ጨምሮ ወደ አሜሪካ መጓዝ እንደማይችሉ ተረጋግጧል። የቪዛ ፍቃድ ያላገኙ ተጫዋቾቹም ከጁፒተር ሆቴል ለቀው ለመውጣት እየተዘጋጁ መሆናቸውን አውቀናል። አሁን ባለው ሁኔታ ጥሪ ከተደረገላቸው 23 ተጫዋቾች መካከል ወደ ከቡድኑ ጋር የሚቆዩት 15 ተጫዋቾች መሆናቸው ታውቋል።
ብሔራዊ ቡድኑ የሀገር ቤት ዝግጅቱን አጠናቆ ማክሰኞ ወደ አሜሪካ እንደሚጓዝ ሲጠበቅ ሐምሌ 26 ቀን ከዲሲ ዩናይትድ ጋር ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናል።
* ቪዛ ባላገኙት ምትክ ሌሎች አማራጮች ይኖራሉ ወይስ 15 ተጫዋቾች ብቻ ይሄዳሉ የሚለውን በቀጣይ ተከታትለን ወደ እናንተ እናደርሳለን።