በዛሬው ዕለት ስምንት ተጫዋቾችን እና ሁለት የአሰልጣኝ ቡድን አባላትን በቪዛ ምክንያት ያጣው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጨማሪ ሁለት ተጫዋቾችን እና አንድ የሕክምና ቡድን አባሉን ማጣቱን አረጋግጠናል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአሜሪካ የፊታችን ሐምሌ 26 ከዲሲ ዩናይትድ ጋር የወዳጅነት ጨዋታን ለማድረግ ወደ ሀገረ አሜሪካ እንደሚያመራ ይታወቃል። የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ከቀናት በፊት ለሃያ ሦስት ተጫዋቾች ጥሪን በማድረግ በአዲስ አበባ ስታዲየም ልምምድ ሲሰሩ የነበረ ሲሆን በብሔራዊ ቡድኑ ጥሪ ከደረሳቸው ተጫዋቾች መካከል በዛሬው ዕለት በአሜሪካን ኢምባሲ በመገኘት የቪዛ አገልግሎትን ለማግኘት ጥረት ካደረጉ የቡድኑ አባላት መካከል ከተጫዋቾች መሐመድ አበራ ፣ ቢኒያም ገነቱ ፣ ያሬድ ካሳዬ ፣ ወገኔ ገዛኸኝ ፣ አህመድ ሁሴን ፣ ቢኒያም ዐይተን እና በረከት ደስታ ከአሰልጣኝ ቡድን አባላት ረዳቱ ተመስገን ዳና በቪዛ ምክንያት ከብሔራዊ ቡድኑ ስብስብ ውጪ መሆናቸውን ከሰዓታት በፊት በነበረው ዘገባችን ያስነበብናችሁ ሲሆን አሁን ደግሞ ተጨማሪ ሁለት ተጫዋቾች እና የሕክምና ቡድን አባሉ ብሩክ ደበበ ከብሔራዊ ቡድኑ ውጪ ሆነዋል።
ከዚህ ቀደም ወደ አሜሪካ ተጉዘው የነበሩት የባህርዳር ከተማው የመስመር አጥቂ ቸርነት ጉግሳ እና የፋሲል ከነማው የመሐል ተከላካይ ምኞት ደበበ ከፓስፖርት ጋር በተያያዘ ከቡድኑ ውጪ ሆነዋል። በዚህም መሠረት ከሀያ ሦስቱ ተጫዋቾች መካከል አስራ ሦስ ብቻ የቪዛ ባለቤት ሆነዋል።