በሳሙኤል ስለሺ
እንደ ዜጋ የተፃፈ
ምስጋና በሁሉም መልኩ ለተረባረቡ ኢትዮጵያውያን ይግባና ‹‹የአባይን ልጅ ውሐ ጠማው›› የሚለው ብሂል ከጳጉሜ 04/2017 ዓ.ም በኋላ በኢትዮጵያ ስነ ቃል ውስጥ ቦታ የለውም፡፡ የኢትዮጵያ ልጅ ኳስ ጥማት ግን መቼም የሚቆረጥ አይመስልም፤ ምን አልባትም አመርቂ ጅምር ስራዎች በሌሉበት በዚህ ሁኔታ ይህ የኳስ ጥማት ለሚቀጥሉት አንድ እና ሁለት ትውልድ የሚቀባበል ሸክም እንደሆነ ይሰማኛል፤ ‹‹እስካልገደብነው›› ድረስ፡፡
ዛሬ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ቡድንን ችግር የታክቲክ ስህተት፣ የጨዋታ አቀራረብ ጥፋት፣ የአሰላለፍ ክፍተት፣ በሎው ብሎክ፣ በሀይ ብሎክ ብንጫወት ኖሮ በሚል ትንተና ብቻ ከገለፅነው ለአመታት በእነ ግብፅ የተጋትነው ሽንፈት እና የልጅ ልጅ ከፍሎ የማይጨርሰው የጎል እዳ አልመረረንም ማለት ነው፡፡ ግብፆች በእኛ ላይ ያላቸው የአባይ የበላይነት በትልቅ ሐገራዊ ቁጭት ዛሬ ላይ ቢቋጭም እግር ኳሱ ግን ይሄንን ያህል ምሬት አልፈጠረብንም እና እንዳስቀጠሉት ይገኛሉ፡፡
አባይ ይሄ ነው የማይባል ገፀበረከት ያለው ወንዝ እንደሆነ ከ3ኛ ክፍል ህብረተሰብ ትምህርት ጀምሮ የሰማነው ሐቅ ነው፡፡ እንደ አባይ ሁሉ ኢትዮጵያም ከእግር ኳስ አንፃር ይሄ ነው የማይባል ተፈጥሯዊ ገፀበረከቶች ያላት ሐገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው እግር ኳስን የማዘውተር፣ የመመልከት እና የመውደድ ባህል ሌሎች ሀገራትን የሚያስቀና እና በገንዘብ ሊገዛ የማይችል እምቅ ሀብት ነው፡፡ አለም ላይ ያሉ ሐብታም ሀገራት እግር ኳስ በሀገራቸው እንዲወደድ የሚያድፋፉት ገንዘብ የትዬለሌ ነው፡፡ ለዚህ እንደ አስረጂ ሳውዲ አረቢያ፣ ኳታር (የአለም ዋንጫ ትዝ ይሏል)፣ ቻይና የሚከተሉትን የእግር ኳስ ልማት ስትራቴጂ መመልከት በቂ ነው፡፡ ሁለተኛ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው እምቅ የታዳጊዎች ችሎታ በጣም ጥቂት ሐገራት ላይ ብቻ የሚታይ ለመሆኑ የብዙ ባለሙያዎችን ተሞክሮ መጥቀስ እና ተዟዙሬ ያየኋቸውን ሐገራት ማንሳት እችላለሁ፡፡
በሶስተኝነት ኢትዮጵያ በአለም ይቅርና በአፍሪካ ላይ ትልቅ የእግርኳስ ታሪክ የበላይነት ያላት፤ ለሌሎች ማጣቀሻ እና ማሳያ ልትሆን የምትችል ሐገር ነበረች፡፡ ኢትዮጵያ እግር ኳስን ስትጀምር ከቅኝ ግዛት ያልወጡ ብሎም ያልተፀነሱ አፍሪካዊ ሀገራት የትዬለሌ ናቸው፡፡ ሌላው ቢቀር በቅኝ ግዛት ስር አለመውደቃችን ከሌሎች አፍሪካ ሀገሮች ጋር ከመጋጠማችን በፊት ልብ የሚያርድ፣ ጀብደኝነትን የሚያዋርስ፣ የበላይነትን የሚያጎናፅፍ የወል ትርክት ነበር፡፡ ይሄንን የማይሸጥ የማይገዛ፣ የማይዳሰስ፣ የማይጨበጥ የስነ ልቦና ሐብት (Psychological Resource) ፍፁም አልተጠቀምንበትም፡፡
ሌላኛው የኢትዮጵያ ወረት የአየር ንብረቷ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምእራብ እስከ ምስራቅ በቀን 24 ሰዓት አመቱን ሙሉ ኳስን ለማዘውተር የሚያስችል የአየር ንብረት አለ ለማለት ያስደፍራል፡፡ ይሄ ለብዙ ሀገራት ቅንጦት ነው፤ አሁን አሁን በአለም እግር ኳስ ካርታ ላይ ብቅ እያለች የመጣችው አይስላንድ ሊጓን ከ 3 እና 4 ወራት በላይ ማከናወን አትችልም፡፡ የበረዶው ግግር እና ብርድ ለመጫወትም ሆነ ተመልካችን ለመሳብ አይመችም እና ፀሀይ ሳትጠልቅባቸው ማጠናቀቃቸው የግድ ነው፡፡ በረዶ እና ጭለማ የአመታቸውን ግማሽ ያህል የሚወስድባቸው የስካንዲኒቪያን ሐገራት ልጆቻቸው በቅጡ እግር ኳስን እንዳያዘወትሩ እና በቤት ውስጥ ስፖርቶች ብቻ እንዲገደቡ አስገድዷቸዋል፡፡
ሌላኛው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ሐብት በማለት የማቀርበው የህዝብ ብዛቷን ነው፤ 130 ሚሊየን ህዝብ ማለት እግር ኳስን ለማሳደግ ትልቅ ሀብት ነው፡፡ ምንም እንኳን 130 ሚሊየኑም ኳስ ይችላል፣ ፍላጎቱም፣ ታለንቱም አለው ማለቴ እንዳልሆነ የሚታወቅ ቢሆንም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን 10 ቁጥር መለያ ለመሸጥ እና ለመግዛት ይሄንን ያህል ሰፊ የማርኬት ሴግመንት አለ እያልኩ ነው፡፡ ትላንት ከሳጥን እስከ ሳጥን ኳስ እየገፋ (መንገድ አደረገን እንጂ) ጎል ያገባብን የሴራሎናዊውን 8 ቁጥር መለያ ከ8 ሚሊየን ህዝብ በላይ ፈላጊ የለውም፡፡ የኤርትራዊውን 10 ቁጥር አሊ ሱሌማንን መለያ ለመግዛት የሚፈልጉ ኤርትራውያን ቁጥር የአዲስ አበባን ግማሽ ወይም 3.5 ሚሊየን ብቻ መሆናቸውን ስናውቅ ምንያህል ሰፊ ሀገር፣ ሰፊ ህዝብ፣ ሰፊ ኢንዱስትሪ እንዳለን እንረዳለን፡፡
ይሄ ሁሉ ሀብት እያለን እግር ኳሳችን ግን እንዳልተገደበው አባይ ሊረባን አልቻለም፡፡ ብዙ ሀብታችንን ጠራርጎ ይወስድ የነበረው አባይ፣ ሞራላችንን ይነካ የነበረው አባይ፣ ስንቃችንን ይቀማን የነበረው አባይ፡፡ የሚዘፈንለት… የሚዘፈንበት ግን ስራ አልቦ የነበረው አባይ፡፡ ልክ እንደ ቀድሞው አባይ ሁሉ የኢትዮጵያ እግር ኳስም ከዚህ የተለየ ባህሪ የለውም፡፡ እምቅ የታዳጊዎች ችሎታ የሚመክንበት፣ ከፍተኛ የገንዘብ ሐብት የሚባክንበት፣ ኢትዮጵያውያን ላይ የተሸናፊነት ስነ ልቦና የሚጭን፣ አንችልም ባይነትን የሚያስተምር፣ አንገት የሚያስደፋ፣ አሳንሶ የሚያሳይ፣ የሚያንበረክክ፣ ከልማት ይልቅ ጥፋት፣ የጨዋታ ማጭበርበር፣ ሙስና፣ ስንፍና፣ ከአንድነት ይልቅ ልዩነት፣ ብሄርተኝነት፣ አሁን አሁን ደግሞ የሀይማኖት ቡድንተኝነት ጎልቶ የሚታይበት ዘርፍ እየሆነ መጥቷል (ፅሁፉ እንዳይረዝም ስጋት ገብቶኝ እንጂ በዳታ፣ በሀሳብ እና በምስል ለሁሉም አመክኖዬ አስረጂ ማቅረብ እችላለሁ)፡፡
በቀድሞው አባይ ዙሪያ ሁለት አካላቶች ነበሩ፤ ‹‹የላይኛው ተፋሰስ›› እና ‹‹የታችኛው ተፋሰስ ሐገራት›› ተብለው የሚጠሩ፡፡ የላይኛው ተፋሰስ ሐገራት የሚባሉት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሐብት ንብረታቸውን በአባይ የሚነጠቁ፣ ከምድር በላይም ሆነ በታች ያለው ሀብታቸውን የሚዘረፉ፣ ተስፋቸው የሚነጉድ፣ ሁሌ ጉም ውስጥ የሚገባባቸው ሲሆኑ የታችኛው ተፋሰስ ሐገራት የሚባሉት ደግሞ እንደ ግብፅ እና መሰሎቿ ያሉ ሲሆኑ አባይ ተድላቸው፣ አባይ ፍሰሀቸው የሆነላቸው፤ ምንም እሴት ሳይጨምሩ ከወንዙ የሚጠቀሙ፣ ከእፍታው የሚወስዱ፣ የመኖራቸው ዋስትና፣ የልጅ ልጆቻቸው ህልውና የሆነላቸው ማለት ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስም እንደ ቀድሞው አባይ ነው፤ የላይኛው እና የታችኛው ተፋሰስ አካላት በሚባሉ ሁለት አካላት መሀል የሚዋልል አይነት ነገር ነው፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ‹‹የላይኛው ተፋሰስ አካላት›› የሚባሉት ተፈጥሮ ከፍተኛ አቅም እና ችሎታ ያደላቸው ኢትዮጵያውያን ታዳጊዎች እና እነሱን ተስፋቸው ያደረጉ ቤተሰቦቻቸው፣ እግር ኳስን አብዝተው የሚወዱ ኢትዮጵያውያን፣ ሳይሰስቱ በገንዘባቸው፣ በሙያቸው፣ በእውቀታቸው የኢትዮጵያን እግር ኳስ የሚደግፉ ሲሆኑ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ‹‹የታችኛው ተፋሰስ አካላት›› የሚባሉት ደግሞ እግር ኳስ ውስጥ ይሄ ነው የሚባል ግብአት የሌላቸው፣ በእግር ኳሱ ውስጥ ነውር ዘርተው፣ ነውር ኮትኩተው ያሳደጉ፣ የነውሩም አንደኛም፣ ሁለተኛም፣ ሶስተኛም፣ የመጨረሻም ደረጃ ተጠቃሚ የሆኑ ማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያ መሸነፍ ግድ የማይላቸው፣ የክለቦች መንኮታኮት የማያንገበግባውቸው፣ የእግር ኳስ ኢንዱስትሪው መድቀቅ የማይሰማቸው፣ የታዳጊዎች ስልጠና አለማግኘት የማያማቸው፣ የከተማው እና የአካባቢውን ታዳጊዎችን ህልም በስጋ ልጆቻቸው የስጋ ወጥ ምሳ እቃ የሚቀይሩ እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡
የቀድሞው አባይ በቅኝ ግዛት ውል የሚተዳደር ሐብት ነበር፤ የኢትዮጵያ ስፖርት (ለዚህ ፅሁፍ ሲባል እግር ኳስ) ግን አሁንም በቅኝ ግዛት ውል የሚተዳደር በሐገር በቀል ቅኝ ገዢዎች ስር የወደቀ ዘርፍ ነው፡፡ ከክለብ እስከ ከተማ፣ ከከተማ እስከ ክልል፣ ከክልል እስከ ፌዴራል ድረስ የቅኝ ግዛት አስተሳሰቦች እግር ኳሱን አንቀው ይዘውታል፡፡ ይህ ደግሞ ከክለብ አመራር፣ እጩ አቀራረብ፣ የምርጫ ስርአት፣ የጠቅላላ ጉባኤ ጥንቅር ድረስ የሚዘልቅ ሲሆን በፖለቲካ አመለካከት፣ በብሄር፣ በአበልጅነት፣ በጉርብትና፣ በዘር፣ በእከክልኝ ልከክልህ፣ በጥቅም ትስስር እና በሌሎች ኢ-ስፖታዊ ግኑኝነት የተተበተቡ ‹‹የታችኛው ተፋሰስ አካላት›› ዛሬም ድረስ የኢትዮጵያን እግር ኳስ በግዞት ይዘውታል፡፡ እግር ኳሱ በእውቀት ጠልነት፣ በአድርባይነት፣ በአሉባልታ፣ በአበል፣ በእጅ መንሻ እንዲሻግት አድርገውታል፡፡ ለስልጣን፣ ለእውቅና፣ ለአበል፣ ለቪዛ፣ ለኔትወርክ ሲሉ እግረ መንገዳቸውን ወደ እግር ኳስ የመጡ፤ እግር ኳስ መድረሻቸው ሳይሆን መንገዳቸው የሆኑ ሰዎች ዘርፉን ‹‹በቅኝ ግዛት ዘመን ውል›› አንቀው ይዘውታል፡፡
አሁን አሁን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ከተነሳ ጥቅሙ ሊሆን የሚችለው ለአለም እግር ኳስ እንደማስተማሪያ መወሰዱ ብቻ ነው፡፡ በፕሮፌሽናል ሊጓ አሰልጣኞቿን እና ተጨዋቾቿን በአንድ ቢበዛ በሁለት አመት ኮንትራት ብቻ የሚያስፈርሙ ክለቦች የበዙባት፤ 15 ተጨዋች ገዝቶ 15 ተጨዋች የሚለቅ ፕሮፌሽናል ክለብ አለኝ የምትል የመጥፎ እግር ኳስ አደረጃጀት ማስተማሪያ ሐገር ብትኖር ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ ሐገር ትመስለኛለች፡፡ ሌላው አለም የተጨዋች ዝውውር በብዙ ትንተናዎች ተደግፎ የሚወሰን፣ ትላልቅ ሰነዶች የሚቀርቡበት ቢሆንም ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ‹‹እመነኝ ይችላል፤ ከፈለክ ልማልልህ›› እየተባለ እንደ ሸቀጥ እና የበአል ሰሞን እንደሚታኝ መደበኛ ንግድ የእጅ መዳፍ እየተሳሳሙ የሚሻሻጡበት ሁኔታ ውስጥ ወድቋል፡፡
በአንድ የልምምድ ሜዳ ላይ አራት ፕሮፌሽናል ክለቦች (ይህን ያየ አንድ ወዳጄ ሜዳውን ፒዛ አደረጉት ብሎኛል) ለአንድ ሰአት የሚለማመዱበት ሊግ የኢትዮጵያው ሊግ ብቻ ይመስለኛል፡፡ 1970ዎቹ ላይ በአያቶቻችን የተሰራ አካዳሚ ላይ አንድ የልምምድ ሜዳ ያልጨመረ፣ አንድ ክፍል አክሎ ያላስፋፋ፣ አንድ ሚስማር ያልመታ የክለብ አመራር ስካርፕ እና ከረባት አድርጎ በዋንጫ የሚታበይባት ሀገር ብትኖር ‹‹ያልተገደበ›› እግር ኳስ ያለባት ሐገሬ ትመስለኛለች፡፡ አንድ ወሳኝ የክለብ ተጨዋች እራሱ ላይ ሆነ ብሎ ሊለቅ ይችላል በሚል በአሰልጣኝ ቡድን አባላት የሚጠረጠርበት፣ ከመጠርጠርም አልፎ ተቀያሪ ወንበር ላይ የሚቀመጥበት ሐገር ተምሳሌት ሳትሆን ለሌሎች ማስተማሪያ የመሆን እድሏ ሰፊ ነው፡፡ የዚህ መሰል በቅጡ ያልተገደበ ሙያ ውስጥ መገኘቴ በእጅጉ ያሳስበኛል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ‹‹የእግር ኳስ ልማት›› የሚል ፅንሰ ሀሳብ ፈፅሞ አይገኝም፤ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ መሪዎች እግር ኳስ ኢንዱስትሪ ሳይሆን የሆነ ‹‹ቻሪቲ›› ነገር ነው፤ ትለምናለህ፣ ታገኛለህ፣ ትጋጠማለህ፣ ታጠፋለህ ከዛ ትለምናለህ አይነት ክብ ልፋት ነገር፡፡ የእግር ኳስ ልማት እጅግ ሰፊ እና ጥልቅ አስተሳሰብ ነው፤ በውስጡ ተቋማዊ ልማት፣ መሰረተ ልማት፣ የሰው ሀብት (ታዳጊዎች፣ ተጨዋቾች እና ባለሙያዎችን ይይዛል) ልማት፣ የፋይናንስ ልማት፣ የብራንድ ልማት እና የመሳሰሉትን ያካትታል፡፡ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ እራሱን እንደ ተቋም የሚያይ ክለብ ፈልጎ ለማግኘት ይከብደኛል፤ ከሞላ ጎደል ሁሉም ሊባል በሚችል ሁኔታ ሁሉም እራሱን እንደተወዳዳሪ ቡድን ነው የሚመለከተው፡፡ እራስን እንደ ‹‹ተቋም›› መመልከት እና እራስን እንደሆነ በልመና እንደሚተዳደር ‹‹ቡድን›› መቁጠር ለየቅል ነው፡፡ አስተሳሰቡ እራሱ የተሸናፊነት፣ እራስን ያለመቻል፣ የማነስ ነው፤ ይህ ለእራስ ያለ ዝቅተኛ አመለካከት ሀገርን እና ማህበረሰብን እየጎዳ ይገኛል፡፡
በኢትዮጵያ ከ‹‹እግር ኳስ ልማት›› ይልቅ ‹‹የግጥሚያ ልፋት›› ሰፊውን ድርሻ ይይዛል፡፡ ግጥሚያው ከልማቱ ጎልቶ የወጣው ‹‹ለታችኛው ተፋሰስ አካላት›› ትልቅ የቅሸባ መሳሪያ ስለሆነ ነው፡፡ ከተጨዋች ዝውውር ይቀሸባል፣ ከአሰልጣኝ ዝውውር ይቀሸባል፣ ከአልቤርጎ እና ሆቴል ይቀሸባል፣ ከትራንስፖርት ይቀሸባል፣ ከአልባሳት ይቀሸባል፣ ሌላው ቢቀር የልምምድ ሰአት ከሚቀርብ ውሐ ይቀሸባል፡፡ ቅሸባው ከሩዝ እስከ ሙዝ እንደሚደርስ ምልከታዬ ይነግረኛል፡፡ ነጥብ ይቀሸባል፣ ካርድ ይቀሸባል… እነዚህ እና የመሳሰሉት ያልተገደበ እግር ኳስ ባህሪያት ናቸው፡፡
ምንም እንኳን ድመት ልጇን የምትበላው በተፈጥሯዊ ምክንያት ቢሆንም የኢትዮጵያ እግር ኳስ አምጣ የወለደቻቸውን ልጆቿን እንደምትበላዋ ድመት ቢጤ እየሆነ ነው፡፡ እስኪ ቢረዝምም ማሳያዎችን ላቅርብ፡፡ ከቀናት በፊት በግብፁ ጨዋታ ትልቅ አድናቆትን ያገኘው ግብ ጠባቂያችን አቡበከር ኑራ ከአይን ያውጣህ የሚያስብል አቋም አሳይቷል፡፡ አቡበከር ይሄንን ቦታ የወሰደው ከሰኢድ ሐብታሙ ነበር፡፡ ሰዒድ ብሄራዊ ቡድኑን ሲቀላቀል ይህንኑ ነበር ያልነው፡፡ ዛሬ ሰዒድ ከብሄራዊ ቡድኑ ሶስት በረኞች መሀከል አይገኝም፡፡ ሰዒድም ቢሆን ይሄንን ቦታ የወሰደው ከፋሲል ገብረሚካኤል ነበር፤ ፋሲል ግን ከብሄራዊ ቡድኑ ምርጫ በኋላ ሶስት ክለቦችን ቀያይሮ ወጥ የሆነ አቋም ማሳየት ተስኖታል፡፡ ፋሲልም ቢሆን ይሄንን ቦታ የተቀበለው ከተክለማርያም ሻንቆ ነበር፡፡ በእጅሙ በእግሩም ይችላል የተባለለት ተክለማሪያም አሁን በስደት አገሩን ለቆ እግር ኳስን ርቆ በእጁም በእግሩም መኪና ሲነዳ አንዳንዴ በቲክቶክ ላይቭ እመለከተዋለሁ፡፡ ይህ እንግዴህ የአራት አምስት አመት ታሪክ ነው፡፡ ለአጭር ጊዜም ቢሆን ከሶስቱም ጋር አብሮ እንደሰራ ባለሙያ ያልተገደበው እግር ኳሳችን የእነዚህን ተጨዋቾች የአቅም ጥግ ሳያሳየን እንድናጣቸው፣ አንዱ በአንዱ አንዲተካካ አድርጓል፡፡ አቡበከር በዚህ መለያ አመታትን ሐገሩን እንዲያገለግል ብመኝለትም ይሄ ‹‹የአልፎ ሂያጆች እግር ኳስ››፣ ‹‹የታችኛው ተፋሰስ አካላት›› እግር ኳስ ግን መድረስ የሚችልበት እንዳይደርስ ሊያደናቅፈው እንደሚችል እና የድመቷ እጣ እንዳይደርሰው የሚል ፍርሀት አለኝ፡፡
ሌላ አስረጂ ላክል፤ ከድህረ ደደቢት ዘመን (Post Dedebit Era) በኋላ ከፍተኛ ገንዘብ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ እየተረጨ ይገኛል፤ ሆኖም ግን ኢትዮጵያን በሚመጥን ልክ ተጨዋች ለማግኘት አልቻልንም፡፡ ይህ ከሆነ ከ2004 ዓ.ም በኋላ ይሄ ነው የሚባል ተጨዋች በክለብም ሆነ በብሄራዊ ቡድን ደረጃ በተከታታይነት ወጥ የሆነ አቋም ሲያሳይ አልተመለከትኩም፡፡ ወጣ ገባ፣ ብርት ጥፍት ከሚሉ ተጨዋቾች በስተቀር የብሄራዊ ቡድኑን መለያ በተከታታይነት የሚለብሱ፣ በክለባቸው ከፍተኛ ሚና ያላቸውን ተጨዋቾች ማፍራት አልቻልንም፡፡ ለምን? ምን አልባትም ከዚህ ሰለባ የተረፉት የመጨረሻው ትውልዶች ሽመልስ በቀለ እና ጌታነህ ከበደ ይመስሉኛል፡፡ ከእነሱ በፊት አዳነ ግርማ፣ ሳልሀዲን ሰዒድን መጥቀስ ይቻላል፤ ትንሽ አለፍ ካልን ደግሞ አሸናፊ ግርማ፣ ሙሉ አለም ረጋሳን እናገኛለን፡፡ ወደ ኋላ ከተጓዝን ደግሞ አሊ ረዲ፣ ዮርዳኖስ አባይ፣ አሰግድ ተስፋዬ፣ ኤልያስ ጆሀርን ማንሳት እንችላለን፡፡ እያልን እያልን ከጠቀስን ሁሉም ትውልዶች ሁሉንም ያግባቡ አውራዎች ነበሯቸው፡፡
በእኔ ዘመን ግን እንደነዚህ አይነት በክለብም ሆነ በብሄራዊ ቡድን የአይን ብሌን የሆኑ፣ እነሱ ከሌሉ ጎዶሎነት እንዲሰማን የሚያደርጉ ተጨዋቾችን ማፍራት አልቻልንም፡፡ ምንም እንኳን ትልቅ አቅም ያላቸውን እነ አቡበከር ናስር፣ ሱራፌል ዳኛቸው፣ አማኑኤል ገ/ሚካኤል፣ ያሬድ ባዬ፣ አስቻለው ታመነ፣ አቤል ያለው፣ ከነአን ማርክነህን አይነት ተጨዋቾች ወደፊት ቢመጡም በዙሪያቸው ያለው የእግር ኳስ ስርዓት ዘመኑን የዋጀ እና አለም አቀፍ ተፎካካሪ ባለመሆኑ የአንዱንም ፍሬ በቅጡ ሳናጣጥም ጊዜያቸው እያለፈ ይገኛል፡፡ የቀድሞዎቹ በ2500 እና በ250 ብር ያሳኩትን ገድል፣ ክብርና ስኬት የአሁኖቹ በ250ሺህ ብርም የከበዳቸው ደካሞች ሆነው ሳይሆም በዙሪያቸው ያለው የእግር ኳስ ስርአት በሙስና የተጨማለቀ፣ በስራ እና ጥረት የማያምን፣ ተፈጥሯዊ የመትጋት ባህልን የሚገድል በአጭሩ እንደ አባይ ‹‹ያልተገደበ›› በመሆኑ ነው፡፡
ይህ ሁሉ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ያለው የኢትዮጵያ እግር ኳስ በአግባቡ ባለመገደቡ ምክንያት ‹‹ለላይኛው ተፋሰስ አካላት›› ምንም እርባና ሳይፈጥር ‹‹የታችኛው ተፋሰስ አካላትን›› ማበልፀጉን ተያይዞታል፡፡ አሁን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ማህበረሰቡ ግድ የማይለው፣ ተስፋ የቆረጠበት ዘርፍ ሆኗል፡፡ ወይ ለብሄር እና ማንነታቸው አልያም ለአካባቢ ቡድናቸው ሲሉ እግር ኳስን ከሚከታተሉ የማህበረሰብ ክፍሎች ወይም ቀጥተኛ ‹‹የታችኛው ተፋሰስ አካላት›› ቤተሰብ ከሆኑ ሰዎች ውጭ የመላው ኢትዮጵያውያንን ቀልብ መሳብ ካቆመ አመታት ተቆጥረዋል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ እንደ ቀድሞው አባይ ሁሉ ‹‹ለታችኛው ተፋሰስ ሐገራት ያዳላ››፣ ‹‹በቅኝ ግዛት ዘመን ውል የተተበተበ››፣ ‹‹ያልተገደበ››፣ አንጡራ ሐብታችንን ወይም ‹‹የልጆቻችንን ታለንት›› እየበላ ያለ ኢንዱስትሪ ነው፡፡ ያልተገደበ እግር ኳስ፣ ስርዓቱን ጠብቆ መስመር ውስጥ ያልገባ እግር ኳስ ደግሞ ከልማቱ ጥፋቱ ያመዝናል፤ ሐብት ይቆርሳል… ሐብት ይዘርፋል! የበታችነት ስሜትን ለትውልድ ያወርሳል!
የኢትዮጵያ እግር ኳስ በመንግስት ደረጃ በጠንካራ ሐገራዊ አመራር እና ትላልቅ ህልም ባላቸው፣ ትንሽ ነገር በማያረካቸው፣ ጥቃቅን ስኬቶች በማያኮፍሳቸው ሰዎች ሊገደብ ይገባዋል፡፡ ትክክለኛውን የእግር ኳስ አቅም የተረዱ፣ በእግር ኳስ ምክንያት ትውልድ እየደረሰበት ያለውን የሞራል ስብራት፣ የተንበርካኪነት ስነልቦና ሊያሽሩ የቆረጡ ሰዎች ያስፈልጉናል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ከሌለው ያለው ነገር ያመዝናልና እንደግለሰብም ሆነ እንደባለሙያ ተስፋ አያስቆርጠኝም፤ አንድ ወደ መስመር የሚያስገባው፣ ‹‹የሚገድበው››፣ ‹‹ሀይ ባይ›› አካል ከተገኘ እንደ አባይ ግድብ የምንዘክረው ዘርፍ፣ ውለታውን መመለስ የሚከብደን ኢንዱስትሪ እንደሚሆን አልጠራጠርም፡፡
ስለፀሀፊው
ፀሀፊው ሳሙኤል ስለሺ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ ት/ክፍል የእግር ኳስ እና የስፖርት ስነልቦና መምህር ሲሆኑ ሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በስዊድኑ ሉንድ ዩኒቨርሲቲ እና በጀርመኑ ሊያፕዚግ ዩኒቨርሲቲ ተከታትለዋል።