ቀዝቃዛ የዝውውር እንቅስቃሴ ያደረገው የ2016 ሻምፒዮን የቅድመ ውድደር ዝግጅቱን መጀመሩ ታውቋል።
አሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድን ለተጨማሪ ዓመት በቡድኑ እንዲቆዮ ያደረገው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከዓመታት በኋላ ወደ ሊጉ ባደገበት 2016 የሊጉ ቻምፒየን መሆን ቢችልም ባሳለፍነው የውድድር ዓመት ግን ፈታኝ ጊዜ ማሳለፉ ይታወሳል። ለ2017 የውድድር ዘመን እራሱን አጠናክሮ በመቅረብ የ2016 ጥንካሬ ለመድገም በዝውውሩ የነቃ ተሳትፎ ያደርጋል ተብሎ ቢጠበቅም የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋቾች ግብ ጠባቂ ፍሬው ጌታሁን ፣ ፈቱዲን ጀማል፣ ሱሌይማን ሀሚድ፣ ኤፍሬም ታምሩ፣ ብሩክ እንዳለ፣ ባሲሩ ኡማር እና ኪቲካ ጅማን ማቆየት ተስኖት አጥቷል።
ሆኖም ቡድኑ በክረምቱ የዝውውር መስኮት የሦስት ነባር ተጫዋቾቹን እንዳለ ዮሐንስ፣ ዮናስ ለገሰ እና ዳዊት ዩሐንስን ውል ሲያራዝም ግብጠባቂ ጆርጅ ደስታ፣ ብሩክ ብፁአምላክን ከከፍተኛ ሊግ ሲያመጣ መስፍን ዋሼን ከሊጉ ማስፈረም ችሏል።
ከፋይናስ ሥርዓቱ ጋር በተያያዘ የተጠበቀውን ያህል የዝውውር እንቅስቃሴ ያላደረገው ቡድኑ በቀጣዮቹ ቀናት ከከፍተኛ ሊግ ተጨማሪ ተጫዋቾችን ለማምጣት እንደሚንቀሳቀስ የሰማን ሲሆን የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ከቀናት በፊት መቀመጫውን በአዳማ ከተማ በማድረግ ዝግጅት መጀመሩን አውቀናል።