ባለፈው ዓመት በሽረ ምድረ ገነት ቆይታ የነበረው ተጫዋች አዲስ ክለብ ተቀላቅሏል።
በ2017 በሀገሩ ክለብ ቡል የነበረው ውል መጠናቀቁን ተከትሎ ወደ ሽረ ምድረ ገነት አምርቶ በውድድር ዓመቱ በአስራ ሰባት ጨዋታዎች ተሳትፎ 880′ ደቂቃዎች ቡድኑን ያገለገለው ዩጋንዳዊው አጥቂ አሌክስ ኪታታ ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ወደ ቀደሞ ክለቡ ቡል ተመልሷል። ሴንት ሙኩኖ ከተባለው የመጀመርያ ክለቡ በኋላ ለ UPDF ፣ ቪላ፣ ኪታራ፣ ጋዳፊ፣ ቡል እና ለሩዋንዳው ኪዮቩ ስፖርት መጫወት የቻለው ይህ የ33 ዓመት አጥቂ ባለፈው ዓመት በሲዳማ ቡና ቆይታ ከነበረው ግብ ጠባቂው ቶማስ ኢካራ ቀጥሎ ከኢትዮጵያ ክለብ ወደ ቡል የተቀላቀለ ሁለተኛው ተጫዋች ሆኗል።
ቤንዜማ በሚል ቅፅል ስም የሚታወቀው ተጫዋቹ በሽረ ምድረ ገነት ከነበረው ቆይታ በፊት ቡል ሁለተኛ ደረጃ ይዞ እንዲያጠናቅቅ የረዱ አስር ግቦች ማስቆጠር የቻለ ሲሆን አሁን ደግሞ ካልተሳካው የአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ወደ ቀድሞ ክለቡ ተመልሷል።