ወሳኙን የግብ ዘባቸውን በጉዳት ያጡት ኢትዮጵያ መድኖች ግብ ጠባቂ ለማስፈረም መቃረባቸው ታውቋል።
በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ የመጀመርያ ዙር የማጣሪያ የደርሶ መልስ ጨዋታቸውን በድል ያጠናቀቁት የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ የሆኑት ኢትዮጵያ መድኖች ሳይጠበቅ ግብ ጠባቂውን ፋሲል ገብረሚካኤልን ለማስፈረም መስማማታቸውን አውቀናል።
ባሳለፍነው ቅዳሜ ወደ ታንዛኒያ አቅንተው ምላንዴግን በደርሶ በደርሶ መልስ የድምር ውጤት በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፉቸውን ባረጋገጡበት ጨዋታ ወሳኙ የክለቡ ግብ ጠባቂ አቡበከር ኑራ ረዘም ላሉ ቀናቶች ከሜዳ የሚያርቀውን ጉዳት ማስተናገዱ አይዘነጋም ።
ይህን ተከትሎ የእርሱን ሁነኛ ተተኪ በማሰብ በቅርቡ ከፋሲል ከነማ ጋር በስምምነት የተለያየውን ፋሲል ገብረሚካኤልን ለማስፈረም መስማማታቸውን አውቀናል። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በተለያዩ ዕድሜ እርከኖች መጫወት የቻለው የግብ ዘቡ ከዚህ ቀደም በዳሽን ቢራ ፣ በሰበታ ከተማ፣ በባህር ዳር ከተማ ፣ በቅዱስ ጊዮርጊስ፣ በሽረ ምድረ ገነት እና በፋሲል ከነማ ሲያገለግል መቆየቱ ይታወሳል።