ጉዳት ባስተናገደው ያሬድ ካሳዬ ምትክ ሌላኛው የመስመር ተከላካይ የዋልያዎቹን ስብስብ ተቀላቅሏል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ ማጣሪያና ከጊኒ ቢሳው እና ቡርኪና ፋሶ ጋር ለሚያደርጋቸው የመጨረሻ የምድብ ጨዋታዎች ዝግጅት አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ለ20 ተጫዋች ጥሪ ማድረጋቸው ይታወሳል። ሆኖም ጥሪ ከተደረገላቸው ተጫዋቾች መካከል የኢትዮጵያ መድኑ ግብ ጠባቂ አቡበከር ኑራ በቻምፒየንስ ሊጉ የመልስ ጨዋታ ጉዳት በማስተናገዱ ለድሬዳዋ ከተማው ግብ ጠባቂ ፍሬው ጌታሁን ጥሪ መደረጉን ትናንት አሳውቀናችሁ ነበር።
ብሔራዊ ቡድኑ ዛሬ የሁለተኛ ቀን ልምምዱን በ19 ተጫዋቾች በአዲስ አበባ ስታዲየም እያደረገ የሚገኝ ሲሆን ከቡድኑ ጋር የማይገኘው ደግሞ ጉዳት ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ መድኑ የግራ መስመር ተከላካይ ያሬድ ካሳዬ ነው።
አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪም በዚሁ ጉዳት ባስተናገደው የመስመር ተከላካዩ ያሬድ ካሳዬ ምትክ ለድሬዳዋ ከተማው የመስመር ተከላካይ አብዱልሰላም የሱፍ ጥሪ ማድረጋቸው ሲታወቅ ተጫዋቹ ከድሬደዋ ዛሬ ወደ መዲናዋ በመምጣት ቡድኑን የሚቀላቀል ሲሆን ነገ ወደ ልምምድ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።